የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አስቀድሞ ማሰብ

“ከመዝለልህ በፊት መጀመሪያ የት እንደምታርፍ አረጋግጥ ።” /የእንግሊዞች አባባል/

ኩርፊያ ፍቅራችንን ይገልጣል ። ኩርፊያ ፍቅራችንን ይገድላል ። ኩርፊያ ስሜትን መግለጫ ነው ። ኩርፊያ ጠባይ ሲሆን ራስን መበቀያ ነው ። ኩርፊያ ሰላምን ከልብ ውስጥ ያወጣል ። ኩርፊያ የጠብ እሳት እንዳይጠፋ እንጨት ያቀብላል ። ኩርፊያ የዳመነ ፊት ፣ የጨገገ ልብ ነው ። ኩርፊያ የአቅም ማነስ መገለጫ ነው ። ኩርፊያ አላድንህም አልገድልህም በሚል አስተሳሰብ መሐል ላይ መቆም ነው ። ኩርፊያ ወላጆቻችን በጠዋቱ ያላስጣሉን ጠባይ ነው ። ኩርፊያ ሞኝ ያደርጋልና ሳልነግረው ብስጭቴን ይወቅልኝ የሚል አስተሳሰብ ነው ። ኩርፊያ ተጎዳሁ ከሚልና ልጎዳ እችላለሁ ከማይል ሕሊና የሚወጣ ነው ።

ኩርፊያ ትክክለኛ ያልሆነ ቅያሜን የመግለጫ መንገድ ነው ። ንግግር በማይችሉ ፣ ውይይት በሚፈሩ ፣ ብወያይስ ምን ለውጥ ይመጣል ? በሚሉ ሰዎች ምክንያት ኩርፊያ ይፈጠራል ። ኩርፊያ ቤትን ያጨልማል ። ትዳርን ገደል አፋፍ ላይ ያደርሰዋል ። ኩርፊያ ልብ ሲቃጠል የሚወጣ ጢስ ነው ። አኩርፈው የተቀመጡ ሰዎችን ማቅረብ ካልተቻለ አንድ ቀን ጦር እየመሩ ይመጣሉ ። የኩርፊያ አደባባዩ ፊት ነው ። ሰዎች በማኩረፍ ዝም ይላሉ ፣ ዝምታው ግን የማስተዋል ዝምታ አይደለም ። ሰዎች በማኩረፍ ኀዘነተኛ ይሆናሉ ፣ ኀዘኑ ግን መንገዱን አልጠበቀምና መጽናናትን አያስገኝም ። ሰዎች በማኩረፍ የጀመሩትን ሥራ ያቆማሉ ፣ ይቅር የሚሉት እንጂ የማይበድል ሰው የለምና ከማንም ጋር መኖር አይችሉም ። አንዳንድ ኩርፊያ በልብ ውስጥ ያለ ሲሆን በሐሰተኛ ፈገግታ ይሸፈናል ፣ አንዳንድ ኩርፊያ ደግሞ ልብ ሊያናግር እየፈለገ አልሸነፍም በማለት ፊቱን የሚያጨልም ነው ። ሰውዬውን በአሳባቸው እያዋሩት ሲመጣ ዝም የሚሉት አኩራፊዎች አሉና ይህ ኩርፊያ ጅል ያደርጋል ። እነዚህን ሰዎች የሚያስቅ ቀልድ ሲያወሩላቸው ወዲያው ወደ ቀድሞ ፈገግታቸው ይመለሳሉ ። በዚህም በኩርፊያ ሕጻን እንደሆኑ እናያለን ። በርግጥ ሰው ሕጻንነት ላይ ሽምግልናን ፣ ሽምግልና ላይ ደግሞ ሕጻንነትን ይኖረዋል ።

ኩርፊያ ከራስ ጋር ፣ ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ጋር ሊሆን ይችላል ። ራሳቸውን ያኮረፉ ሰዎች ራሳቸውን የሚጎዳ ነገር ያደርጋሉ ፣ ሰዎችን ያኮረፉ ሰዎች ብቸኛ ይሆናሉ ። እግዚአብሔርን ያኮረፉ ሰዎች ጸሎት ማድረግ ፣ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ያቆማሉ ። አኩራፊ ስንሆን ሰዎች እየፈሩን ይመጣሉ ። ስህተታችንን ከመንገር ሰላሜን እፈልጋለሁ ብለው ከነቆሻሻችን ያቅፉናል ። ኩርፊያ እንድንጠላ ያደርገናል ። ምክንያቱም ሰዎች አቅማቸው ውስን ስለሆነ እኛን ማባባል እየደከማቸው ይመጣል ። በመጨረሻ ይለዩናል ። መልካምነታችን ሁሉ በኩርፊያ ይሸፈናል ። በተገቢው መንገድ አሳብንና ቅሬታን መግለጥ ፣ ለመወያየት መፍቀድ ፣ ሰጥቶ የመቀበልን መርሕ መጠቀም ፣ ላለመስማማት መስማማትን አማራጭ መውሰድ ፣ ካልሆነ በሰላም ለመለያየት ስልጡን መሆን ኩርፊያን ያርቃል ። ኩርፊያ ቅጽበታዊ ፣ ዕለታዊና እስከ ዕለተ ሞት የሚቀጥል ሊሆን ይችላል ። “እረኛ ቢያኮርፍ እራቱ ቁርስ ይሆናል” ይባላል ። ረጅሙን ሌሊት በረሀብ ያሳልፋል ። የበደሉት ሰዎችን ትቶ ያልበደለውን ምግብ ይጣላል ። በማኩረፉ ራሱን በራሱ ይቀጣል ። ወዳጆቹ ባለ መብላቱ ቢያዝኑም የተበሳጩበት ደግሞ ደስ ይላቸዋል ። በማኩረፍ ቤተ ክርስቲያን የቀሩ ፣ ከማኅበር የተለዩ ፣ ቃለ እግዚአብሔር ያቆሙ ብዙ ሰዎች ይኖራሉ ። ሰዎች በተለያየ ምክንያት እራታቸውን ይተዋሉ ፣ በፈቃዳቸው ስለሆነ አይርባቸውም ። በማኩረፍ እራቱን የተወ ግን ረሀቡ ኩርፊያውን ያስጥለዋል ። በልቶ ለመተኛት ቢያስብ የሚመግቡት ተኝተዋል ። በብስጭትም በረሀብም ሌሊቱን ያሳልፋል ። ኩርፊያ ማረፊያን ሳያዩ መዝለል ነው ። በማስተዋል ፣ በዕድሜ የምንማረው ነገር ማረፊያን ሳያዩ መዝለል እንደማይገባ ነው ። የበላይን ብናኮርፍ ለእኛ ይብስብናል ። ያ የበላይ ከምናስፈልገው የሚያስፈልገን ይበልጣልና ። ለበላያችን እንደ እኛ ያለ ሰው ማግኘት አይቸግረውም ፣ እንደ እርሱ ያለ ሰው ማግኘት ግን ለእኛ ይቸግረናል ።

ወደ ላይ የሚዘልል ትንሽ ሸክም የያዘ ነው ። ቀለል ያለ እውቀት ያላቸው ሰዎች መዝለል ይወዳሉ ። እየዘለሉ ሰው ላይ ጭቃ መለጠፍ ፣ እየዘለሉ “እኔ ብቻ ቅዱስ” ማለት ይቀናቸዋል ። ኖረው ሳይጨርሱ በሌላው ስህተት መሳቅ አይገባም ። ይህችን ዓለም ለመልቀቅ አንድ ቀን ቢቀረንም ልንስት እንችላለን ። ሰው ካልሞተ በቀር ራሱን ማመን አይችልም ። ሌላው የሚያደርገውን ኃጢአት ባለማድረጋችን ንጹሕ ነን ማለት አይደለም ። እኛም የራሳችን ድካም አለንና ። ጠዋት ታጥቦ የሚወጣ ማታ ቆሽሾ እንደሚመለስ ይረሳና ሰው ሁሉ የቆሸሸ መስሎ ይታየዋል ፣ ይጸየፋል ። የዛሬ ሰው የነገ ሬሳ ነንና መመካት አይገባንም ። “አለሁ በእግዚአብሔር” እንጂ “አለሁ በራሴ” የማይባልበት ዓለም ነው ።

በአንዲት ንግግር ጨርቃቸውን ይዘው ከቤት የሚወጡ ባለ ትዳሮች ብዙ ናቸው ። ባለ ትዳር የሚኖረው ተነጋግሮ ነው ። አካል አካሉን አይቀየምም ። ቀኝ እጅ ስቶ ስለ መታው ግራ እጅ ካልተቆረጠልኝ ብሎ ቀኝ እጅን አይከስስም ። ልጆች የአካል ክፋይ ሲሆኑ ተቆርጠዋልና ይሄዳሉ ። ባል ወይም ሚስት ግን አካል ናቸውና እስከ ዕለተ ሞት አብረው መኖር አለባቸው ። በአንዲት ቃል ዘለው ከቤታቸው የወጡ ብዙ ይጎዳሉ ። የፈረሰ ትዳርና የድንጋይ መቀመጫ እየቆየ ይቆረቁራል ።

አንዲት ተግሣጽ ሲናገሩአቸው መምህራነ ወንጌልን አኩርፈው የሚሄዱ ፣ ዘለው የሚወጡ ብዙ ናቸው ። ወትሮም ልጅ አልነበሩምና በአንድ ቍጣ ይሄዳሉ ። ልጅ ግን እየገረፉትም አይለይም ። በዕለት ጠብ ዘለው ከሃይማኖት የሚወጡ ፣ ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ ብለው ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን የእነ እገሌ ናት ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ።

ሯጭ ግቡን ያውቃል ። ከሯጭ በላይ እረኛ ሲሮጥ ይውላል ። ከብቶች የሚያሯሩጡት እንጂ በግብ የሚሮጥ አይደለምና ማንም ሳያውቀው ይኖራል ። የሚዘልልም ማረፊያውን ያያል ። በአገራችን፡- “አገባ ያለ ላያገባሽ ፣ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” ይባላል ። አለሁ ያሉን ሁሉ ሰዓቱ ላይ አይገኙምና ። መሬት ከመልቀቃችን በፊት ማረፊያችንን ማየት አለብን ። አስበን መድረስ እንጂ ደርሰን ማሰብ ከባድ ነው ። ለምወስነው ውሳኔ የሚጠብቀኝ ዋጋ ምንድነው ? ብሎ ማሰብ ይገባል ። ቢቻል ከሦስት ቀን እስከ ሦስት ወር ማሰብ ፣ ከአንድ እስከ ሦስት አዋቂዎችን ማማከር ፣ ጸሎትና ሱባዔ መያዝ ይገባል ። በነጻ የተውነውን ነገር በዋጋ አናገኘውምና መጠንቀቅ አለብን ። ዔሣው በቀላሉ የተወውን ብኵርና በእንባ አላገኘውም ። ፈርዖን በክብር የመጣለትን የንስሐ ድምፅ ቀይ ባሕር ውስጥ ሲሰጥም አላገኘውም ። ዕድል ካለፈ ከባድ ነውና ከመዝለላችን በፊት ማረፊያውን ማየት ይገባል ።

“ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ ፣ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” የሚባለው እንዳይደርስብን ጠንቃቃ መሆን ይገባናል ። ከሁሉ በላይ ሰው ከትላንት ጉዳቱ ፣ ከሊቃውንት ምክርም ላይማር ይችላልና የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ በጸሎት መጠየቅ ይገባዋል ።

የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ዓይኖቼን ክፈት !

የብርሃን ጠብታ 13

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 5 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ