/ከመጽሐፈ መነኮሳት አረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳን 34 ላይ ተወሰደ/
ቤተ ጳውሎስ፤ዓርብ፣ ሚያዝያ 12 2004 ዓ.ም.
ድንቅ ነገር እነግርህ ዘንድ እወዳለሁና፤ ወንድሜ ጸጥ ብለህ ስማኝ ኅሊናህን ከዝንጋዔ ወስነህ ስማኝ፡፡ ልብህን ከሥጋዊ ሁከት ለይ፡፡ እንዲህ የሆነ እንደሆነ በትሩፋት የተነገረውን ጸጋ ታገኛለህ በትሩፋት መዓዛ ጸጋን ታሸታለህ፡፡
ሕፃናትን የፈጠረ ጌታ ትሕትናን የዕለት ጽንስ በመሆን እንደ ዠመረ ዕወቅ፡፡ ትሕትናን ከሱ ተማር፤ ስላንተ የሠራውን ሥራ ሁሉ ታውቅ ዘንድ በትሕትና ኑር፡፡ እርሱን አስመስሎ ይወልድህ ዘንድ አንተን መስሎ ተወለደ፤ ዓለምን የፈጠረ፣ የሁሉ ማረፊያ ጌታ ቤት እንደሌለው በጎል ተወለደ፤ በጨርቅ ተጠቀለለ፣ በተናቀ ቦታ በጎል አደረ፡፡ የሥጋ ሀብት የነፍስ ሀብት መገኛ ሲሆን ለዘለዓለሙ ነግሦ የሚኖር ንጉሠ ነገሥት ጌታ በጨርቅ ተጠቀለለ፡፡ የስደተኞች ማረፊያ፣ መጠጊያ የሚሆን እሱን እሽኮኮ ብለው አሸሹት፡፡ የሁሉ ደስታ የሚሆን ጌታን ሄሮድስ ይገድለዋል ብለው እየፈሩ አሳደጉት፣ መንግሥትን ሁሉ የሚያሳልፍ መከራን የሚያሳልፍ እሱን ጸብ ክርክርን የሚያጠፋ እሱን ይሙት በቃ እንደተፈረደበት ሰው ካገር አስወጥተው ሰደዱት፣ ሞትን የሚያጠፋ እሱ ሲሆን እንገለዋለን ከሚሉ ሸሽቶ አመለጠ፡፡
ከተለዩ የተለየ፣ ከከበሩ የከበረ ሲሆን አንተን ያከብርህ ዘንድ በውኃ ተጠመቀ፡፡ ልዕልናውንም አብ በዮርዳኖስ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲመሰክር ተሰማ፤ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍበት ታየ፡፡ ካባቱ ጋር ያዋህድህ ዘንድ አንተን ለመሻት የመጣ ወልድ እንደሆነ ታውቅ ዘንድ ከርሱ ጋር ለመኖር በበጎ ሥራ ብትመስለው ወደ አባቱ ያቀርብህ ዘንድ በትሩፋት መጋደልን፣ ድል መንሣትን ያስተምርህ ዘንድ አርባ ቀን ጦመ፡፡ አንተ ቡሩክ ተብለህ ትመሰገን ዘንድ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ…” ብለው አይሁድ ዘበቱበት። በአጋንንት እጅ በኃጢአት በትር የተመታ ርእሰ ልቡናህን ያከብር ዘንድ ራሱን መቱት። የሰይጣንን ምክር ሰምታ የሚያሳዝን ኃጢአት የሠራች ሰውነትህን ጣዕም እንዲገኝባት ያደርጋት ዘንድ መራራ ከርቤ ጠጣ፡፡
በዕፀ በለስ ምክንያት ከመጣ ሞት ያድንህ ዘንድ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ። ከመቃብር ያስነሣህ ዘንድ ወደ መቃብር ወረደ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያወጣህ ዘንድ ወደ ሲኦል ወረደ፤ ይህን ሁሉ ስላደረገልህ ፈንታ አንተ የምትሰጠው ዋጋ ምንድን ነው? እስኪ ንገረኝ፤ ከዚህ ማዕረግ ደርሰህ እርሱን በማየት ደስ ይልህ ዘንድ ከወደድክ የእርሱን ነገር በመናገር የምታደንቅ ብቻ አይሁን እንደ ዮሐንስና እንደ ጴጥሮስ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከተው እንጂ። እኔ እንደነገርኩህ እሱን በማሰብ ፀንተህ ኑር። እንዲህ የሆነ እንደሆነ በእውነት ይገለጽልሃል፣ የተወደደ መልኩን ዓይቶ ለማድነቅ እንድትበቃ ያደርግኻል፡፡ በበጎ ፍቅሩ ሰውነትህን እንደ እሳት ያቃጥላታል፡፡ በሱ ዘንድ ባለሟልነትን ሰጥቶ ደስ ያሰኝኻል፡፡
እንደ እመቤታችን በክንድህ እቀፈው፣ ሰውነትህም እንደ እመቤታችን ለሱ ሞግዚት ትሁን። ሰብአ ሰገል እጅ መንሻን ይዘው ወደሱ በመጡ ጊዜ እጅ መንሻህን ይዘህ ከርሳቸው ጋር እጅ መንሻውን አቅርብለት፡፡ ከእረኞችም ጋር መወለዱን ተናገር፡፡ ምስጋናውን ከመላእክት ጋር ተናገር፣ ወደ ቤተ መቅደስም ባገቡት ጊዜ እንደ ስምዖን በክንድህ ታቀፈው፤ ወደ ግብጽ በወረደ ጊዜ አሽኮኮ ብለኸው ውረድ። አቅፈኸው ከዮሴፍ ጋር ሂድ፡፡ እንደ ምድረ ግብጽ ያለች ሰውነትህን እንደ ኢየሩሳሌም ያደርጋት ዘንድ ከሕፃናት ጋር ሲድህ ሰርቀህ ሳመው፡፡ በመዓዛው ደስ ይላት እንደነበረች እንደ እመቤታችን የመላእክት፣ የጻድቃን መገኛ የሚሆን የጌታ መዓዛውን አሽት፡፡ እንደ እመቤታችን ያቅፈው የነበረ፣ በመዓዛውም ደስ ይለው የነበረ አንዱን ሰው እንደማውቀው በእውነት እናገራለሁ፤ ሕፃናትን ምሰል፤ በሕፃንነቱ ሳለ ከሄደበት ሁሉ ተከተለው፡፡ እንዲህ የሆነ እንደሆነ ፍቅሩ ባንተ ታድራለች፡፡
ከሱ ጋር አንድ በመሆንህ ይዳሰስ በነበረ በማኅየዊ ሥጋው ያለ መዓዛን ከሟች ሥጋህ ታሸታለህ፡፡ መምህራን በጠየቁት ጊዜ እሱም በመለሰላቸው ጊዜ አጠያየቁን አመላለሱን አድንቅ፡፡ ለማጥመቅ ከዮሐንስ ጋር ባንድነት ኑር፣ በዮርዳኖስ የሚደረገውን ሁሉ ስማ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ሲቀመጥበት እይ፡፡ በሚጾምበትም ጊዜ ከሱ ጋር ጹም፤ ውኃውን ለውጦ ወይን ባረገ ጊዜ ጋኖችን ውኃ እየመላህ ኑር፤ ከውኃ አጠገብ ከሳምራዊት ጋር በተነጋገረ ጊዜ ያስተማረውን ትምህርት ስማ፤ አብ የሚወደውን በመንፈስ የሚደረገውን ስግደት፣ የሚሰግዱ ሁሉ በመንፈስ ለአብ ይሰግዳሉ ብሎ ሲያስተምር ስማ፤ ሙታንንም ባስነሣ ጊዜ ትንሣኤ እሱ እንደሆነ እወቅ፣ ኅብስቱንም ባበረከተ ጊዜ እንቅቡን ይዘህ ለተሰበሰቡት አድል፣ ወደ ገዳምም በሄደ ጊዜ ሄደህ ሸኘው፡፡
በመርከብም በተኛ ጊዜ፣ ጌታ ሆይ አድነን ልንጠፋ ነው ብለህ አስነሣው፣ በጉባኤም ከሱ ጋር ኑር፣ በጎዳናም ከሱ ጋር ሂድ፣ ወደ ገዳም ከሱ ጋር ሂድ፣ በመርከብም ከሱ ጋር ኑር፣ ወደ ደብረ ዘይትም ከሱ ጋር አብረኸው ውጣ፣ በምኩራብም፣ ብፁዓን እያለ ሲያስተምር ትምህርቱን ስማ፣ ያስነሣህ ዘንድ ከአልዓዛር ጋር በመቃብር ኑር፣ በኃጢአት ከመጣ ፍዳ ትድን ዘንድ እንደ ማርያም በዕንባህ እግሩን እጠበው፤ በራስህም ጠጉር አድፈው፡፡ የኃጢአትህን ሥርየት ኃጢአትህ ተሰረየልህ ሲል ትሰማ ዘንድ፤ በማዕድም ጊዜ እንደ ዮሐንስ ባጠገቡ ተቀመጥ። ኅብስቱን በባረክ ጊዜ ሥጋውን ደሙን ከጁ ተቀበል፡፡ የደቀ መዛሙርቱን እግር ባጠበ ጊዜ ከኃጢአት ያነጻህ ዘንድ ቀርበህ እጠበኝ በለው፡፡ ማኅደረ እግዚአብሔር ሰውነትህን ንጽሕት አድርጋት፡፡ እሱን ለማመስገን ብቃ፣ በምግባር፣ በሃይማኖት ተከናወን፡፡ ነገረ ጰራቅሊጦስን ለመማር የበቃህ ትሆን ዘንድ፣ ካምስት ገበያ ሰዎች ጋር ከፊቱ ቁም፣ ከሱ ጋር መከራ ተቀበል፡፡ ይህ አሳች፣ መባልን፣ ሳምራዊ መባልን፣ መዘበቻ መሆንን ተቀበል፡፡
ወሪቀ ምራቅን ተቀበል፤ በቀኖት መቸንከርን ተቀበል፣ ከሱ ጋር እንደ እሱ በመስቀል ተሰቀል፡፡ በተነሣ ጊዜ (በመዋሐድ ጊዜ) ደስ ይልህ ዘንድ ከሱ ጋር መፃፃውን ፣ ከርቤውን ጠጣ፡፡ ራሱን ዘለፍ እንዳደረገ አንተም ዘለፍ አድርግ፣ እርሱ እንደ ተነሣ ትነሣ ዘንድ እንደሱ፣ ከሱ ጋር ሙት እኩያን አይሁድ በሱ ያደረጉትን ሁሉ ተቀበል፡፡ የማትመረመር ቸርነቱን ፈጽመህ አድንቅ፣ ምን አደረገ ትለኝ እንደ ሆነ፣ መላእክትን አታጥፉ ብሎ ከለከላቸው፣ ዓለምን፣ በዓለም የሚኖሩትን ሁሉ ያጠፏቸው ዘንድ አላሰናበታቸውም፡፡ ዓለቶች ተሰነጣጠቁ፣ ሙታንም ተነሡ ልቡናችን ግን ከጽናቱ አልተለየም፣ ማለት አላመነም፡፡ ሕዋሳተ ነፍስም ትንሣኤ ኅሊና አልተነሡም።
ሰውነትህ እንደ ማርያም መግደላዊት በፍርሀት፣ በረዓድ ሁና ከመቃብሩ አጠገብ ትቁም፡፡ መላእክት ምን ያስለቅስሻል ብለው ይጠይቋት ዘንድ፣ ጌታን ባየችው ጊዜ የት ወሰድከው ብላ ተክል ጠባቂውን እንደ ጠየቀችው ትጠይቀው ዘንድ ያን ጊዜ እንድታውቀው ሆኖ ይናገራታል፡፡ በዝግ ደጅ ወደ ጽርሐ ጽዮን በገባ ጊዜ ተነሥተህ ተቀበለው፡፡ በጥብርያዶስ ቁሞ ልጆቼ የሚበላ አላችሁን? ብሎ በጠየቀ ጊዜ ጴጥሮስን ምሰለው፡፡ መላእክት ያዘጋጁትን ማዕድ ከሱ ጋር ብላ፡፡ ባረገም ጊዜ በአንብሮተ እድ ይባርክህ፣ ይሾምህ ዘንድ ራስህን ዘንበል አድርግ ወዳየር ተመልከት፡፡ ጌታ ባረገ ጊዜ በመላእክት ብርሃን ያበራልና፡፡ ጥቂት ቀን በጽርሐ ጽዮን ኑር፡ ቋንቋ የሚገልጽ መንፈስ ቅዱስ ያድርብህ ዘንድ ወንድሜ በፍጹም ትጋት ሁነህ በልቡናህ ይህን አስብ፡፡
(አረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳን 34 ገጽ 189-194)