የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አስተማሪዎቻችን

“ደስተኛ ያልሆኑ ደንበኞችህ ዋናዎቹ አስተማሪዎችህ ናቸው ።” ቢል ጌትስ

ጀማሪዎች የሚኖራቸውን ፣ ማዕከላውያን ያላቸውን ፣ ምሉዓን የሌላቸውን መስማት ይፈልጋሉ ። ጀማሪዎች ተስፋ ይፈልጋሉና የሚኖራቸውን ፣ ማዕከላውያን ብርታት ይፈልጋሉና ያላቸውን ፣ ምሉዓን ግን ማደግ ይፈልጋሉና የሌላቸውን መስማት ይናፍቃሉ ። ጀማሪዎችን ያላቸውን ብንነግራቸው ትዕቢተኛ ፣ የሌላቸውን ብንነግራቸው ደንባራ ይሆናሉ ። ማዕከላውያን ለበጎ ሥራ ሲጣጣሩ ተቃውሞን ይፈራሉና ያላቸውን መልካም ነገር ብቻ መስማት ይሻሉ ። ለማዕከላውያን የሌላቸውን ብንነግራቸው ቶሎ ተስፋ ይቆርጣሉ ። ምሉዓን ገና የማደግና የመለወጥ ናፍቆት አላቸውና የሌላቸውን ሲሰሙ እንደገና ለመሥራት ይነሣሉ ። ለምሉዓን የሚኖራቸውን ብንነግራቸው የሚኖረኝ ስኬት ካለኝ ክርስቶስ አይበልጥም ብለው አርፈዋል ። ያላቸውን ብንነግራቸው ያረጋጋቸዋል እንጂ አያሠራቸውም ። የጎደላቸውን ስንነግራቸው ግን ገና መሥራት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል ። ለሰው በቅንነት የሌለውን መንገር መሙላት ትችላለህ ብሎ ማክበር ነው ። ለሰው በጥመት የሌለውን መናገር እኔ ካንተ እሻላለሁ ለማለትና የበታችነት ስቃይን ለማስታገሥ የሚደረግ ሙከራ ነው ።

በዚህ ዘመን በሀብት ቍጥሩ ከፍተኛ ተብሎ የሚነገርለት ቢል ጌትስ ነጋዴ ነውና በንግዱ የተማረውን ሲገልጥ፡- “ደስተኛ ያልሆኑ ደንበኞችህ ዋናዎቹ አስተማሪዎችህ ናቸው” ብሏል ። ደንበኞች ለምን ደስ አልተሰኙም የሚለው ነገር እንደገና ለማሰብ ዕድል ይሰጣል ። የሠሩትን ፣ ያቀረቡትን ፣ ያደነቁትን ነገር ከልሶ ለማየት ያስችላል ። የማይረኩ ደንበኞች ጎደለ የሚሉት ነገር ቀጣዩ ሥራ ላይ ሲጨመር የበለጠ እየተዋበ ይመጣል ። ውበት የሚመጣው ጉድለትን ከማስወገድ ነው ። ዓይን ላይ ያለውን ቆሻሻ ማጽዳት ውበት ያመጣል ። ውበት ያለው ጉድለት አጠገብ ነው ። የዓይንን ቆሻሻ ለማየት መስተዋት ወይም ወዳጅ ሊነግረን ያስፈልጋል ። ውበት የሚመጣው ጉድለትን ከማወቅ ነው ። ሰው የዓይኑን ቆሻሻ ሲያይ ቀጠሮ አይሰጥም ። ወዲያው ለማስወገድ ይነሣል ። አንዳንድ ሰዎች የዓይናችንን ቆሻሻ እያዩ አይነግሩንም ። ዓይን ስንቱን ሲያይ ራሱን አያይም ። አንዳንዶች ደግሞ ቆሻሻ እንዳለብን ወይ በቅንነት አሊያም ራስህን አታጸዳም ወይ? በማለት በነቀፋ ይነግሩናል ። በቅንነትም በጥመትም ቢነግሩን የቆሻሻው መኖር ትክክለኛ ከሆነ ወዲያው እናስወግደዋለን ። ወዳጆቻችን ደግሞ ቆሻሻችንን ከመንገር ሊያነሡልን ሲጣደፉ ለዓይኔ የራሴንም እጅ አላምነውም ብለን ቶሎ ብለን እናስወግደዋለን ። ይህን ጎዶሎህን አስወግድ ወይም ልታስወግደው አትችልም በማለት ንግግር የሚጀምሩ አሉ ። በጸጋ  የበሰሉ ግን ማስተካከያውን መንገድ በማሳየት እንዲህ አድርገህ ብታስተካክለውስ ? ይሉናል ። ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሔውንም ያሳዩናል ።

ደስተኛ ያልሆኑ ተማሪዎቻችን ብዙ እንድናነብ ፣ የማብራራት ችሎታችንን እንድናዳብር ፣ የንግግር ጥበብን እንድንማር ፣ አሳብ ያለውን ቋንቋ እንድንጠቀም ያደርጉናል ። አንባቢዎቻችን ደስተኛ ካልሆኑ የአቀራረብ ስልታችንን ስናስተካክል መልካም ፀሐፊ ያደርጉናል ። የምንመራቸው ወገኖች ደስተኛ ካልሆኑ የት እንደምናደርሳቸው በትክክል አላወቁምና ራእይ እንዲኖረንና ራእያችንን መግለጥ እንድንችል ያደርጉናል ። የተደሰቱብን የጨበጥናቸው ድሎች ሲሆኑ ያልተደሰቱት ግን የምንጨብጣቸው ድሎች ናቸው ። የተደሰቱብን ሳይገባቸው ሳይረዱት ሊሆን ይችላል ። የሚነቅፉን ግን ሥራችንን እንድንመዝን ያደርጉናል ። የማይደሰቱብን ብዙዎች ሊሆኑ ይችላሉ ። የእነርሱን ጠባይ ከመገምገም ፣ ቅንነት የላቸውም ብለን ከመቀየም ያልተደሰቱብንን ነገር ደግሞ ማየት መልካም ነው ። ሲፈጠሩ ለነቆራ የተፈጠሩ የሚመስላቸው ሁልጊዜ ትችት ያበዛሉ ። አንዳንዴ ወዳጆቻችን የማይነግሩንን ጉድለት ስለሚነግሩን ልናመሰግናቸው ይገባናል ። ከጠመንጃ አፍ ደግ ነገር እንደማይወጣ ከእነዚህ ሰዎች አንደበትም የሚያንጽ ነገር አይወጣም ። ራሳቸውን የጥበብ ፖሊስ አደርገው ያስቀመጡ ፣ ጥበብ አምጡ ቢባሉ በሬን እንደማለብ ወተት የማይወጣቸው ፣ ለመንቀፍ ግን የሰሉ ሰዎች አያሌ ናቸው ። ቢሆንም ይጠቅሙናል ። እነርሱ በጥመት የተናገሩትን እኛ በቅንነት መስማት ይገባናል ። ሐኪም ቤት በዋነኝነት የምንሄደው በሽታችንን እንጂ የማያመንን ጎን እንዲነግሩን አይደለም ። በሽታችንን ለመስማት ብዙ ንዋይ እናፈስሳለን ።

አንዳንድ ባሎች በሚስታቸው ደስተኛ አያደሉም ። እርስዋም ችግሬ ምን ይሆን ? ስትል ፍጹም መንፈሳዊ ወደ መሆን ትደርሳለች ። አንዳንድ ሴቶች በባሎቻቸው ደስተኛ አይደሉም ። ባልም የጎደለኝ ምንድነው ? በማለት ራሱን ሲያይ የበለጠ እየታነጸ ይመጣል ። መምህራኖቻችን ደስተኛ ካልሆኑብን ብዙ ለማጥናትና እውቀት ጠገብ ለመሆን እንጥራለን ።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማት የጎደለንን አሳውቁን በማለት ችግሮችን ነቅሰው ለሚያወጡ ድርጅቶች ራሳቸውን ክፍት ያደርጋሉ ። ነቃሾቹም ብዙ ክፍያ የሚጠይቁ ሲሆን ድርጅቱ ያለውን ችግር ያለ ይቅርታ ዘርዝረው ያቀርባሉ ። ደስተኛ ያልሆኑብን ግን በነጻ የጎደለንን ነገር እየነገሩን ነውና እንደ አስተማሪዎቻችን ልንወስዳቸው ይገባል ። የተናገሩበትን መንፈስ ማጥናት ጥቅም የለውም ። ይህችን ዓለም ያሳወቁን ከደጎች ይልቅ ክፉዎች የሚባሉት ናቸው ። ደጎችም ጌታን አሳይተውናልና ምስጋና ይገባቸዋል ። እንደገና መሞከር ግን ሥራችንን ውብ ያደርገዋል ። ሠርተን የማንፈጽም ፤ ተሠርተንም የማናልቅ ነን ።

አቤቱ ሥራችንን ባርክልን ።

የብርሃን ጠብታ 9

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ