የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ኃይለኛው ጠላት

“በእነርሱም ፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው ።” ኤፌ. 1፡2።

በድን ባለበት አሞራ እንዲሰበሰብ እንዲሁም ሙታነ ሕሊናና ሙታነ ነፍስ ባሉበት አጋንንት ይሰለጥናሉ ። የሕሊና ሞት አለማወቅ ፣ የነፍስ ሞት ኃጢአት ነው ፤ ሞቱ ሞት ብቻ ሳይሆን ክፉ ገዥ ያለበት ነው ። በሥጋ የሞቱ በመቃብር በመፍረስና በመበስበስ ያበቃሉ ። ሙታነ ነፍስ በቁማቸው ሳሉ መንፈሳቸው የሕይወት ውኃ አጥቶ ይዝልባቸዋል ። በመንከራተትም ዘመናቸውን ይፈጽማሉ ። ሰላም አጥተው ይቸገራሉ ። ፍርሃትና ሽብር ፣ የነፍስ መድኅን ማጣት ያንገላታቸዋል ። ይህ ሞት ብቻ ሳይሆን ሞቱ አለቃ አለው ። አለቃውም ክፉ የሆነው ሰይጣን ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ያለው ኑሮ መታዘዝ የሌለበት ፣ ሐሰተኛ ደስታን ከኃጢአት የሚከጅሉበት ነው ። በዚህ ዓለም ያለው ኑሮ መምሰል እንጂ እውነት የሌለበት ፣ ከእግዚአብሔር ሥራ ሰው ሠራሽ ነገር የሚከብርበት ፣ ለመክበር ብሎ ሌላው ማዋረድ ፣ ለማግኘት ብሎ ብዙዎችን ማስጨነቅ ያለበት ነው ። የዚህ ዓለም ኑሮ ውድድሩ ስግብግብነት ፣ ሥልጣኑ ሰው በላነት ፣ ሀብቱ በድሆች እንባና ላብ ላይ የተመሠረተበት ነው ። የዚህ ዓለም ኑሮ ድንገት የሚታጠፍ ቢሆንም ሰዎች ግን እንደ ዘላለም አድርገው የሚኖሩት ፣ የሚበቃቸውን በትክክል ማወቅ ተስኗቸው አልጠግብ ባይ የሚሆኑበት ነው ። የዚህ ዓለም ኑሮ ሆድን ሞልቶ ሕሊናን የሚያራቁቱበት ነው ። የአሁን ሰው ሁኖም ነገን የሚያበላሹበት ነው ። “ሆዳችንን ለመሙላት ፣ የሞላ ታሪካችንን አናጎድልም” እንዳሉት አባት ሳይሆን የዚህ ዓለም ኑሮ ሆድን ለመሙላት ታሪክን ማጉደል ያለበት ነው ። የአፌሶን ሰዎች በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ ተመላልሰው ነበረ ።

ይህን ሕይወት ቀድሞ ጥሩ ኑሮ ይሉት ነበረ ። ሐዋርያው ግን ሙታን የሚያሰኝ ነው ይለዋል ። በቀደመው እውቀታችን የቀደመውን ኑሮ የምንሰጠው ስም አለ ፣ መጽሐፍ ደግሞ የሰጠው ስም አለ ። ቀድሞ ሕይወት የምንለውን ዛሬ ሞት ብለነዋል ። በቀድሞው ኑሮአችን ውስጥ ያሉ ደግሞ መንፈሳዊውን ሕይወት ሞት ብለው ይጠሩታል ። የጨለማው ኑሮ ካልወጡበት የሚታወቅ አይደለም ። የጨለማውን ኑሮ ስለነበርንበትና ብርሃን ስላገኘን ጨለማ ብለን መጥራት እንችላለን ። በጨለማ ውስጥ ያሉ ግን የብርሃንን ሕይወት አያውቁትምና መጥፎ ስያሜ ቢሰጡት የሚደንቅ አይደለም ። ሰው በሕይወት ሁለት ገጽ የሚያገኘው ክርስቶስ ሲደርስለት ነው ። ሙት ነበርሁ ፣ ዛሬ ግን ሕያው ነኝ ለማለት ፤ በጨለማ ነበርሁ ዛሬ ግን አያለሁ ብሎ ለመመስከር ባለሥልጣኑን ክርስቶስ ማግኘት ግድ ይላል ። በወንድነት ሳይሆን በእምነት የሚገኝ ርስት ነው ።

ሐዋርያው “ሙታን ነበራችሁ” ሲል የግዳጁን ሞት ሞታችሁ ነበረ ፣ ተቀብራችሁ ነበር ማለቱ አይደለም ። ሞታችሁ ለመኖር ወስናችሁ ነበር ማለቱ ነው ። ኖረው ለመሞት ያልወሰኑ ፣ ሞተው ለመኖር የተዘጋጁ ናቸው ። በዚህ ዓለም ያለው ኑሮ ክፉ ፣ ከእግዚአብሔርና ከሕሊና የሚለይ ነው ። ጥቂቶችን ለማኖር ብዙዎች ይሞታሉ ፣ በየዋሆች ልፋት ብልጦች ይከብራሉ ። ከመንደር እስከ አገር ፣ ከአህጉር እስከ አህጉር ጠብ የበዛበት ፣ አራዊት ሲጠፉ ሰው አውሬ የሆነበት ነው ። “ለሰው ተኩላው ሰው ነው” የሚባለው በዚህ ዓለምና በዚህ ዘመን ጎልቶ እየታየ ነው ። ሰዎች የመግደያ መሣሪያቸው የተለያየ ነው ። ጉቦ በመብላት ፣ ያለ ፍትሕ በማሰር ፣ ነጻነትን በመንፈግ ፣ ኑሮን በማስወደድ ፣ የማይገባቸውን ትርፍ በመፈለግ ፣ የጦር መሣሪያ በመሸጥ ፣ የሚፈርሱ ድልድዮችን ሠርቶ አደጋን በመጋበዝ ፣ ሰው የሚኖርበትን ቤት አድፋፍቶ በመሥራት ፣ በቃለ መሐላ የያዙትን ሙያ በገንዘብ በመሸጥ ፣ በሐሰተኛ ትምህርትና ትንቢት ያልተማሩትን በማታለል ፣ እፈውሳለሁ እያሉ በሽተኞችን በማሰቃየት ፣ እወድሃለሁ እያሉ በመሸንገል ፣ ቃላቸውን በማፍረስ … መግደልን ይፈጽማሉ ። የዚህ ዓለም ኑሮ ይህ ነው ። ከዚህ ኑሮ ሊለየን ክርስቶስ ወደ ዓለም መጣ ። ወደ ዓለማችን በመምጣቱ ዓለማችንን ቀደሰ ።

“በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ” ይላል ። የማይታዘዙ ናቸው ግን ልጆች ናቸው ። ልጅነት ይጎሳቆላል እንጂ አይቀርም ። ባሕርይም ይጎዳል እንጂ አይሰበርም ። እግዚአብሔር ሰውን በልጅ ማዕረግ ስላስቀመጠው የማይታዘዙትም ዓመፀኛ ልጆች ናቸው ። ወደ እግዚአብሔር በንስሐ ሲመለሱ አንብዐ ንስሐ ወይም የንስሐ እንባ እንደ ጥምቀት ይሆንላቸዋል ። ጥምቀት አይደገምም ። አንድ ልጅ ቢበድል በይቅርታ ከወላጆቹ ይታረቃል እንጂ እንደገና አይወለድም ። መወለድ አንድ እንደሆነ ጥምቀትም አንድ ነው ። የንስሐ እንባ ግን ቢክድ ፣ ቢከፋ እንደ ጥምቀት ሁኖ ዳግም ይመልሰዋል ። አዳም በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ልጅነቱ ተጎሳቁሏል ። በኖኅ ዘመን በዚያ ታላቅ ቅጣት የሰው ልጅ ካለፈ በኋላ ሰው ሕንፃ ሥላሴ ነውና ማንም እንዳይጎዳው ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ፡- “የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና።” አለ ። ዘፍ. 9፡6። በደለኛም ቢሆን የእግዚአብሔር መልክ ጨርሶ አይጠፋም ። በኖኅ ዘመንም ስለዚህ መልክ መነገሩ ሰው ቢበድልም ጨርሶ መልኩ እንዳልጠፋ ማሳያ ነው ። ሐዋርያውም፡- “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤” ይላል ። ሮሜ. 3፡23። የእግዚአብሔር ክብር ጎደለ አለ እንጂ ሙሉ በሙሉ ጠፋ አላለም ።

አለቃ የተባለው ሰይጣን ነው ። አለቃ ነውና ይነዳል ፣ ያስጨንቃል ። ራሱ ንስሐ ሳይገባ ሰውን በኃጢአቱ ይከስሰዋል ። በሥሩ ብዙ አጋንንት አሉና ደግሞም የማይታዘዙ ሁሉ የእርሱ ተገዥዎች ናቸውና አለቃ ተብሏል ። ይህን አለቅነት የሰጠው ግን አለመታዘዝ ነው ። ሰይጣን አለቅነቱ በማይታዘዙት ልጆች ላይ ሲሆን የሚታዘዙትን ግን መንካትም መጠጋትም አይችልም ። ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ፡- “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤” ይላል ። ያዕ. 4፡7። ከዲያብሎስ የምንርቀው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ነው ። ወደ እግዚአብሔር የምንቀርበውም በመታዘዝ ነው ። ዘመን የማይለውጠው ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ንጹሕ መባ የተቀደሰው አኗኗር ነው ።

“በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው” ይላል ። በአየር ላይ ሥልጣን ያለው ማለት ምን ማለት ነው ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። መላእክት ተፈጥሮአቸው ከነፋስም ነውና ጠላታችን ረቂቅ መሆኑን ሊነግረን ነው ። ከረቂቅ ጠላት ጋር በግዙፍ መሣሪያ አንዋጋም ። መሣሪያው እንደ ጠላቱ ፣ እንደ ዐውዱ ነው ። በአየር ላይ ሥልጣን ያለው ማለት በዚህ ዓለም ይልቁንም በማይታዘዘው ትውልድ ላይ ሥልጣን ያለው ማለት ነው ። የተለያዩ ታላላቅ ተቋማት የዲያብሎስ የሚታዩ ሥራ አስፈጻሚዎቹ ናቸው ። እንደ ሆሊውድ ፣ እንደ ስለላ ተቋማት ያሉ የዲያብሎስ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ናቸው ። የክፋት ሥልጣኑ ዛሬም ይታያል ። ደግሞም በአየር ላይ ያሉ ነገሥታትን የሚመሩ ክፉ መናፍስት ፣ በምድር ላይ ጦርና ጦርነትን የሚፈበርኩ እኩይ አጋንንት አሉ ። የኤፌሶን ሰዎች በእነዚሀ አገዛዝ ሥር ወድቀው ነበረ ። ከዚህ ግዛት ክርስቶስ ነጻ ሲያወጣቸው በይገባኛል ክስ ሰይጣን መቆም አልቻለም ። ሰው የክርስቶስ መሆኑን ያውቃል ። ሰይጣን ሲረታ ዞር ይላል ፣ በሌላ ዘዴ ይመጣል እንጂ ድርቅ አይልም ።


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል አድርጎ መቃብርንና መግነዝን ወደ ታች ጥሎ ሁሉ እያየው ወደ ሰማይ ዐረገ ። በመለኮቱ ወረደ ፣ ዐረገ የማይባልለት በለበሰው ሥጋ ግን ወደ ላይ ዐረገ ። ወደ ላይ ሲያርግም በአየር ላይ ሥልጣን የነበረውን ጠላት ግዛቱን ሁሉ ደመሰሰበት ። ዛሬ ኃይለኛ ጠላት የለብንም ። ኃይለኛው ጠላት አለመታዘዛችን ብቻ ነው ። በአየር ላይ ያለው ጠላት ፈቃድ አለው ። ፈቃዱም የሰዎች መርከስ ነው ። የኤፌሶን ሰዎች በዚህ ጭቃ ውስጥ ሲመላለሱ ፣ ሲወጡና ሲገቡ ኖረዋል ። አሁን ግን ከሞት ድነው ፣ ለዓለም ሞተዋል ። ድሮ ለክርስቶስ ምውት ፣ ለዓለም ሕያው ነበሩ ፤ አሁን ግን ለክርስቶስ ሕያው ለዓለም ምውት ናቸው ።

የእግዚአብሔር ሰላም ከእናንተ ጋር ትሁን !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /29

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ