የትምህርቱ ርዕስ | ትዝብት

ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው ፣
ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አምቡላው ፣
ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ ፣
ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ ፣
ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ ።

ዛሬን ያስረሳኛል የምንለው የዓመት ልቅሶ ይዞ ይመጣል ። ለአንድ ብር ችግር መቶ ብር ይከፈላል ። ችግሩ የታወቀ ነው ፣ መፍትሔው ችግር ሲሆን ግን ግራ የሚያጋባ ነው ። ለመዝናናት በሄዱበት አዝነው መመለስ ፣ ለማስደሰት ሞክሮ ሰውን ማሳዘን በሕይወት ጉዞ ውስጥ ተደጋጋሚ ነው ። ችግሮችን ለመርሳት ከመሞከር መፍትሔውን መፈለግ ጊዜና አቅምን ይቆጥባል ፣ ችግርን በችግር ለማጥራት መነሣሣት ወደ ኀዘን ሸለቆ መውረድን ያስከትላል ። በእኔ የሚሆነው በሁሉ የሚሆን ነው ። የሆነውም ሲሆን የነበረ ፣ ወደፊትም የሚሆን ነው ብሎ መቀበል ብርታት ይሰጣል ። እኛ የምንቀጥለው እንጂ እኛ የምንጀምረው ደስታም ኀዘንም የለም ። ሺህዎች ባለፉበት የሕይወት መንገድ ላይ ሺህ ትምህርት ተቀምጧል ። ታሪክን ማንበብ የሚጠቅመው አዲስ ነገር በዓለም ላይ እንደሌለ ለመረዳት ነው ። ሦስት ትምህርቶች ለማንኛውም ነገር ይጠቅማሉ ይባላል፡- ሂሣብ ፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ ማወቅ ። ታሪክን ማወቅ የዛሬው ችግር ዛሬ እንዳልጀመረ ያሳየናል ። ትላንት ያለፉት ምን መፍትሔ ተጠቀሙ የሚለውንም ያስገነዝበናል ። ብቻ ለደስታ የምንሞክረው ነገር በመጨረሻ የሚቀረው በራስ መናደዱ ሊሆን ይችላል ። ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው ። የጠላ መጨረሻ ጠላ አይሆንም ። የአቋራጭ ደስታ መጨረሻውም ደስታ ሊሆን አይችልም ። ደስታ በፊት በር እንጂ በጓሮ በር ገብታ አታውቅም ።

ከከበሩ ሰዎች ጋር መዋል ፣ የከበረ ሰው ወዳጅና አጫዋች መሆን የራሱ መነቃቃት አለው ። የትልቅ ሰው ወዳጅነት አእምሮንም አካልንም ይቆጣጠራል ። የሌለንን ትልቅነት ያገኘን ስለሚመስለን ዕድላችን ያመልጠናል ። ከትልቅ ጋር ቢያዩን ይፈሩናል እንጂ አያግዙንም ። አማልደን ይሉናል እንጂ ወዳጅ አይሆኑንም ። መሰላል የሚወጣበት እንጂ የሚኖርበት ወዳጅ የለውም ። ድልድይ ይሻገሩበታል እንጂ ማንም አያስበውም ። ቶሎ ለማምለጥ ይጣጣሩበታል ። የድልድዩ ስም የሚነሣው ፣ በዜና የሚነገረው የተሰበረ ዕለት ነው ። ትልቅነትና የትልልቆች ወዳጅነት የስብራት ቀኑ በጉጉት የሚጠበቅ ነው ። ትንሽነት የሚሰማቸው ሰዎች በትልልቆች ውርደት በደስታ ይፈነጫሉ ። ትልቅነት ቢያዝዝ እንጂ መራመድ አይችልም ። ትልቅ የሆነው ራስ እግር እያጣ ያሰበውን ሳይፈጽም ዘመኑ ይቋጫል ። የንጉሥ መጠጥ ነው የሚባለውም ጠጅ መጨረሻ ላይ አምቡላ ሆኖ ይጣላል ። “ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አምቡላው” እንዳሉት ነው ። የትልልቆች ወዳጅ የሆኑ ዘመን ይከዳቸዋል ። ትልቁ ሰው እልፍ ሲል እጅ እንዳልተነሡ ሰላም የሚላቸው ያጣሉ ፣ የአንድ ምስኪን ክብር ያጣሉ ።

የምንጋደልበት ፣ በአምሮት የምንሰቃይበት ፣ ስርቆት ውስጥ የሚከተን ያ ፍላጎት መደምደሚያው የማይረባ ይሆናል ። ያሸነፍነው ሰው አንድ ቀን ሊያሸንፈን ይመጣል ። እኛ በአሸናፊነታችን ደስ ሲለን እርሱ ግን ማደጉን ለመለካት በእግር ኮቴአችን ላይ እግሩን ሲለካ ነበር ። “የናቁት ያደርጋል ዕራቁት” እንዲሉ የተኛው ውሻ እኛ ላይ ሊነሣሣ ፣ ሞኙ ብልጥ ሊሆን ይፈልጋል ። በዓለም ላይ ያለው ጠብ ሁሉ መነሻው ፍቅር ነው ። ዛሬ አፋፍ ላይ ደርሶ የምናየው የኢትዮጵያና የኤርትራ እሰጥ አገባ መነሻው ያሸለመ ፍቅር ነው ። በአንድ አፍንጫ ካልተነፈስን ፣ በአንድ መቀመጫ ካልተቀመጥን ያልንበት ነገር ሁሉ የማይሰበር አጥንት የሚሆንበት ጊዜ አያሌ ነው ። የምናኝከው ሥጋ መጨረሻው አጥንት ነው ፣ አጥንቱን ከተጫወቱበት ፣ ጊዜ ይህንንም ያሳያል ካሉበት ትምህርት አለው ።

ሰው ሲቸግረው ይበደራል ፣ ባለጠጋን ባለጠጋ ያደረገው ከሥራ በላይ ብድር ነው ። የብድር ጥቅሙ ሲሠሩበት ፣ በጊዜው ሲመልሱት ነው ። ከግለሰብም ከተቋምም እንደገና ለመበደር የሚያስብ ሰው ፈጥኖ መመለስን ፣ ሳይጠየቅ መስጠትን ማወቅ አለበት ። ቀስ ቀስ እያሉ ዕዳም ይቃለላል ። የረዳንን መርዳት ፣ ያገዘንን ማገዝ አይቀርም ። የምንኖረው ብድር ለመመለስም ነውና ።

በዚህ ዓለም ላይ ራስን እንደ መታዘብ ያለ ብርቱ ነገር የለም ። በርግጥ ራስንም ከታዘብን ሕሊና ጥሎን አልሄደም ማለት ነው ። ትዝብት ወደን ስንጠላ ፣ አብደን ስንሰክን ፣ ልሙትላችሁ ብለን ካልገደልሁ ስንል ለራሳችን የምንሰጠው አነስተኛ ዋጋ ነው ። ሰዎችን እንታዘባለን ። አንቱ ብለውን አንተ ሲሉን ፣ ወንበር እንዳልመረጡልን ወንበር ሲያነሡብን ፣ አፈር ልብላልህ እንዳላሉ አፈር ሲያበሉን እንታዘባለን ። ሰላም ለማለት እንኳ ጉዳይ ካልገጠማቸው የማይፈልጉንን ሰዎች ስናስብ እንታዘባለን ። ብልጠት ቶሎ ይታወቃልና ለትዝብት ይዳርጋል ፣ ሰዎች ሳይነግሩን የሚሸሹን ሲታዘቡን ነው ። መታዘብ ግን ስስ ሕመም ነውና ቆይቶ ሊጥለን ፣ ብቸኛ ሊያደርገን ይችላል ። ትላንት እንሞትለታለን ይሉለት የነበረውን ሃይማኖትና ርእዮት የጣሉ ሰዎችን ስናይ ፣ ዝምታ ሳለ ወደ መርገም የገቡትን ስንሰማ እንታዘባለን ። ሊያልፍ ቀን የማያልፍ ንግግር የተናገሩ ተሸማቀው ይኖራሉ ። ሁሉም ነገር ሊረሳ ይችላል ። ትዝብት ግን አይረሳምና ከሚያስተዛዝብ ግብር እንራቅ ።

ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው ፣
ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አምቡላው ፣
ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ ፣
ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ ፣
ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ ።

ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ