የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አሳርፈን

“እርሱ ሰላማችን ነውና ፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው ።” ኤፌ. 2 ፡14-17 ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው ሰላምን ይዞ ነው ። ስለ ሰላም ሰበከ ፣ ስለ ሰላም ደሙን አፈሰሰ ። እርሱ ራሱም ሰላማችን ተባለ ። አንዳንድ ሰዎች ጋ ስንሆን ሰላም ይሰማናል ። ሕይወታችን ከፍርሃትና ከጥድፊያ ይድናል ። እነዚህ ሰዎች ክርስቶስን በልባቸው የተሸከሙ ሰዎች ናቸው ። ሰላማቸው ከእነርሱ ተርፎ እኛን ያረጋጋናል ። ሕይወትን ቀለል አድርገን እንድናያት ፣ ኑሮንም እንዳንሰጋ ያስገነዝቡናል ። ወደ እነርሱ ስንሄድ በፍርሃት ከነበረ ፣ አሁን ስንመለስ ግን በመረጋጋትና ከችግሩ በላይ በማየት ነው ። ክርስቶስ ያላቸው ሰዎች እንዲህ ካረጋጉ ራሱ ክርስቶስ ከዚህ ይልቅ ዕረፍትን ይሰጣል ። የሰላምን ፍቺ ለማየት እንሞክራለን ። ሰላም ማለት አለመታወክ ፣ አለመፍራት ፣ አለመጨነቅና አለመስጋት ነው ። ሰላም የችግሩ መወገድ ሳይሆን ከችግሩ በላይ የሚሰማን መለኮታዊ ዕረፍት ነው ። ሁከት የሚባለው መናወጥ ፣ ዕረፍት የሌለው ሌትና ቀን ማሳለፍ ነው ። ሰዎች እንፈልጋችኋለን ሲሉን በግምት ማብሰልሰል ፣ የሕክምና ናሙና ሰጥተን ውጤት እስኪመጣ ክፉ ክፉ ማሰብ ፣ የውጭ ጉዳይ ይዘን ቪዛ ይሰጡኝ ይሆን ወይስ ይከለክሉኝ እያልን ሌትና ቀን መጨነቅ እርሱ ሁከት ነው ። ያለመቋረጥ የሚተነኳኮሉን ሰዎች ካሉ እነዚህ ሰዎች ሰላም አጥተው ሰላም እየነሡን ነው ። ለጊዜው እንጋፈጣቸውና ማዘን ስንጀምር ሁከት በውስጣችን ይነሣል ። እነርሱ ተኝተው እኛ መበጥበጥ እንጀምራለን ። ልጆቻችን ደጅ ወጥተው እስኪመለሱ ፣ የትዳር አጋሮቻችን ሲያመሹ የሚሰማን ሰይጣናዊ ሁከት አለ ። ሁከትን ማባበል አይጠቅምም ፣ ያለማመን ኃጢአት ነውና ንስሐ መግባትና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መጠየቅ ይገባል ።

ሁከት ስስ ማዕበል ሲሆን ውስጣችን ማረፊያና መቆሚያ ያጣል ፣ ኮት ልናነሣ ሂደን ሱሪ እናነሣለን ፣ ሰላም እደሩ ማለት ሲገባን ሰላም አደራችሁ ወይ  ብለን ሰላምታ እንሰጣለን ፣ በአሳብ ጭልጥ ማለት ፣ ዝም ብሎ ግራ መጋባት ፣ ሰዎች እያዋሩን በአሳብ መጥፋት ፣ ከውስጣችን ጋር ውጤት የሌለው ስብሰባ መቀመጥ እርሱ ሁከት ፣ የቁም ቅዠት ነው ።

ሰላም ማጣት የምንለው ሁለተኛው ፍርሃት ነው ። ፍርሃት መንቀጥቀጥ ፣ የሥጋና የነፍስ መራድ ነው ። ፍርሃት ሞትን እየተመኘ ሞትን የሚፈራ አደናጋሪ አሳብ ነው ። ፍርሃት በሚያስፈራሩ አሳቦችና ነገሮች ሊመጣ ሲችል ከዚህ ውጭም ዝም ብሎ ሆዳችንን ባር ባር ይለናል ። አንዳንድ ጊዜ ይሆናል የምንለው ነገር ቢሆን እንኳ ከዚህ ፍርሃት ያነሰ ሊሆን ይችላል ። አንድ ሰው፡- “የማይፈሩት ለምንድነው ” ብዬ ስለ ድፍረታቸው ጠየቅኋቸው ። እርሳቸውም፡- “ብታሰር እፈታለሁ ፣ ብሞት እቀበራለሁ ለምን እፈራለሁ ?” አሉኝ ።

አንዳንዴ የምንፈራው የሚፈሩንን መሆኑ ይገርማል ። ፍርሃት የምንፈጥረውና የተፈጠረ ነገር ላይ የሚመሠረት የነፍስ ውዥንብር ነው ። በይሆናል ፍርሃት ውስጥ የምንገባበት ፣ በግምትና ባልተጨበጠ ነገር ራሳችንን አስረን የምናሰቃይበት ነው ። ፍርሃትን ማባበል አይገባም ። በቆራጥነትና በእምነት ከሁሉ በላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወግድ ልንለው ያስፈልጋል ። “ዘጠኝ ሞት ቢመጣ አንዱን ግባ በሉት” እንዲሉ ። የምንሞተው አንድ ጊዜ ነው ማለት ነው ። ደግሞም “ሰው ታሞ እንጂ ፈርቶ አይሞትም” ይባላል ። ሰይጣን አማንያንን ከሚዋጋበት ዋነኛ መሣሪያዎቹ አንዱ ፍርሃት ነው ። የፈራ ሰው በእጁ ያለውን ይጥላል ። የወርቅ ጉድጓዱን ለሌባ ያስጎበኛል ። ፍርሃት ስፍራን ያስለቅቃል ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶ ሰላም ግን ከፍርሃት ያድናል ።

መጨነቅ መጠበብ ፣ መድረሻ ማጣት ፣ በአሳብ ሰንጣቃ ዓለት ውስጥ ገብቶ መፈራገጥ ፣ ነገሮችን አጨልሞ ማየት ፣ ፀሐይ ወጥታም በግርዶሽ ውስጥ መቀመጥ ፣ ተስፋ ማጣት ፣ አንድን ነገር ደጋግሞ ማሰብ ፣ ከራስ ጋር መጋጨት ፣ መኖርን መጥላት ፣ ስፍራ መልቀቅ ፣ ብረሩ ብረሩ የሚል ሰይጣናዊ ስሜት ነው ። የብዙ ሰዎች አዋኪነት አመል ብቻ አይደለም ፣ ጭንቀትም ሊሆን ይችላል ። በትዳር ውስጥ የጭንቀት ስሜት ሲከሰት ሌላኛው አጋር ከመገንዘብ ይልቅ የጸባይ ለውጥ እየመሰለው አላስፈላጊ ጠብ ውስጥ ይገባል ። በዚህ ዓለም ላይ የሚያሳዝኑ ሰዎች ቢኖሩ በጭንቀት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ናቸው ። እነዚህ ሰዎች በትንሽ ነገር እንደ ተጨነቁ በትንሽ ተስፋ ሊበረቱ ይችላሉ ። ሁለት ነገሮችን ላለማጣት ፣ ሁለት ሰዎችን በእኩል ይዞ ለመሄድ ፣ ሰዎችን ሁሉ ለማስደሰት መሞከር ፣ ዋስትናን ገንዘብ ላይ ማድረግ ፣ ልጆችን በጣም አትኩሮ ማየት ፣ ፍቅርና አምልኮትን ለይቶ አለማወቅ ፣ ለሁሉም ሰው የማይፈጽሙትን ነገር አደርጋለሁ ብሎ ቃል መግባት ፣ ወደፊት እንዲህ ቢመጣስ ፣ ይህ ችግር ይህን ችግር ይዞ ከተፍ ቢልስ ብሎ መስጋት ፣ ለማያፍሩ ሰዎች ማፈር … ለጭንቀት ይዳርጋል ። እርሱ ሰላማችን ነውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማንነቱ ሰላምን ይሰጠናል ።

ስጋት ነገና ኋላ ላይ የሚመሠረት የአሳብ ረመጥ ነው ። ስጋት ይለበልባል ፣ ያቃጥላል ። ነገ ለመድረሳችን እርግጠኛ ሳንሆን ለነገ በብዙ እንሰጋለን ። ያልመጣው ነገ ፣ የመጣውን ዛሬ ያበላሻል ። ስጋት ውስጥ የምንገባው ሥልጣን የእግዚአብሔር መሆኑን ረስተን ሰዎችን ሰጪ ነሺ ፣ አዳኝ ገዳይ አድርገን ማመናችን ነው ። የሚመጡ ዘመናት እንዳያሰጉን እግዚአብሔር የትንቢት ጸጋን ይልካል ። ትንቢት ነገም በእግዚአብሔር የታወቀ ነውና አትስጉ የሚል የእምነት መልእክት አለው ። የሚሰጉ ሰዎች ሥጋቸውን ይጨርሳሉ ፣ ነፍሳቸውን ያቀጥናሉ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሰላማችን ነው ። በቤተ ክርስቲያን ከሚጸለዩ ድንቅ የቡራኬ ጸሎቶች አንዱ “የተጨነቀችውን ነፍስ አሳርፍ” የሚል ነው ። በሞት ጣር ብቻ ሳይሆን በአሳብ ጣር ያሉትን ክርስቶስ ያሳርፋል ። አቤቱ አሳርፈን !!!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ