እግዚአብሔር አምላክ ከአሌፍ እስከ ታው ያሉትን ፊደላት በጸፍጸፈ ሰማይ /በሰማይ ገበታ/ ላይ ለሄኖክ እንደ ገለጠለት ቤተ ክርስቲያን ታምናለች ። እግዚአብሔር አምላክ ሕግጋቱንም በሙሴ በኩል በድንጋይ ሰሌዳ ወይም በጽላት ላይ ጽፎ ለእስራኤል እንደሰጠ ኦሪት ትነግረናለች ። የክርስትና ሃይማኖት መጽሐፋዊ ሃይማኖት ነው ስንልም ክብር ይሰማናል ። ሃይማኖታችንም በብሉይና በአዲስ ኪዳን የተመሠረተ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ አሳቡን በሰው ቋንቋ ማስተላለፉ ሰው እንዲያውቀውና እንዲረዳው ስለፈለገ ነው ። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ ከሰማያዊ አባት ለምድራውያን ልጆች የተጻፈ የፍቅር ደብዳቤ ነው ይባላል ። ይህ የሚያሳየን እግዚአብሔር ሕጉንም ፣ ፍቅሩንም መግለጥ የፈለገው በጽሑፍ ነው ። “በቃል ያለ ይረሳል ፣ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” ይባላል ። ትልቅ ውርስ ካለ መጽሐፍ ነው ። ተንቀሳቃሽ ሐኪም ቤት ፣ ተንቀሳቃሽ ሐውልት ፣ ተንቀሳቃሽ ሀብት መጽሐፍ ነው ። መጽሐፍ በእያንዳንዱ ቤት ሲገባ ፈውስን ይሰጣል ፣ ዘመናትን አሻግሮ ትላንትን ፣ ተሻግሮ ነገን ያሳያል ፤ ሰዎች ብዙ ሀብት ጥለው ሲሰደዱ መጽሐፍ ቅዱስን ግን ጦር ሜዳ ይዘው ሲሄዱ ይታያሉ ። መጽሐፍ ወዳጅ ነው ። እብለትና ኩሸት የሌለበት ወዳጅ ፣ ቃሉን የማይለውጥ ጓደኛ ፣ በር ዘግቶ የሚወቅሰን አበ ነፍስ ነው ።
እግዚአብሔር ሥነ ጽሑፍን ያከብራል ። በቋሚነትም አሳቡን በመጽሐፍ ይገልጣልና የሰው ልጆች መጽሐፍ ምን አለ ? ማለት አለባቸው ። የእግዚአብሔር ልጆች አንባቢዎች ናቸው ። ለዛሬ የሚሆን እንጀራን ፣ ለነገ የሚሆን ስንቅን ፣ ለዘመናት የሚሆን ትንቢትን ከመጽሐፍ ያስሳሉ ። መጽሐፍን በመመልከት የዘመኑን መልክ ይለያሉ ። ኮምፓስ የሌለው የመርከብ ካፒቴን ፣ ካርታ የሌለው መንገደኛ እንደሚጠፉ የማያነብ ሰውም እንደዚሁ ነው ። ማዕድን ቆፍረው ቢያገኙት ያጋድላል ፣ መጽሐፍ ግን ማዕድን ሳለ ያፋቅራል ። ምግብ ቢመገቡት ቁንጣን ይሆናል ፣ መጽሐፍ ግን ልብን ያሰፋል ። ማንበብ የተለያየ ጥቅም አለው ። አለማንበብም የተለያየ ጉዳት አለው ። ለማንበብ የሚያስፈልጉ ነገሮችም አሉ ።
የንባብ ጥቅም አያሌ ነው ። የመጀመሪያው ከሰዎች ጋር በእኩያነት ለመነጋገር ንባብ አስፈላጊ ነው ። የማያነብ ሰው ፀጥታን ለመሻር ሐሜት ውስጥ ይገባል ። ንግግሩም ፍሬ ስለሌለው ይሰለቻል ። ጆሮ ጠገብ በመሆኑ አሉታ እንጂ እርግጠኛ እውቀት የለውም ። ንባብ ሁለተኛው ጥቅም አእምሮን ያነቃል ። አእምሮ ያለ እውቀት እየዛገና እየሞተ ይመጣል ። ከማወቂያ መንገዶች ቀዳሚው ንባብ ነው ። የማያነብ ሰው ወደ መርሳት ውስጥ ይገባል ። ሦስተኛው የንባብ ጥቅም ውስጣዊ ጥንካሬን ለማግኘት ወሳኝ ነው ። ቀኑ የራሱ የሆነ ፈተና አለው ። የቀኑን ትግል የምናሸንፈው በንባብ በምናገኘው እውቀት ነው ። የቀኑ ፈተና ሲመጣ ካነበብን ንባቡ ላይ ያርፋል ፣ ካላነበብን እኛ ላይ ያርፋል ። አራተኛው የንባብ ጥቅም ለማስታወስ ይረዳል ። የሚያነቡ ሰዎች አእምሮአቸው ሥራ ላይ ነውና ያስታውሳሉ ። ማስታወስ ከሚያስከብርና ከሚያስደንቅ ነገሮች አንዱ ነው ። ካላስታወስን ንብረታችንን እንረሳለን ። ልጃቸውን ረስተው የሚገቡ ሰዎችም አሉ ። ጡንቻ ካልሠሩበት እንደሚረግብ አእምሮም ካላነበቡበት እየረገበ ይመጣል ። አምስተኛው የንባብ ጥቅም የሚጽፉትን ለማግኘት ይረዳል ። የሚሰማ ሰው መናገር ፣ የሚያነብ ሰው መጻፍ ይችላሉ ። ስድስተኛ ፀሐፊዎችን ለማብዛት ንባብ አስፈላጊ ነው ። ጡት ሕፃኑ እስከጠባ ድረስ ቀጣይ ይሆናል ፣ ሲያቆም ይነጥፋል ፤ ካነበብን ፀሐፊያን ይጽፋሉ ። ካላነበብን ፀሐፍያን ይጠፋሉ ፣ ምድር በጨለማ ትዋጣለች ። የመጽሐፍ ገጾችን የማይገልጡ ጣቶች የጠመንጃ ቃታ ይስባሉ ። ሰባተኛው ቋንቋን ለማሳደግ ንባብ በጣም ይረዳል ። ቋንቋ እንደ ሰው ነው ። ከልደት እስከ ሞት ደረጃዎች አሉት ። ቋንቋችንን ለማሳደግ ንባብ አስፈላጊያችን ነው ። ስምንተኛ ዓይንን ለማሠራት ንባብ ወሳኝ ነው ። እንዲያነብ የተፈጠረ ዓይን ማንበብ አለበት ። ልብስና ምግብ ቤት ብቻ የሚያይ ዓይን ለነፍስ የሚሆነውን ስንቅ መጽሐፍን አያይም ። ምግብ ቤት እየሄድን መጻሕፍት ቤት አለመሄድ እለ ከርሦሙ አምላኮሙ – ሆዳቸው አምላካቸው የተባለው ቃል እንዲፈጸምብን ያደርጋል ።
ዘጠነኛ መጽሐፍ የማንበብ ጥቅም ተጠያቂ ለመሆን ነው ። እገሌ ያነበበ ነው ጠይቁት ይባላል ። ዐሥረኛ ለልጆች አርአያ ለመሆን ማንበብ ወሳኝ ነው ። የሚያነብ ወላጅ የሚያነቡ ልጆች ይኖሩታል ። ንባብ ካለ ሥራ ፈትነት በቤተሰብ ውስጥ ስለማይኖር የነገር እሳት አይሞቁም ።
ለማንበብ የሚረዳ ነገር ምንድነው ? ብለን ከጠየቅን የመጀመሪያው መጻሕፍትን መለየት ነው ። መጽሐፍ ጓደኛ ነው ብለናል ። ክፉ ጓደኛ እንዳለ ክፉ ጽሑፍም አለ ። የምናነበው ምንድነው ማለት ያስፈልጋል ። የሚያነቡ ሰዎችን መጠየቅ መልካም ነው ። ሰዓታችንን መመደብ አስፈላጊ ነው ። ከእንቅልፍ እንደ ተነሣን ሠላሳ ደቂቃ ያህል ብናነብ ፣ ከምሳ ቀጥሎ አሥራ አምስት ደቂቃ ብናነብ በጣም ጠቃሚ ነው ። ንባብ ጽሞናና መረጋጋት ይፈልጋል ። ታክሲ ውስጥ ማንበብም መንገዱን ሳናውቀው እንዲያልቅ ደግሞም እንድናተርፍበት ያደርጋል ። ያነበብነውን ማካፈል እንዳንረሳው ያደርገናል ። ያነበብነውን ለመተግበር መሞከርም አስፈላጊ ነው ። በግምትና በአሉታ ከማውራት ንባብ ይታደጋል ።
የንባብ እንቅፋት አለ ፤ በዝግ ልብ ማንበብ ፣ ለትችት ማንበብ ፣ አንብቤዋለሁ ብሎ ለማውራት ለጉራ ማንበብ ፣ ለጠቅላላ እውቀት ማንበብ ፣ ለክስ ማንበብ ያለ ማንበብን ያህል ንባብን የሚጎዳ ነው ። በእውነት መጽሐፍ በሃምሳ ፐርሰንት ቅናሽ ሲሸጥ ስንሰማ ውርደት ላይ መሆናችንን ያሳያል ። ኪሎ ሥጋ እስከ አንድ ሺህ ብር በሚበላበት በዚህ ጊዜ የሃምሳ ብር መጽሐፍ ለመግዛት መሰሰት ራስ ላይ መተኮስ ነው ። የምናየው ችግር ያለማንበብ ችግር ነው ። የማንበብም ችግር ነው ። ደጉን ያለ ማንበብና ክፉን የማንበብ ውጤት እዚህ አረንቋ ውስጥ ከትቶናል ። እየሄድን እየመሰለን የምንዋጥበት የማጥ መንገድ እንዲያበቃ እናንብብ ። ዓይን ይዘን ፣ ማንበብና መጻፍን ተምረን አለማንበብ ተፈጥሮንና ትምህርትን ማባከን ነው ።
ጌታ ሆይ አለማንበብ ለተባለ ሞት እንዳልተኛ ዓይኖቼን ለንባብ አብራ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም.
እውነት 11
ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ !