የትምህርቱ ርዕስ | ኑዛዜ

ጌታ ሆይ መኖሪያዬ መሥሪያ ቤቴ ነው አልንህ ፣ መሥሪያ ቤቱም እንዳትመጡብኝ ብሎ ዘጋ ። አዋቂዎች ስለ እኛ እየተመራመሩ ነው እንተኛ አልን ፣ እነርሱም ከአቅማችን በላይ ነው አሉን ። ሰንበትን ሽረን ትምህርት ቤቶችን ከፈትን ፣ ስድስት ቀን የሠራነው ሳይበቃን በሰባተኛውም ቀን እንሥራ አልን ፤ ትምህርት ቤቱም ፤ ለወራት ተዘጋ ። አንድ ሰንበትን ሽረን ሰባቱንም ቀን ሰንበት አደረግኸው ። ከምርጫ ግርግር ለመዳን ብለን ውጭ አገር ኮበለልን ፣ እዚያም ሞት ቀድሞ ጠበቀን ። ይህ መሬት የእኛ ነው ውጣልን ተባባልን ፣ እጃችሁ የእናንተ አይደለም አፋችሁን አትንኩ ተባልን ።ጎዳናው ማረፍ ፈልጎ ለመነህ ፣ አንተም ሰምተኸው ጸጥ አደረግከው ። ሰማዩን በተበከለ አየር ጋረድነው ፣ እኛን እቤት ስታስቀምጥ ውበቱ ፈክቶ ይኸው እየሳቀ ነው ። በሽታውን ከእንስሳ መጣብን አልን ፣ በልተውን ሳይሆን በልተናቸው መሆኑን ረሳን ። ጭጋጉ ያደጉ ከተሞችን ሸፍኖ ነበር ፣ ይኸው ከዋክብት ሊያበሩ መጡ ። አንድ በሽታ ሲመጣ የሚያጠቃው ጥቁሮቹን ነው አልን ፣ ሁሉም የሚያቃስትበትን በሽታ አመጣህ ። እግዚአብሔር አላመጣውም ሰዎች ለቀውብን ነው አልን ፣ ክፉዎችን በክፉዎች እንደምትቀጣ ረሳንህ ። እኛን አይነካንም ብለን ተመጻደቅን ፣ እምነታችን ከካዱት የተለየ እንዳልሆነ አሳየኸን ። ጸሎታችን ልዩ ነው አልንህ ፣ የወንድም ቀባሪዎችን ጸሎት መስማት መቼ ጀምረህ ነው ? ያልታመመውን ካልፈወስን እያልን ነገድን ፣ የታመመ ሲመጣ አዳራሹን ለቀን ወጣን ። እግዚኦ ብንል አልን ቅዱሶቹን አርክሰን ፣ አማኞቹን አውግዘን ፣ ንጹሖቹን ስም ሰጥተን የምትሰማን መስሎን ተታለልን ። አቤት ፣ አቤት እያልንህ እህል እንደብቃለን ። እየጸለይን ሰውን እንዘርፋለን ።

የእኔ ዘር ያልሆነ አልይ አልን ፣ እናትና ልጅን የማያስተያይ በሽታ ተማለን አወረድን ። ሰው ዘቅዝቀን ሰቀልን ፣ አየር የሚያሳጣ ጉድ መጣብን ። ያለ ፍርድ ሰውን እንደ እባብ ቀጥቅጠን ገደልን ፣ ፍርድ ቤት የሚያዘጋ የበሽታ ባለሥልጣን ከተፍ አለብን ። የገደልነውን ሬሳ አይነሣም ብለን ፎከርን ፣ ቀባሪ የሚያሳጣ ደዌ ጎተትን ። ጠግበን ነበረ ፣ የምንናገረውን መመጠን አቅቶን አፍስሰነው ነበረ ። በሰማይ ደመና እንጂ ዙፋን አልታየንም ነበር ። ጌታ ሆይ እንዴት ታዘብከን ።
በጣም ተገፋፋን ፣ አብሮ አደጎች ተካካድን ፣ በሚያራርቅ ሕመም አትነካኩ ተባልን ። ሥልጣኔአችንን የሚያቆመው ኃይል የለም ብለን ተናግረን ሳንጨርስ ጉንፋን አቆመን ። የአንዲት አገር በሽታ ነው ብለን ስንሳደብ የሁሉም አገር እንዲሆን አደረግን ። ተፋፍገው የሚኖሩ ድሆች በሽታ አያጣቸውም አልን ፣ ቤተ መንግሥት የሚኖሩ ሲጠቁ አየን ። ፈረንጅ አገር ሂዶ መምጣት ልዩ ነገር መሰለን ፣ ዛሬ የሚያሳስበን ሆነ ። ግደለኝ እያልንህ ስንለምንህ ከረምን ፣ ዛሬ አልኮል ለመግዛት ተሰለፍን ።
የዛሬውን ችግር ሳናይ የትላንቱን አደነቅን ፣ ይባስ እንደማያልቅ አስተማርከን ። ሁሉም ነገር አንድ ቀን ቀጥ እንደሚል ዋዜማውን አሳየኸን ። ቃልህን ለመስማት ኮራን ፣ የተማርኩት በቂ ነው አልን ፤ ስብከተ ወንጌል የለም ተባልን ። ቅዳሴ ለማስቀደስ ተፈተንን በየቤታችሁ ሁኑ ተባልን ። ሰው ሰብስቦ ማስተማር ሰለቸኝ አልን ፣ ባዶ ቤት መስበክ ጀመርን ። ሰው ሰላም እንዳይለን እንሸሽ ነበር ፣ በአዋጅ አትጨባበጡ ተባልን ። የጠላነው መነካካት ዛሬ ሕግ ሆኖ መጣ ። መተቃቀፍ አስጠላን ፣ የሚተቃቀፉትን ፖሊስ ይለይ ተባልን ። ጨረቃ ላይ ደርሰናል ብለን ስንኮራ ገና እጃችሁን ታጠቡ የሚል ምክር እንሰማለን ። ጠላት አለብኝ እያልን ስንለፈልፍ በእጃችሁ ዓይናችሁን እትንኩ ፣ እጃችሁ ነው ጠላታችሁ ተባልን ።
ለትዳራችን የሚሆን ጊዜ አጥተን ተረሳስተን ነበር ፣ አሁን ሃያ አራት ሰዓት አብረን ስንቀመጥ ተፋጠጥን ። ሥራችንን ጠልተን ጥቁር ሰኞ እንል ነበር ፣ ዛሬ መሥሪያ ቤቱ ናፈቀን ። ሰዓቱ ሳይሞላ ከሥራ ወጥተን ነበር ፣ ዛሬ ትርፍ ሰዓት መሥራት አማረን ። ከሠራነው ላይ አሥራት ለመስጠት ተፈትነን ነበር ፣ ዛሬ ግን ያስቀመጥነውን ያለ ደስታ እንበላለን ።
ጌታ ሆይ ጣትህን ብትዘረጋ እንዲህ የሟሸሽን ክንድህን ብትዘረጋ የት ልንገባ ነው ? ብናኝ ልጆችህን ይቅር በለን ። አክብረኸን ማረን እንጂ አክብረኸን እንዳትጣላን ። እኛ ሰው ፣ አንተ አምላክ ነህ ። እባክሀ ይቅር በለን ። በመልካም አስበን ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ይሁን ። ከምታልቀዋ ከዛሬዋ ቀን እስከማይፈጸም ዘመን ። ከደካማው ልባችን እስከ ጸናው ሰማይ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 19
መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም