የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትጉና ጸልዩ

 የተጋነው ለምንድነው ? የተጋነው ለጸሎት ሳይሆን ለወሬ ፣ ለወንጌል ሳይሆን ለመረጃ ፣ ለፍቅር ሳይሆን ለሐሜት ፣ ለእርቅ ሳይሆን ለማባላት ፣ ለምስጋና ሳይሆን ለትችት ፣ ለአንድነት ሳይሆን ለመከፋፈል ፣ ለይቅርታ ሳይሆን ለቂም ፣ ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ ፣ የወደቀን ለማንሣት ሳይሆን ለመርገጥ ፣ ለማበርታት ሳይሆን ለመፍረድ ፣ ለመስጠት ሳይሆን ለመቀበል ፣ ለመባረክ ሳይሆን ለመራገም ፣ ሆሳዕና ለማለት ሳይሆን ስቀለው ለማለት ፣ ለማሳመን ሳይሆን ለማውገዝ ነው ። ለእግዚአብሔር ሥራ ካልነቃን ለሰይጣን ሥራ እንነቃለን ።
ስለ ሰዎች ብዙ እናውቃለን ፣ በፍርድ ቀን ስለምንጠየቅበት ስለ ራሳችን ግን ምንም አናውቅም ። ሰዎች አጠፉ እንላለን ፣ የራሳችንን ስህተት ግን ካባ እናለብሰዋለን ፣ በእነ እገሌ ቍጣ መጣብን እንላለን ፣ ራሳችንን ግን የእግዚአብሔር ባለሟል እናደርጋለን ።

ለቁርስ ሃያ ደቂቃ እንመድባለን ፣ ለአምስት ደቂቃ ግን ከልባችን አንጸልይም ። ለገንዘብ ስምንት ሰዓት እንሮጣለን ፣ ለእግዚአብሔር ሥራ ግን ምንም አንሮጥም ። ለስፖርት ሁለት ሰዓት መድበናል ፣ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ግን ደክሞናል ። ለዜና ሠላሳ ደቂቃ እንሰጣለን ፣ ለቃሉ ግን አሥር ደቂቃ የለንም ። ለፊልም ሁለት ሰዓት ሰጥተናል ፣ ድሆችን ለመጎብኘት ግን አንድ ደቂቃ የለንም ። ለሻይ ቡና ሠላሳ ደቂቃ አለን ፣ ለምስክርነት ግን ምንም ሰዓት የለንም ። ከጓደኞቻችን ጋር ሦስት ሰዓት እናወራለን ፣ ከመንፈሳውያን አባቶች ጋር ግን የውልብታ ያህል ጊዜ ሰጥተናል ። ስንት ሰው እንደ ሞተ ለመስማት እንጓጓለን ፣ ስለ ዳነ ሰው ለማመስገን ግን ግዴለሽ ነን ። ጊዜን ላልሰጠን ዓለም ጊዜ ሰጥተናል ፣ ጊዜን ለሰጠን አምላክ ግን ጊዜን ነፍገናል ።ጥቅጥቅ ያለ የጋዜጣ ጽሑፍ ሃያ ገጽ እናነባለን ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንብቡ ስንባል የማንበቢያ መነጽር አልገዛሁም እንላለን ። የስድብ ጹሑፍ አሥር ገጽ እናነባለን ፣ የእግዚአብሔርን ቃል አሥር መስመር ለማንበብ ለጥሩ ዘመድ የሚሆን እንባ እናፈሳለን ፣ እናፋሽካለን ። ጀርባችንን የሰጠነውን እግዚአብሔር በክፉ ቀን እንሻዋለን ፣ ክፉ ቀን አልፎ ያልጨረስነውን ክፋት ለመጨረስ ዕድሜ እንለምነዋለን ። አዎ ትጉና ጸልዩ ።
ዓይናችን እንባ እያፈሰሰ ፣ ልባችን ይስቃል ። እያዘንን መልሰን እናፌዛለን ። ምስኪን ነው እያልን ዞር ብለን ከባድ ሰው ነው እንላለን ። በአፋችን እሺ እያልን በልባችን እንቢ እንላለን ። ካንተ በፊት ያድርገኝ እያል ያለ ድምፅ ደሀው ምን በወጣኝ እንላለን ። አድናቂህ ነኝ እያልን በውስጣችን “ሰው መሳይ በሸንጎ” በማለት እንሳደባለን ። ሰጠሁ እያልን በልባችን ስንት አተርፋለሁ እንላለን ። መነንኩ እያልን ከነቆባችን እንዘላለን ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዲሱን ኪዳን ድንቅ ሥርዓት ከመሠረተ ፣ ደቀ መዛሙርቱንም ካቆረበ በኋላ ትጉና ጸልዩ አላቸው ። ሰዓቱ ምሽት ነው ። ዓለም ጌታን ለመስቀል የተሰናዳችበት ነው ። ቦታው የጌቴሴማኒ ጫካ ነው ። ይሁዳ ጠላት እየመራ ሊመጣ ነው ። ተግተው ካልጸለዩ ጨለማው ሊያስደነግጣቸው ፣ ከዓለም ጋር ጌታን ሊሰቅሉ ፣ በጫካው ውስጥ ከይሁዳ ጋር አምላክን ሊሸነግሉ ይችላሉ ። ተግተው የሚጸልዩት ከራሳቸው ለመዳንም ነው ። ክዳት የሚገባብን የውጭ ወራሪ ሳይሆን ከውስጣችን ብቅ የሚል ሰባሪ ነው ። እርሱን የሚጠቀጥቀው በጸሎት መትጋት ብቻ ነው ።
ከቆረቡ ፣ ከዘመሩ ፣ ኅብረት ካደረጉ በኋላም መፈተን አለ ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነው እኛ ከእርሱ ጋር እንዳንሆን አይደለም ። ያመነው በጎ ላለ መሥራት ፣ የቆረብነው ተኝቶ ለማደር ፣ ኅብረት ያደረግነው ተመሳስሎ ለመኖር አይደለም ። ጌታችን በዚህች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ ሲል ጴጥሮስ ሁሉ ቢክዱህ እኔ አልክድህም አለ ። እምነት ሳይሆን ፉከራ አሰማ ። ውጤቱ ግን ሁሉ ሳይክዱ ጴጥሮስ ካደ ። ስለ ራሳችን ያለን ከፍተኛ ግምት ፣ ስለ ሰዎች ያለን ዝቅተኛ ግምት የማይጨባበጥ ነው ። ያውም በሚያውቀን እግዚአብሔር ፊት መፎከር ከንቱ ነው ። “እመት ስመኝ ለማያውቅሽ ታጨኝ” እንዲሉ ። ጴጥሮስ በራሱ ተማመነ ። በራስ መተማመን የሥነ ልቡና ግንባታ ነው ፣ በእግዚአብሔር መተማመን ግን የሃይማኖት ፍሬ ነው ። በራስ መተማመን ሌሎችን እንዲንቅ አደረገው ፤ ሌሎችን መናቅም ተግቶ እንዳይጸልይ አደረገው ።
ጌታችን አሁንም ጴጥሮስን፡- ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።” ጸሎት ወደ ፈተና እንዳንገባ ይጋርዳል ፣ ከገባንም የውጪያውን በር ያሳየናል ። የፈተና ዘመንን ጉልበትም ሀብትም አያልፈውም ፣ ጸሎት ብቻ ድልድይ ሁኖ ከመከራ ቀን ያሻግራል ። በዚያች ሌሊት የነበረው ፈተና ምንድነው ? ስንል ክርስቶስን መካድ ነው ። በሕይወት ውስጥ ሕይወት የሆነውን ጌታ ከመካድ የበለጠ ፈተና የለም ። ያለ መጸለይ ፈተና የመካድ ፈተና ውስጥ ይጥላል ። በጸሎት የደከሙ እንደ ጴጥሮስ ሰይፍ ለመምዘዝ ይተጋሉ ፣ ለመካድ ቅርብ ይሆናሉ ። መንፈሳዊ ውጊያን በጸሎት መዋጋት ካልቻልን በሰይፍ ወይም በስድብ ሥጋዊ ውጊያ መዋጋት እንጀምራለን ።
ጴጥሮስ በራስ መተማመኑ ሌሎችን እንዲንቅ ፣ ሌሎችን መናቁ ተግቶ እንዳይጸልይ ፣ ተግቶ አለመጸለይ ፣ ሰይፍ እንዲመዝዝ ፣ ሰይፍ መምዘዝ ጌታን እንዲክድ አደረገው ።
በራስ መተማመን፡- ዓለሙ እምቅ ኃይል አለህ እያለ ይሸነግለናል ፣ እኛ በውስጣችን ያለው እምቅ ድካም ነው ። ደክመን የማናባራ ሰዎች ነን ። የአረም እርሻ እስክንመስል መልካም ነገር ይታጣብናል ። የትችላለህ ስብከቶች እውነተኛውን ወንጌል እንድንንቅ አደረጉን ። የሐሰት ነቢያት በራስ መተማመን ስብከቶችን በመስበክ በትዕቢት ይጥሉናል ። እንደ አዝማሪ ስማችንን እየጠሩ ሲያወድሱን ኪሳችን ኪሳቸው ይሆናል ። በሽታ መጥቶ ተጠንቀቁ ሲባል የእኔ እጅ በሽታ ያቃጥላል እያልን እንድንቃጠል ያደርገናል። በራስ መተማመን እንደ ባሎን በነፋሱ አቅጣጫ እንድንጓዝ ፣ እንደ ፊኛ አብጠን በአየር ላይ እንድንጎማለል ያደርገናል ። እኔ ፣ እኔ የሚሉ የበታችነት ስሜት የሚወልዳቸው ድምፆችን እናበዛለን ። እኔ ፣ እኔ በማለት ትዳር ይፈርሳል ፣ ወዳጅነት አፈር ይበላል ።
ሌሎችን መናቅ፡- የተከበረ ያከብራል ፣ የተናቀ ይንቃል ። የበታችነት ስሜት የበላይነት ስሜት ይወልዳል ። ስለ ሰዎች ክፉ ሲያወሩ የሚውሉ ስለ ራሳቸው ማሰብ የማይፈልጉ የኅሊና ቍስለኞች ናቸው ። አሁንም ስለ ሰዎች የሚያወሩ ግባቸው እኔ ትልቅ ነኝ ለማለት ነው ። ሌላውን ካላሳነሡ ፣ ሌላውን መናፍቅ ፣ የሚሸቃቅጥ ካላሉ ስቃዩ አይታገሥላቸውም ። እምነት እፎይ ያሰኛል ። የሰው ጓዳ ሲቧጥጡ ማደር አለመተኛት ፣ አለማረፍ ነው ።
ተግቶ አለመጸለይ፡- የዚህ ዓለም ዘመን በጣም አጭር ነው ። ያዕቆብ ዘመኔ አጭር እርስዋም መከረኛ ናት ያለው መቶ ሠላሳ ዓመት ኑሮ ነው ። /ዘፍ. 47፡9/ የእኛ አርባና ሃምሳ ዓመት ምን ሊባል ነው ? በአራዊት መንደር ውስጥ የሚያልፍ ሰው ሊይዛቸው የሚገቡ የተለያዩ ነገሮች አሉ ። አንበሳ ሰፈር ሲደርስ እሳት መያዝ አለበት ። አንበሳ እሳት ጎፈሬውን ከያዘ እንደማይለቀው ያውቃል ። ስለዚህ ይፈራል ። ሰይጣን የሚፈራው ፉከራን ሳይሆን ጸሎትን ነው ። በሰላም ውለን ስንገባ የሚታየን ተመስገን ብሎ ለመጸለይ ነው ወይስ ቴሌቪዥን ለመክፈት ነው ? ተግቶ መጸለይ በማዕበል ውስጥ በሰላም ያሻግራል ።
ሰይፍ መምዘዝ፡- ለጸሎት የተኛው ጴጥሮስ ሰይፍ ለመምዘዝ ነቃ ። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው በመግደል አይከብርም ። እግዚአብሔርን በጸሎት ሳይሆን በስድብ ለማስከበር የወጡ እንዴት ማስተዋል አጥተዋል ? እንኳን እግዚአብሔር የመከራቸው ጨዋ ያሳደጋቸው አይመስሉም ። ጴጥሮስ በሰይፉ የጆሮ ቀንበጥ እንደ በጠሰ ጭው የሚያደርግ ስድብ ይዘው የሚወጡ አያሌ ናቸው ።
ክርስቶስን መካድ፡- ክህደት ወይ በአፍ ወይ በተግባር ነው ። በአፋቸው እግዚአብሔር አለ እያሉ በሥራቸው ግን እንደሌለ አድርገው የሚኖሩ አሉ ።እንደ ጴጥሮስ በአፍ እየካዱ በልብ ማመን ፣ እንደ አርዮስ በአፍ እያመኑ በልብ መካድም አለ ። ክህደት ግን ሩቅ አይደለም ። ጴጥሮስም ክዷልና ። እኔ አላደርገውም አትበሉ ፣ ጴጥሮስም አላደርገውም ብሎ አድርጎታል ። ተግቶ መጸለይ ግን ይሻላል ።
ሰዓቱ ጨለማ ፣ ዓለም ክርስቶስን በክፋት ሥራዋ ልትሰቅል የወጣችበት ፣ ይሁዳ ጠላት መርቶ የመጣበት ፣ ድንዛዜ የበዛበት ቢሆንም አሁንም ተግታችሁ ጸልዩ ። በመንፈስ ካልተዋጋችሁ በሥጋ ትዋጋላችሁ ። የሥጋ ውጊያ መጨረሻው ክህደት ነው ።
ጸሎት
ጌታዬ ሆይ አንተ ራስህን ለእኔ የሰጠህበት ልክ እኔ ራሴን ላንተ ለመስጠት የሰሰትኩበት ልክ ሊወራ አይችልም ። ላንተ የሰሰትኩትን ለዓለም ሰጥቻለሁ ። ስጸልይ ለማደር ደክሜ ስበድል አድራለሁ ። አንተ ያለ እኔ ትኖራለህ ፣ እኔ ያላንተ አልኖርም ። ከማስፈልግህ ይልቅ ታስፈልገኛለህ ። እባክህን በቃልህ ላስስህ ፣ በእምነት ላግኝህ ። የጸሎት ሕይወቴን ጠግንልኝ ። መፍትሔውን እያወቅሁ እሞኛለሁ ። ፀሐይህ አይጠልቅም ፣ ፍቅርህም አይለወጥም ። ለዘላለሙ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 2
ሚያዝያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ