የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ኒቆዲሞስ፤ የማታው ተማሪ

       የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8 2008 ..
በዓለም ላይ ነጻ ፍቅር ማግኘት ከባድ መስሎ ይሰማናል፡፡ ዓለሙ የእከክልኝ ልከክልህ መድረክ እንደሆነ እንናገራለን፡፡ ከሰው ልጅም ንጹሕ ፍቅርን አጣሁ የሚል የብሶት ውዝዋዜ አለብን፡፡ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ነው እያልን ሁሉም ሰው የገዛ ጥላውን እንዲጠራጠር ማስጠንቀቂያ እናዘንባለን፡፡ ፍቅር የለም፣ ፍቅር አልቋል፣ ዋናው ገንዘብ ነው፣ እንደ ምንም ባለጠጋ መሆን ብቻ ያዋጣል፣ ከዚያ በኋላ ሁሉም ይመጣል እንላለን፡፡ የምናየው ግን የተለዩንን እንጂ አብረውን ያሉትን አይደለም፡፡ ዋጋ የምንሰጠው ለጠሉን ሰዎችና ለጥላቻቸው እንጂ ለወዳጆቻችንና ለፍቅራቸው አይደለም፡፡ የሚጠሉን ብዙ ቢሆኑ እንኳ የሚወዱን አሉ፡፡ በነጻ ያፈቀሩን ወላጆቻችንን፣ ጉልበታቸውንና መልካቸውን አርግፈው ያሳደጉንን አባት እናቶቻችንን ለማየት መቼ ይሆን ዓይናችን የሚገለጠው? አዲስ ፍቅር ስንፈልግ የተገኘውን ፍቅር የምናጣጥለው እስከ መቼ ይሆን? ፍቅር ይቀዘቅዛል እንጂ ይጠፋል እንዳልተባለ ማሰብ አለብን (ማቴ. 2412)፡፡ ዛሬም አግብተን ወልደን የሚያስቡልን፡– ‹‹ዳር ዳር ሂዱ መኪናው በዝቷል፣ ታክሲው ይንቀዠቀዣል፤ ገላጋይ ይሞታልና ከጠብ መሐል አትግቡ›› የሚሉን ወላጆቻችን እያሉ ነጻ ፍቅር የለም ማለት ይከብዳል፡፡ ይልቁንም የእናትና የልጅን ፍቅር ስናየው ከማኅፀን ሲወጣ በስለት ይለያሉ፣ ኋላም በሞት ስለት ይቆራረጣሉ፡፡ 

 ወላጆች በልጆች እንዲደሰቱ ልጆች በወላጆቻቸው እንዲኰሩ በተፈጥሮ ጸጋ ተለቋል፡፡ ወላጆች በልጆቻቸው የሚደሰቱት እነርሱን የሚመስል ሰው፣ ተንቀሳቃሽ ፎቶ ስለተገኘ፣ ነገም አለሁ ብለው ነገን በልጆቻቸው ስለወረሱ ሊሆን ይችላል፡፡ ልጆችም በወላጆቻቸው የሚኰሩት እንደ እነርሱ ወላጆች በዓለም ላይ ምሁር፣ ባለሥልጣን፣ ኃያል፣ ባለጠጋ ያለ ስለማይመስላቸው ነው፡፡ 
 በአንድ ልቅሶ ላይ አንድ ባለሥልጣን ልቅሶ ሊደርሱ መጥተው ሕጻኑን ልጅ ያጫውቱታል፡፡ ታዲያ ከሕፃኑ ጋር ሲጣሉ ሕጻኑ፡– “ቆይ ለአባቴ እነግርልሃለሁአላቸው፡፡ ባለሥልጣን የአባቱም አለቃ እንደሆነ ልጁ አያውቅም፡፡ ከአባቱ በላይ ትልቅ እንዳለ አይቀበልም፡፡ እንዲህ አድርጎ ያከበረውን ልጁን አባት ቢወደው ትክክል ነው!! አንዲት ሕፃን ልጅን ሚሚ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አገኛለሁ ምን አድርጉላት ልበላቸው ብላት፡– “ረጅም ቀሚስ ግዛልኝ በለውብለኛለች፡፡ ያደገው ሰው ከጠቅላይ ሚኒስትር አንድ ጨርቅ አይለምንም፡፡ አንድ ክፍለ አገር ገምሶ እንዲሰጠው ነው የሚለምነው፡፡ ልብስ ቢቸግረውም ከአንድ መሪ ይህችን መቀበል አይፈልግም፡፡ ከቢልጌት የጐደለውን የታክሲ መሳፈሪያ የሚጠይቅ ጎበዝ አለ ወይ? ልጆቹ ግን የሚያስፈልጋቸውን ብቻ ይጠይቃሉ እንጂ የስግብግብነት ልመና የላቸውም፡፡ ልጅ በራሱ ዓለም ነው፡፡ ወላጆች በልጆች መደሰታቸው፣ ልጆች በወላጆች መኰራታቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ 
 በዚህ ዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በእንግድነት የተቀበሉን ለትልቁ ቤተሰብ ለዓለም አቀፋዊው የሰው ልጆች ማኅበር ወኪል ሆነው የቀላቀሉን፣ ለአካለ መጠን እስክንበቃ የወሰኑልን፣ የመጀመሪያ ስጦታዎቻችን የሆኑልን፣ የመጀመሪያዎች ጓደኞች፣ መጋቢዎች፣ አገልጋዮች በመሆን ዓለምን ያላመዱን ወላጆቻችን ናቸው፡፡ በሰለጠነው ዓለም የወላጆች ቀን ይከበራል፤ የወላጆች ውለታ ግን በዓመት አንድ ጊዜ ሳይሆን በየዕለቱ ሊታወሰና ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡ 
 ሊወደድ የማይችለውን ያንን እርጥብ ሕፃን የወደዱ፣ እንቅልፍ አጥተው እስረኛ ሆነውለት ስለ ልጁ መጐዳትን ሁሉ እንደ ጥቅም ቆጥረው ያሳደጉ፣ ሁልጊዜ እርዱኝ የሚለውን ልጅ አብልተው፣ አጥበው፣ አስተኝተው፣ ቆሻሻውን አጽድተው፣ ሰው እንዲስመው አድርገው አሳምረው ያሰናዱ የነበሩእነዚያ ወላጆች ሊወደዱና ሊከበሩ ይገባቸዋል፡፡ ድሆችን ብንወድ በጸጋ ሊሆን ይችላል፣ ወላጆቻችንን መውደድ ግን የውለታቸው ምላሽ ነው፡፡ በእውነት በዓለም ላይ ፍቅርን ዘርቶ ፍቅርን ማጨድ ሕግ ቢሆንም ወላጆች ግን ይህን አላገኙትም፡፡ ለዚህ ነው፡– ‹‹የእናትና የልጅ ፍቅር እንደ ጅረት ውሃ ከላይ ወደ ታች እንጂ ከታች ወደ ላይ አይፈስስም›› የሚባለው፡፡ 
 እግዚአብሔር አምላክ በቤቱና በመንግሥቱ የተቀበለን በልጅ ወግ ነው፡፡ እግዚአብሔር በመልኩ የፈጠረን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ከውድቀት አንሥቶ እንደገና ያቀፈን አባታችን ነው፡፡ በምድር ላይ ያሉ አባቶች የእርሱ አባትነት ምሳሌ ናቸው፡፡  እውነተኛው የፍጥረት አባት ግን እግዚአብሔር ነው፡፡  ከወላጆቻችን ጋር ለመገናኘት ዕውቀት መስፈርት ቢሆን ኖሮ ምንም የማያውቀው ራሱንም የማይረዳው ሕጻን ገና  ከማኅፀን ሲወጣ ተጥሎ ይቀር ነበር፡፡  መስፈርቱ ባለጠግነት ቢሆን ኖሮ ዕርቃኑን የተወለደ ልጅ ተረስቶ ይቀር ነበር፡፡  መስፈርቱ ግን ነጻ ፍቅር ብቻ ነው፡፡  የእግዚአብሔር ቤት ድርጅት ቢሆን ሙያችን በተጠየቀ ነበር፡፡  ቤታችን በመሆኑ ግን በፍቅር መስፈርት ይኸው አለን፡፡  አላዋቂ ድሀ ብንሆንም የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንችላለን፡፡  ልጅነት መወለድ እንጅ ቁሳዊ መስፈርት የለውም፡፡  ብዙ ባልንጀሮችን ለውጠናል፡፡ ወላጆቻችንን ግን አለወጥንም፡፡ እግዚአብሔርም አባታችን ነውና አይለወጥም፡፡ ወላጆቻችን ወላጅ እንጂ ፈጣሪ አይደሉም፣ እግዚአብሔር ግን ፈጣሪ አባታችን ነውና ከወላጆቻችን ይበልጣል፡፡ የገፋነውን የወላጆቻችንን ቤት ሳናፍር  ተመልሰንበታል፡፡  ጀርባችንን የሰጠነው ጌታም ወደ እነርሱ ስንመለስ አያሳፍረንም፡፡  ምንም ተበሳጭተን አባቴ አይደለም ብለን የሥጋ አባታችንን ብንክድ አባት መሆኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ልጅነት የደምና የሥጋ  ቋጠሮ በመሆኑ በፍላጎት አይፈታምና፡፡  እግዚአብሔርም በማይፈታ  ቋጠሮ ከእኛ ሊሆን ስለወደደ ራሱን የፍቅር እስረኛ አድርጎ አባት ሆኖልናል፡፡  ይህን ሁሉ ሐቅ የሚተረከው በኒቆዲሞስ እሑድ በዐቢይ ፆም ሰባተኛው ሰንበት ነው፡፡ የቅዱስ ያሬድ የመዝሙሩ ርእስሖረ ኅቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስስለሚል ዕለቱ ኒቆዲሞስ ተብሏል፡፡ የዕለቱ የወንጌል ምንባብ ዮሐ. 3÷ 1- 2 ነው፡፡ 
ከአዲስ ኪዳን ዋና ዋና ትምህርቶች አንዱ የሆነው ዳግም ልደት የተገለጠው ለኒቆዲሞስ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ከአይሁድ ሊቃውንት አንዱ፣ የሸንጎ አማካሪ፣ የክርስቶስ የማታ ተማሪ፣ በዕለተ ዓርብ በመከራው ቀን የግልጥ መስካሪ ነበር፡፡ ኒቆዲሞስ የተከበረ ሰው ቢሆንም በሕይወቱ ግን ዕረፍት አልነበረውም፡፡ ያም ነው በሌሊት እንዲገሰግስ ያደረገው፡፡ የነፍሱን ጥያቄ በማዳለል ማለፍ ያልቻለ፣ ፍጥረት ሁሉ አሸልቦ እርሱ <
span style=”font-family: ‘Visual Geez Unicode’; font-size: 14pt;”>ግን መልስ ፍለጋ ቤቱን ሰብሮ የወጣ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ለቀን ተማሪዎቹ ያልነገረውን ለሌሊት ተማሪ ለኒቆዲሞስ ነገረው፡፡ ስለ ዳግም ልደት ገለጠለት፡፡  ይህችን ዓለም ባንወለድ ኖሮ አናያትም ነበር፣ ያችኛዋንም ዓለም ካልተወለድን አናያትም፡፡ ዓለም የሚወረሰው በልደት ነውና፡፡ ይህችን ቁሳዊ ዓለም ለማየት በሥጋ መወለድ ነበረብን፤ መንፈሳዊውን ዓለም ለማየትም በመንፈስ መወለድ አለብን፡፡ ስንወለድ ልጅ ብቻ ሳይሆን የተወለድንበት አገር ዜጋ የመላው የሰው ዘር አባል ሆነናል፡፡ እንዲሁም በቃሉ ስንወለድ ልጅ ብቻ ሳይሆን በሰማይ ዜጋ፣ በዓለም ዓቀፋዊቷ /     እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት/ በተባለችው ኅብረትም አባል ሆነናል፡፡ ይህንን ምሥጢር ለኒቆዲሞስ ገለጠለት፡፡ የብዙ ሰው ችግሩ ያለ ማረፍ ምክንያት በሌሊት የሚያዞረው ምሥጢር አለመወለድ፣ በነፍስ ስደተኛ መሆን ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ጥያቄው እንቅልፍ ቢነሣው ወግ ነው፡፡ ጌታ ግን እንቅልፍ አጥቶ ማገልገሉ ትጋቱን ለዛሬ አገልጋዮች ያሳየናል፡፡
 ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ በሌሊት ይመጣ የነበረው ሌላው ምክንያት አይሁድን መፍራት ነው፡፡ ከተነቀፈው ጌታ ጋር ቢታይ በአገር በመንደሩ ስሜ ይጠፋል ብሎ አስቦ ነው፡፡ እንዲህ ያለውም ጭንቀት ካለመወለድ የሚመጣ ነው፡፡ወንድ ወደሽ ጢሙን ጠልተሽእንደሚባለው ክርስቶስን ወዶ ነቀፋን ጠልቶ አይሆንም ወንድን ያለጢም፣ ክርስቶስን ያለነቀፋ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ጌታ ግን ይህንን ፍርሃቱን አልነቀፈውም፡፡ ጌታ ሊፈውስ የሚፈልገው የችግሩን ምንጭ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ አለመወለድ ነው፣ ወራጁ ሰውን መፍራት ነው፡፡ የፈራነውን ሰው አምልከነዋል ማለት ነው፡፡ ፍርሃትና ረዓድ አምልኮ ሲሆን ይህም ለእግዚአብሔር ብቻ የሚሰጥ ነው፡፡ የሚያስፈራውን ጌታ ካገኘን ፍርሃት ይለቀናል፡፡ 
 ኒቆዲሞስ ወደ ጌታ ሲመጣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር እንዳለ የሚያሳምኑ ተአምራቶችን ዓይቶ ነው፡፡ ክርስቶስ ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ አላወቀም፡፡ ጌታ ለዚህ አዋቂ ዕውቀትን ይዞ ሕይወትን ላጣው፣ ሰው ችግሩን ለማይረዳለት ኒቆዲሞስ እንዲህ አለው፡ እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም(ዮሐ.33)፡፡
 የእግዚአብሔር መንግሥት በልጅነት ክብር የምትወረስ ናት፡፡ በቃሉ፣ በመንፈሱ፣ በጥምቀት መወለድ ያስፈልጋል፡፡ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ መወለድ ማለት ይህ ነው፡፡ ካልተወለድን እግዚአብሔርን በፍቅር ድፍረት አባ አባት ብለን መጥራት አይሆንልንም፡፡ የእግዚአብሔር ደጅ በቅርብ አይገኝም እንደሚሉት የኔ ቢጤዎች ማሰባችን አይቀርም፡
በመንግሥተ ሰማይ ምስክር አብጁ
በቅርብ አይገኝም የፈጣሪ ደጁ
እያሉ ይለምናሉ፡፡ ምስክሩ ያው የኔቢጤው ነው፡፡ መቼም ለድሀ ቸርነት ማድረግ ለእግዚአብሔር ማበደር ነው ተብሏል፡፡ እግዚአብሔር ግን የቅርብ አባታችን ነው፡ ‹‹አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና›› ተብሎ ተጽፏል(ሮሜ. 815)፡፡ ኒቆዲሞስ የማታ ተማሪ ቢሆንም የግልጥ ተማሪዎች የነበሩት ደቀ መዛሙርት ጌታን ጥለው በሸሹበት ቀን ጌታን ከመስቀል አውርዶ ገንዞ ቀብሯል (ዮሐ.1939)፡፡ ሁሉ በሚገኝበት ቀን ሳይሆን ሁሉ በሚሸሽበት ቀን ታማኝ ሆኖ ተገኘ፡፡ በመከራ በፈተና ያለፉ የማታ ተማሪዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር የሚያስተምረን እርሱ በሚመርጠው መንገድ እንደሆነ ተጽፏል (መዝ. 2412)፡፡ በክፉ ቀን ፀንተን ለመቆም ክፉውን ቀን ማወቅ ይረዳል፡፡ መከራን ያዩ በመከራችን አይደነቁም፡፡ በመልካም ቀን የዘመሩና የሰበኩ በጠፉበት ቀን የማታ ተማሪዎች በአደባባይ ይገኛሉ፡፡ የግልጾቹ ህቡዕ ሲሆኑ ኅቡዓን ይገለጣሉ፡፡ እኛስ የማታ ተማሪዎች፣ የክፉ ቀን ምስክሮች እንሆን ይሆንን? እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ ዛሬ ለእግዚአብሔር የተበቀልንለት እየመሰለን እያሳደድን እያስራብን ነው፡፡ ስደትና ረሀብ ሲመጣስ እኛም ፀንተን እንቆም ይሆን? መስቀል የሚሸከም ክርስትና ሳይሆን መስቀል የሚያሸክም ክርስትና ውስጥ ነንና እግዚአብሔር ያስበን! መስቀልን ሲሸከሙትና ሲያሸክሙት ልዩነት አለውና ልቡና ይስጠን! 
በመከራና በፈተና ውስጥ እያለፍን ከሆነ የማታ ተማሪዎች ነንና ደስ ይበለን፡፡ በሕይወት ውስጥ እያሳለፈ የሚያስተምር ብቸኛው መምህር ክርስቶስ ነውና እንበርታ!  ከእርሱ ጋር ገደሉ ሜዳ ነው፤ ሲደክመን ይሸከመናልና!  
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ