የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አለሁ !!!

ባሕረ ጥበባት በሆንከው ፣ ሁሉን እንደ መላህ በምታኖረው ባንተ አለሁ ። ደዌያትን በቃልህ ፣ አጋንንትን በሥልጣንህ በምትሸኘው ፤ ትላንትን ለመካስ ፣ ዛሬን ለማድረስ ፣ ነገን ለማውረስ አቅም ባለህ ባንተ አለሁ ። የሞትን አዋጅ በሕይወት ፣ የስቅላትን ደብዳቤ በሹመት በምትለውጠው ባንተ በመፍቀሬ ሰብእ/በሰው ወዳዱ ጌታ አለሁ ። የነበረው የነበረ እስከማይመስል ደብዛው ጠፍቷል ፣ ያለው የማያልፍ ይመስል ይሸልላል ። የሚታየው የማይታይ ሲሆን ፣ አፈር የላሰው እንጀራ ሲያገኝ ፣ ተስፋ ያጣው ቀን ሲወጣለት ባንተ ደስ ይለኛል ። እኔ ግን ባንተ አለሁ !

ይሻላሉ የሚባሉት ሲበላሹ ፣ አይረቡም የተባሉት ለተጠቃው ጠበቃ ሲሆኑ ፤ የጠሩኝ ሲመልሱኝ ፣ የመረጡኝ ሲከሱኝ ፣ አንተ ግን ንጋትህ ምሽት የሌለበት ብርሃን ነህና ባንተ አለሁ ። ራሴን በኃጢአት ጦር ወግቼ እንደማቆስለው እንደ እኔ አይደለህም ፣ ላይ ሳስቀምጣቸው ታች እንደሚወርዱት እንደ ሰዎች አይደለህም ። ዝናብ እንደሌላቸው ደመናዎች ከፍ እንዳሉት ሰዎች አይደለህም ። ኮከብ ክብር ተቀብለው የሲኦል ጨዋታ እንደሚጫወቱትም አይደለህም ። አንተ እንደ ራስህ ነህና እኔ ባንተ አለሁ ።

ውስጡ በብቸኝነት ፣ ዙሪያው በሌጣነት ፣ ጀርባው በታሪክ የለሽነት ፣ ፊት ለፊቱ በጭጋግ ለተያዘበት አለኝታ አሳዳሪው በምትሆን ባንተ አለሁ ። ፍጹም ልጅህ ልታደርገኝ ፣ ፍጹም ሰው በሆንከው ፣ ሰማያዊ ልታሰኘኝ በምድራዊው እጅ በተጠመቅኸው ባንተ አለሁ ። መሰላሉ ቢሰበር ባንተ እወጣለሁ ፣ ደረጃው ቢረዝም ባንተ ራስ እሆናለሁ ። ቀኔ ላይ ምሽት ፣ ጀምበሬ ላይ ውድቅት ሌሊት ቢታወጅ እኔ ግን ባንተ አለሁ ። ምልክት ስሻ መኖሬ ከንቱ ነው ። ድንግል በድንግልና መፅነሷ ፣ ዘር ምክንያት ሳይሆናት አንተን መውለድዋ ትልቅ ምልክት ነው ። እንዴት ይሆናል ብዬ አልጨነቅም ፣ አንተ ደመና አዙረህ ማዝነብ ፣ በጠራራ ፀሐይ ጠል መስጠት ትችላለህ ።

አንተን አይመጥንህም ፣ ይህን አልነግርህም ብዬ ዳር ዳሩን ስዞር ነበር ። ለምታውቀኝ ላንተ መሸፋፈን ፣ ልቤን ለምታነበው ላንተ ለመንፈስ ቅዱስ አለመናገር የፍጡርነቴ ድካም ነውና ሁሉን እነግርሃለሁ ። ቃል የገባውን በሚያጥፈው ዓለም ውስጥ ፣ የተመኘሁትን የምትፈጽም አንተ አለኸኝ ። እኔ ባንተ አለሁ ። ሞት የተፈረደበት የሚኖርብህ ሕይወት ፣ ኃይል የሌለው የሚሰለጥንብህ ድል አንተ ነህ ። እኔ ባንተ አለሁ ። አንተ ባትኖር አልኖርም ነበር ። ላንተም በማይቆጠር ምክንያት ክብር ምስጋና ይሁን አሜን ። ለቀዳማዊነትህ መነሻ የለህም ብሎ የሚያምን አሜን ይበል !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ