የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አሻግረን

ወዳጄ ሆይ !

ከታገሥህ ሁሉም ያልፋል ፣ በሕይወትህ ከወሰንህ ግን አለማለፍ ዘላለማዊ ይሆናል ። ሞት ወዳንተ መምጣቱ አይቀርምና አንተ ወደ ሞት አትሂድ ። ወደዚህ ዓለም ተመልሰህ አትመጣምና ሕይወትህን ተንከባከባት ። ብረት ብታገላብጥ ፣ ድንጋይ ብታንከባልል የቆምከው ግን በአፍንጫ እስትንፋስ ነውና በማስተዋልና በጥንቃቄ ኑር ። አለመሳካት ማለት አለመኖር ማለት አይደለም ። ራእይ አልባ ሰው ካርታውን የጣለ መንገደኛ ነው ። ውጤቱም ተንከራታች መሆን ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ሰዎች የዘሩትን ሲያጭዱ ስታይ አንተም ዛሬ እየዘራህ ነገ ደግሞ የምታጭድ መሆኑን አስብ ። የዕድሜ ጀምበር የሚጠልቀው አንዱ ባንዱ ሲስቅ ነው ። ዕድልን ዕድል ተሰጥቷቸው ካመለጣቸው ሰዎች ተምረሃት አክብረህ ያዛት ። የወደደም ይጠላል ፣ ያከበረም ያዋርዳል ። ሳትዋዥቅ የምትኖር ግን እውነት ብቻ ናት ። 

ወዳጄ ሆይ !

በየዋህነቴ ተጎዳሁ ብለህ ጨካኝ አትሁን ፣ ነገር ግን ብልህ ሁን ። የደስታ ጊዜ ረጅም ቢሆን አጭር ፣ የመከራ ጊዜ አጭር ቢሆንም ረጅም ነው ። ጓደኛን አለማመን ሁልጊዜ በሥቃይ ውስጥ መኖር ነው ። የምትሠራው የሚጠፋህ ራስህን ማድነቅ ስትጀምር ነው ። መልካም ሰውን በውድ ገዝተን በርካሽ መሸጣችን ትልቁ ኪሣራችን ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ሰው ስልክ ሲያወራ ሣንቲሜ ቆጠረ እንጂ ዕድሜዬ ቆጠረ አይልምና ከዕድሜው ይልቅ ለሣንቲም ዋጋ እንደ ሰጠ ያሳያል ። በሽተኛ በሌለበት እንፈውሳለን የሚሉ ፣ በሽተኛ ሲመጣ ግን የሚጠፉ ናቸው ። ፈውስ በፕሮግራም ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ። ማስታወቂያ የበዛበት አገልግሎት ከእውነት ይልቅ የዝና ፍቅር ያለበት ነው ። ነቢያት ስላልመጣው ዘመን ያውቁ ነበር ፤ እኛ የምንኖርበት ዘመን ተሰውሮብናል ። ሐዋርያት ሄደው ይሰብኩ ነበር ፣ እኛ ግን መጥታችሁ ተሰበኩ እንላለን ። ሰማዕታት ለክርስቶስ ፍቅር ሞቱ ፣ እኛ ግን ለጥቅማችን እንገድላለን ። ጻድቃን ጣዕመ ዓለምን ንቀው መነኑ ፣ እኛ ግን ዓለም መራራ ሆናብንም ገና እንፈልጋታለን ። ቅዱሳን ከሕግ አልፈው በትሩፋት ኖሩ ፣ እኛ ግን የታዘዝነውን መፈጸም ተስኖናል ። ደናግል መነኮሳት የክርስቶስ ሙሽሮች ሆኑ ፣ እኛ ግን በአሚናችን/በአንድ መጽናት አቅቶናል ። ሊቃውንት አህያ የማትሸከመውን መጽሐፍ በቃላቸው አጠኑ ፣ እኛ ግን በአንድ ጥቅስ ያዙኝ ልቀቁኝ እንላለን ። 

ጌታ ሆይ ከዘመን ማዕበል እባክህ አሻግረን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ