የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አልለውም

አንቱ የምለውን ሰውዬ ፣
አንተ አልለውም አቃልዬ ፤
ዓባይ ይጎድላል እንኳን ሰው ፣
ጊዜ ሲያዋርደው ።

የቅጥር ተሳዳቢዎች አሉ ። ከተከፈላቸው ለሰው ጠብ ተሳዳቢ ይሆናሉ ። አልቃሽ በሚቀጠርበት ዓለም ፣ ዘፋኝ በሚጠራበት ምድር የሚሳደብም ይገዛል ። ይህች ምድር ብዕራቸውን ያረከሱ ፣ አንደበታቸውን ያጎደፉ ፣ በሐሰት ምስክር ሃይማኖታቸውን የጣሉ ፣ ሌላውን ዝቅ በማድረግ እንጀራ ለመብላት የሚጥሩ ሰዎችን ተሸክማለች ። እገሌ ሞተ ሲሉን ከማዘን ይልቅ ቀብሩ የት ነው ? ብለን የምንጠይቀው የአዩኝ አላዩኝ ኑሮ ስለምንጫወት ነው ። የወደቀን ሰው ለማቃለል የምንሽቀዳደመው ቀድሞም ያከበርነው በሐሰት ላይ ተመሥርተን ነው ። የምናከብረው ውብ ፀጉርን ከሆነ ፀጉሩ ላሽ ሲበላው ፣ በራነት ሲያጠቃው ሰውዬውን እንጠላዋለን ። የምናከብረው ለገንዘብ አለመሰሰቱን ከሆነ የሚሰጠው ያጣ ቀን እንርቀዋለን ። የምናከብረው ቁመናውን ከሆነ እጅ እግሩ ታስሮ ቤት ሲውል ገሸሽ እንለዋለን ። የምናከብረው ተጫዋችነቱን ከሆነ ዱዳ የሆነ ቀን እንጸየፈዋለን ። የምናከብረው ሥልጣኑን ከሆነ የወረደ ቀን እናዋርደዋለን ። የምናከብረው የእርሱ ጎሣዎች እየገዙ ነው ብለን ከሆነ ገለል ሲሉ “ምን ያመጣል ?” ብለን እንተርትበታለን ። የምናከብረው ሃይማኖቱን ከሆነ ሃይማኖቱን የለወጠ ቀን ድሮስ ? ብለን ካከበርነው በላይ እናዋርደዋለን ። የምናከብረው ሥነ ምግባሩን ከሆነ የተሳሳተ ቀን ከሳሽ ወቃሽ እንሆናለን ። የምናከብረው ጥሩ ሰላምታውን ከሆነ ቀዝቀዝ ያለብን ቀን ጠላት እናደርገዋለን ።

የምናከብረው ሙያውን ከሆነ ከሙያው ገለል ያለ ቀን ስልካችንን እናጠፋበታለን ። የምናከብረው ልጅነቱን ከሆነ ሲያድግ እንጠላዋለን ። የምናከብረው ሽምግልናን ከሆነ ወጣቶችን በክፉ ዓይን እናያለን ። የምናከብረው ጾታን ከሆነ እግዚአብሔር በሰጣቸው ነገር ሰዎችን ለምን ወንድ ወይም ሴት ሆናችሁ ብለን እንጋፋቸዋለን ። የምናከብረው ጎበዝ ልጆች ስለወለደ ከሆነ ልጆቹ የሞቱ ቀን እናንጓጥጠዋለን ። የምናከብረው ሰውነቱን ከሆነ ክብራችን ጸንቶ ይኖራል ።

ወንድም ሴትም ሰው ናቸው ። ሰው የወል መጠሪያ ነው ። ሰው የሚለው የተፈጥሮ ስም ነው ። ሰው የሚለው ባሕርያችንን የሚገልጥ ስም ነው ። ጠባያችን ይለዋወጣል ፣ ባሕርይ ግን የጸና ነው ። ጠባያችን ልዩ ልዩ ነው ። ባሕርይ ግን ወጥ ነው ። ሰው መሆን ቀዳሚ ነው ። ሰው መሆን በእግዚአብሔር ፊት እውቅና አለው ። ሰው መሆን ዋጋ አለው ። ሰው መሆን አርአያ ሥላሴ ነው ። ክርስቶስ የሞተው ለሰው ነው ። ለሀብታም ለድሀ ፣ ለጥቁር ለነጭ አልሞተም ። ሰውን ለማክበር ሰው መሆኑ በቂ ነው ። ለወዳጃችን ሰው ሆነን ከመቅረብ በላይ ምንም ማድረግ አንችልም ። ሰው መሆን ንጉሥ ዳዊት ለአልጋ ወራሹ ለሰሎሞን የመከረው ነው ። ንጉሥነትም ሰው አያደርግም ። ሰውነት ተፈጥሮ ነው ። ሰው ሆኖ የተወለደው በምርጫው አይደለም ። ሰው ሆኖ ለመኖር ግን ምርጫ ያስፈልጋል ። ሰውን የምናከብርበት መስፈርት ማንነታችንን ይገልጣል ።

አንቱ ለማለትም አንተ ለማለትም መቸኮል መልካም አይደለም ። አክብረን ስናዋርድ የሰማን ሰው ይታዘበናል ። እየሸሸን ይመጣል ። ቀኑ ወጥ አይደለም ። ጠዋት ቀዝቃዛ ፣ ከሰዓት ሙቅ ፣ ሰርክ ነፋሻ ይሆናል ። ሰውም ወጥ ኑሮ የለውም ፣ ከአየሩ ጋር ሲለዋወጥ ይውላል ። በደስታ የጀመረውን ቀን በሕመም ሊፈጽም ይችላል ። ምድር ብትዞርም በራስዋ ምሕዋር ላይ ሆና ነው ። የምትዞረውም ሰውን ይዛ ነው ። በምትዞር ምድር ላይም ሰው ኑሮው ተዘዋዋሪ ነው ። ኑሮው ቢዘዋወርም ሕይወቱ ግን ቋሚ ነው ። ትላንት ሰጪ የነበረ ዛሬ ለማኝ ይሆናል ። ትላንት አሳሪ የነበረ ዛሬ ታሳሪ ይሆናል ። የትላንት ዳኛ ዛሬ ተከሳሽ ይሆናል ። ትላንት አዛዥ የነበረ ዛሬ ታዝዞ ለመኖር እንኳ ዕድሉን ያጣዋል ። ትላንት ሰገነት የሚለቀቅለት ዛሬ መቃብር ይቆፈርበታል ። ትላንት ስም አጠራሩ ረጅም የነበረ ዛሬ በሁለት ቃል “ሌባ” ይባላል ። ትላንት ጥሩ ሥነ ምግባር የነበረው ዛሬ ተሳስቶ ይሆናል ። የትላንት ዘማሪ ዛሬ ዘፋኝ ፣ የትላንት አማኒ ዛሬ ከሀዲ ፣ የትላንት ሰባኪ ዛሬ ሰነፍ ሆኖ ይሆናል ። ክብራችን ግን እንደ ጥንቱ ሊሆን ይገባዋል ። በማክበር ውስጥ ክቡርነታችንን እናሳያለን ። ክቡር ያከብራልና ። ሰው ሰውን አይንቅምና ።

አባ መስጠት እያለ ያወድስ የነበረ ዛሬ ሲያጡ ድሮም በሌብነት የተገኘ መቼ ይበረክታል ? ካለ ፣ አገር ወዳድ ብሎ ይመሰክር የነበረ “ባንዳ” ብሎ ከሰደበ ፣ ቅዱስ እኮ ነው ብሎ አወድሶ “ሰው መሳይ በሸንጎ” ካለ ፣ “በአንተ መዝሙር ባንተ ስብከት ሕይወቴ ተለውጧል” ብሎ የመሰከረ “ሊያሳስተኝ ነበር” ብሎ ከከሰሰ … ይህ ራስን ማዋረድ ነው ። ሰውን ቋሚ በሆነ አድራሻ ማግኘት ከባድ ነው ። ሰው ሲዋዥቅ የሚኖር ተወዛዋዥ ፍጡር ነው ። ለመጣው ጌታ ሁሉ መነስነስ ፣ ያከበሩትን እያዋረዱ አዲሱን ልዘልህ ማለት ቀላል መሆናችንን የሚያሳይ ነው ።

አንቱ የምለውን ሰውዬ ፣
አንተ አልለውም አቃልዬ ፤
ዓባይ ይጎድላል እንኳን ሰው ፣
ጊዜ ሲያዋርደው ።

ያከበርነው ሰው ዝቅ ብሎ ፣ ራሱን ሸጦ ፣ ቀኑን መስሎ ፣ ኑሮውን ከስሮ ብናየውም ክብራችን ቋሚ መሆን ይገባዋል ። ነገ ለማዋረድ ዛሬ ማክበር አይገባንም ። በዚህ ሕሊናችንን ፣ ሰዎችንና እግዚአብሔርን እናተርፋለን ። እርሱ ለተጎዳው የእኛ ማቃለል ከንቱ ነው ። ክፉ ሰው ቢሆንም በፍርድ እንጂ በበቀል ልናሳምነው አይገባንም ። ጉዳት በራሱ ተናጋሪ ነውና የተጎዳን ሰው መናገር አያስፈልግም ። ራሱን እንዳያይ እናደናግረዋለን ። ክፉ ሰውም መልካም ስናደርግለት ያልዘራውን እያጨደ ነውና እየከበደው ይመጣል ። ከዚህ ሁሉ በላይ ያከበርነውን ማዋረድ አይገባንም ። እኔን ጠብቀኝ እያልን ለደከሙት ፣ ለሰነፉት መጸለይ ይገባናል ። ባልጸናው ዓለም ላይ ሰው የተለዋወጠ ኑሮ ይኖራል ። ባገኘው ዕድል ይከብራል ፣ ተራው ሲያበቃ ዝቅ ይላል ። ይህ የሚገርመን እንግዳ ሰዎች ሳንሆን ይህ በእኛም እንደሚደርስ የምናምን ሰዎች መሆን ይገባናል።

ቃል እንግባ ። በምንም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ያከበርኩትን ሰው አላቃልለውም ። እግዚአብሔር ሆይ እባክህ አግዘኝ ።

የብርሃን ጠብታ 15
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ