ሁሉም አባቶች ክፉ አይደሉም ። ሁሉም እናቶችም ደግ አይደሉም ። አባቶች የእናቶችን ክፉነት ለልጆች መንገር ፣ እናቶችም የአባቶችን በደል ለብላቴናዎች ማውራት አይገባቸውም ። በበረሃ ፣ በባሕር እየማሰነ ቤተሰቡን ለመመገብ የሚደክመው አባት ፍቅር እንደሌለው ሌላ ወድዶ እንደሚሸሽ መቆጠሩ ተገቢ አይደለም ። ብዙ አባቶች ልጆቻቸውን እንደ ካዱ ይታወቃል ፣ በደከሙለት ቤተሰብ የተካዱ አባቶችም ብዙ ናቸው ። በጉብዝናቸው የተከበሩት ሲደክሙ ደጋፊ ያጣሉ ፣ እንደ አረጀ ፈረስ ይጣላሉ ። ብቻዬን አመጣሁህ የማለትን ያህል እናቶች ለልጆቻቸው የአባትን ባዶነት ለማስጠናት ብዙ ጊዜ ይደክማሉ ። ልጆችም ቋሚ ሥራ ማግኘታቸውን ሲያረጋግጡ ትዳር ለማፋታት ደፋ ቀና ይላሉ ። የሃያና የሠላሳ ዓመት ስፖንሰር የነበረው ያ ሰው ያለ ምስጋና ይሸኛል ።
ታላቁ እስክንድር አባቱ ትልቅ ውለታ የዋለለት ፣ ዓለምን እንዲገዛ መሠረት የጣለለት ነው ። ባልተለመደ መልኩ ፣ ነገሥታት የዘነጉትን ንጉሥ ፊልጶስ ለልጁ ለእስክንድር አድርጎለታል ። በዘመኑ ፈላስፋ ከነበረው ከአሪስቶትል ይማር ዘንድ ወደ ሊቁ ልኮት ነበር ። አባቱ ልጁን በታናሽነቱ ኃላፊነት እየሰጠ ጀግንነቱ እንዲታወቅ አድርጎታል ። እስክንድርም አባቱን እጅግ ይወድ ነበር ። የመቄዶንያው ንጉሥ ፊልጶስ በጦርነት አንድ ዓይኑ የጠፋ ፣ እግሩ የሚያነክስ ፣ በጽኑ ቍስል የሚሰቃይ ሰው ነበር ። አንድ ቀን እያቃሰተ ሲጨነቅ ልጁ እስክንድር እንዲህ አለው፡- “አባቴ አትዘን ፣ ቍስሎቹ ምንም እንኳ ስቃይ ያላቸው ቢሆኑም ያገኘሃቸውን ድሎች ያስታውሱናል ፤ አባቴ ከአውሮፓ ወደ እስያ እየተጓዝህ እንዴት እንደ ተንከራተትህ እይ ፣ ይህ ቍስል ውርደት አይደለም ፣ የጀግንነት ምልክት ነው።”
እናቱ ኦሎምፒያስ አስማተኛ ፣ በራስጌዋ እባብ ይዛ የምትተኛ ክፉ ሴት ነበረች ። የአባትና የልጅን ፍቅር ለማደፍረስ በብርቱ ትተጋ ነበር ። እስክንድርም ፍቅሩ ተሸርሽሮ አባቱን እየጠላ መጣ ። ለአባቱ መሞት ፣ አባቱ ላገባት ለኪሊዮፓትራና ለልጅዋ መገደል የእስክንድር እናት እጅዋ ነበረበት ። ከዚህ ሁሉ ሬሳ በኋላ እስክንድር ነገሠ ። ዓለምን አስተዳደረ ። ከወደቀ በኋላ እንኳ በግብጽ በጥሊሞሳውያን የግሪክን ዘር ይዘው ፣ የእስክንድርን ሥልጣን ተካፍለው ለሁለት መቶ ዓመታት ያህል አስተዳደሩ ። እስክንድሪያ በስሙ ተሰይማ እስከ ዛሬ ድረስ ትናገርለታለች ። በጥሊሞሳውያኑ በእስክንድርያ የመሠረቱት ትልቁ ቤተ መጻሕፍት ከ800 ሺህ በላይ በእጅ የተጻፉ የዓለም መጻሕፍት ስብስብ ነበረው ። ይህ ቤተ መጻሕፍት የሰባ ሊቃናት ትርጉም የሆነው የብሉይ ኪዳን ግሪክኛ ለመተርጎሙ አስተዋጽኦ ነበረው ።
ታላቁ እስክንድር ለአባቱ የተናገረው አጽናኝ ቃል እጅግ የሚደንቅ ነው ። ጥበብን ከጀግንነት ከያዘ ሰው የሚጠበቅ ነው ። ጀግንነትን ከአባቱ ፣ ጥበብን ከአሪስቶትል ያገኘው ወጣቱ እስክንድር ያንን የሚሰቃይ አባቱን አበረታታው ። በአባቱ ቍስል ክብር እንደሚሰማው ይነገር ነበር ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመቄዶንያው ፊልጶስ ይልቅ ስለ ዓለም ሁሉ ቆሰለ ። ግዛቱን ለማስፋፋት ሳይሆን የሄደብንን ግዛት ለመመለስ ፣ ክብርንና ንግሥናን ሊያካፍለን ቆሰለ ። ለመንገሥ በሚቆሰልበት ዓለም ንግሥናውን ለመስጠት ፣ እኛን የካህናት መንግሥት ለማድረግ የቆሰለ አንድ ጌታ አለ ። እርሱም ዛሬን ያየንበት ፣ እዚህ የቆምንበት ምሥጢር ክርስቶስ ነው ። ክርስቶስ በቍስሎቹ ለግሪክ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም ድልን ሰጠ ። ቍስሎቹ ድሉን ስለሚያስታውሱን ሁልጊዜ ይነገራሉ ። ቍስሎቹ ያለ መቻል ሳይሆን የመቻል ምልክት ናቸው ። ከማቍሰልም መቍሰል እንደሚሻል የሚያስተምሩን ናቸው ።
የክርስቶስን አርአያ የተከተሉ ፣ ለአገልግሎት በከፈሉት ዋጋ ዓይናቸውን ፣ እግራቸውን ያጡ ፣ በማያቋርጥ ነዝናዛ ቍስል የሚሰቃዩ አባቶች ዛሬም አሉ ። ሌላውን ለማሳወቅ ብለው አሳሳች የተባሉ ፣ ሌላውን ለማትረፍ ብለው አካላቸውን ያጡ ዛሬም አሉ ። ይህች ዓለም ያለ መሥዋዕትነት የዋለችበትና ያደረችበት ቀን የለም ። መሥዋዕትነት ካለ መሥዋዕት የሚሆኑ አሉ ማለት ነው ። ብዙ ባለ ራእዮች ቍስላቸው ጽኑ ቢሆንም ድላቸውን ያስታውሰናል ። እንደ ብዙኃኑ ምን አገባኝ ብለው የተቀመጡ ሳይሆኑ ያገባኛል ብለው ጦሩን ለደረታቸው ፣ ድሉን ለሕዝባቸው የናኙ ናቸው ። ቤታቸውን ለማጽናት ብለው በቤት የቀሩ ብዙ አባቶችና እናቶች አሉ ። እኛን ለማሳደግ የተከፈለ መሥዋዕትነት ነውና ደስ ይበላችሁ ማለት ይገባናል ። መድኃኒት ያላስታገሠውን ቍስል ይህ ቃል ይሽረዋል ። ሌሎችን ስለ መርዳት የተከፈለ ዋጋ ሁሉ የጀግንነት ምልክት እንጂ የውርደት ሕመም አይደለም ። ለአገሩ ሠርቶ በሰው አገር የሚጦረው ደስተኛ አይደለም ፣ የደከመለት ሕዝብ ቍስሎቹን እንዲያውቅለት ይፈልጋል ። የሰው ልጅ ደስታ ያለው በምቾት ውስጥ ሳይሆን የኖረላቸውን ሰዎች ምላሽ በመስማት ውስጥ ነው ።
በለው ሳይሆን በሉኝ ብላችሁ እኛን ያስተማራችሁ ክብር ይገባችኋል ። መሥዋዕትነታችሁ መሥዋዕትነት አድናቂ ሳይሆን መሥዋዕት መሆንን ያስተምረናል ። የሚሰማችሁ አጥታችሁ “ሰማይ ስሚ ፣ ምድር አድምጪ ፣ ቤተ ክርስቲያን መስክሪ” ብላችሁ የተናገራችሁ ዛሬ ብዙ ጆሮዎች ወደ እናንተ ቃል አዘንብለዋልና አክብሮታችን በሰማይ ካላችሁበት ርስት ይድረሳችሁ ። እናንተን አስችሎ እኛን የመገበ አምላክ ቡሩክ ነው ።
የምንማረው፡-
የሌሎችን ውለታ መርሳት አይገባንም ።
ከአንድ በላይ የሆኑ ትዳሮች ሞትን ያፋጥናሉ።
የሰላም መሣሪያ እንጂ የጠብ ምክንያት መሆን አይገባም።
የቆሰሉ ባለ ራእዮችን ማበረታታት አለብን ።
ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም.