የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አልተዋችሁም /ክፍል 2

መስከረም 5

2- ፍርሃት እያከታተለ ልባቸውን ይደልቀዋል

የሙት ልጅ ስሜት የሚታገላቸው በፍርሃት ራሳቸውን ይቀጣሉ። ፍርሃት ውስጣዊ ብርድ ነው። ቢለብሱ አይሞቅም ። በዙሪያ ያሉ ሰዎች ፍርሃትን ሊያስወግዱ አይችሉም ። ፍጥረታት ሁሉ በአጠገባችን ሊቆሙ ይችላሉ ፣ በውስጣችን የሚሆን ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። አዎ የፍርሃት መድኃኒቱ እርሱ ያህዌ ብቻ ነው ። በልብ ዓለም ተገኝቶ የልብን ብርድ ማውጣት የሚችል እርሱ ብቻ ነው። ደጋግ አባቶች ልጃቸው ሲታመም “እኔ እያለሁ ና” ብለው ካቦርታቸው ውስጥ ያቅፉታል ። በፍቅር ሙቀት ላብ በላብ ሁኖ ልጁ ይድናል ። ትልቁ መድኃኒት አለኝታ ማግኘት ነው ። ከትልልቅ ሆስፒታሎች ይልቅ የአፍቃሪ አባት ካፖርት ውስጥ እውነተኛ ፈውስ አለ ። ዓለም አልተቀበለኝም ለሚሉ ፣ ራሳቸውን በመስተዋት ሊያዩ ለፈሩ የእግዚአብሔር ፍቅር የመኖር ድፍረት ይሆናቸዋል ። ከእርሱ በቀር አልተዋችሁም የሚል ፣ እንደ ተናገረው የማይተው ማንም የለም ።

የሙት ልጅ ስሜት ፣ ስሜት እንጂ እውነት ላይሆን ይችላል። ብዙ ሰዎች አለመርካት ሲይዛቸው እያላቸው እንደሌላቸው ይሰማቸዋል፤ እምነት በልባቸው የሞላ ሰዎች ደግሞ ምንም ሳይኖራቸው ሁሉ እንዳላቸው ይሰማቸዋል። የአእምሮ መረበሽ ሲመጣም ምንም የለኝምና ሁሉ አለኝ የሚል እንቅስቃሴ ሊታይ ይችላል። ሁሉ እንዳላቸው እየተሰማቸው “አንተን አንግሥሃለሁ ፣ ሚሊየን ብር እሰጥሃለሁ” ይላሉ ፤ አሊያም ልጃቸው አጠገባቸው ተቀምጦ “ልጄ ትቶኝ ሄደ” የሚል የእጦት ስሜት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ። የሙት ልጅ ስሜት የሚሰማቸው ሁሉም ነገር የከዳቸው መስሎ ይሰማቸዋል። ነቢዩ፡- “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ?” ብሏል። (መዝ. 21፡1) ። እግዚአብሔር ትቶኛል የሚለው ሰዋዊ ስሜት እንጂ እውነት አይደለም ። ምክንያቱም የቃል ኪዳን አምላክ የሆነው እግዚአብሔር “አለቅህም ፣ ከቶም አልተውህም” ብሏል ። እግዚአብሔር ልጆቹን ተወ ማለት ራሱን ካደ ማለት ነው ። ትተኸኛል ብንለው ግን በፍቅር ይሰማናል ። አባት ልጁን የማይተወው ስለ አባታዊ ፍቅሩ እንጂ ልጁ አትተወኝ ስላለው አይደለም። ልጅም “እኔን ትተኸኛል” ብሎ አባቱን ቢወቅስ አባት በፈገግታ ያየዋል ፣ በመገረም ይሰማዋል ። ምክንያቱም ስሜት እንጂ እውነት አይደለምና ። ስሜት ካደረ የማይውል ፣ ከዋለ የማያድር ተለዋዋጭ ነው። እውነት ግን አድሮ የሚገኝ ነው ።

እግዚአብሔርም ስሜታችንን የመግለጥ ነጻነት ሰጥቶናል ። ጌታችን በመስቀል ላይ ካሰማው ጩኸት አንዱ፡- “አምላኬ አምላኬ ፣ ስለምን ተውኸኝ?” የሚለው ነው (ማቴ. 27፡46)። የሚበዛው የሰው ልጅ በዚህ የመተዉ ስሜት ውስጥ ያልፋልና ሕመማችንን እውቅና ሊሰጠው የዚህን ስሜት ስቃይ ለዘላለም ሊሽረው ይህን አለ ። ንጉሥ በመጨረሻ አንድ ተግባር ላይ ሲገኝ የከረመው ሩጫ ሁሉ መጠቃለሉን ሊያበስር ነው ። እግዚአብሔር እንዳልተወን በገነት ጫካ መፈለጉ በቂ ነበር ፣ በሥጋ ማርያም ተገልጦ በመስቀል ላይ መሞቱ ፣ ከዚህ በኋላ ይተወኛል የሚል ስሜት እንዳይገዛን ለማወጅም ነው ። የሞተለትን ልጁን የሚረሳ አባት የለም ። ልጁ ከንቱ ቢሆን እንኳ ስለ ድካሙ ልጁን ይዞት ይኖራል ። ፍጥረኝ ሳንለው ፈጠረን ፣ በመስቀል ላይ ሞቶ አዳነን ፤ ከማኅፀን እስከዚህች ሰዓት ጠበቀን ። ታዲያ እንዴት ሊተወን ይችላል?

የመተው ስሜት ከባድ ነው። ብዙ የሰው ዘር በየዘመናቱ አልፎበታል። ጌታችንም ለዚህ ጩኸት እውቅና ሰጥቷል ። መልእክቱ ጩኸታችሁን አውቀዋለሁ የሚል ነው ። ጥያቄአችንን ወስዶ መልሱን ሰጥቶናል። በአማኑኤል ስሙ ከእኛ ጋር ሆኗል። አንዳንድ ጊዜ ሰማይ የጠቆረብን ፣ ቀትር የጨለመብን ፣ ምድር የከዳን ፣ ክርስቶስ የተወን መስሎ ይሰማናል ። የተሰቀለው ክርስቶስ ይህን ስሜታችንን በዕለተ ዓርብ ፈውሶታል ።

ይቀጥላል

ዕለተ ብርሃን 5

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ