የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“አቡነ ጳውሎስ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ አባት ናቸው”

                                                                      የአርመን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ጳውሎስ፤ ሰኞ ነሐሴ 21 2004 ዓ.ም.
ምንጭ፡- ሪፖርተር
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈቱ አባት መሆናቸውን የአርመን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስታወቀች፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን 20 ዓመታት በርእሰ ሊቃነ ጳጳስነትና ፓትርያርክነት የመሩት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀብር ባለፈው ሐሙስ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲፈጸም የተገኙት የአርመን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሞቭሰስ ሞቭሰስያን እንደተናገሩት፣ ቅዱስነታቸው በዘመናዊው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍን ከፍተዋል፡፡

ከወንጌል ልዑክነት ባሻገር በልማት ተግባራት፣ በአብያተ ክርስቲያናት አንድነት (ኢኩሚኒዝም) የነበራቸው ቁርጠኝነት፣ የኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት (ኢትዮጵያ፣ አርመን፣ ግብፅ፣ ሶርያ፣ ህንድ) የሚቀራረቡበትን መድረኮች በማመቻቸት ሁነኛ ስፍራ እንዳላቸው ያመለከቱት ሊቀ ጳጳሱ፣ ሃይማኖት ለሰላምና ለመቻቻል ያለውን ጉልህ ድርሻ በተገቢው መንገድ በማሳየት ረገድ የአቡነ ጳውሎስ ሚና ጉልህ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የቅዱስነታቸው ማረፍ ለኦሬንታል ኦርቶዶክስና ለአብያተ ክርስቲያናት አንድነት እንቅስቃሴ (Ecumenical movement) ታላቅ ጉዳት መሆኑንም አክለዋል፡፡

ነፍስኄር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በርካታ ሺዎች በተገኙበት ነሐሴ 17 ቀን 2004 .. ሰባት ሰዓት ላይ ግብዓተ መሬታቸው በክብር ሲፈጸም፣ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ እንዲሁም ከዓለም ዙርያ የመጡ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃነ ጳጳሳትና መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

 

በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አገላለጽ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ኢትዮጵያን በዓለም በማስተዋወቅ በተለይም በውጭ አገር የሚገኙ ቅርሶች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ትልቅ ተግባር አከናውነዋል፡፡ ሃይማኖታዊ በዓላት በዓለም ቅርሶች እንዲመዘገቡ ትልቅ ሚናም ነበራቸው፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሕልፈተ ሕይወት ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰላምና የሃይማኖት መቻቻል ኃይሎች ሁሉ አስከፊ መርዶ እንደሆነ የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ ናቸው፡፡ቅዱስነታቸው በአገራችን በሃይማኖቶች መካከል መቻቻል እንዲጠናከር ያስተማሩ፣ የሚመሯት ቤተ ክርስቲያን በዚህ መንገድ እንድትጓዝ ከልብ የሠሩ የሃይማኖት አባት ነበሩ፤በማለትም ገልጸዋቸዋል፡፡ በአገሪቱ ጧሪና ቀባሪ ያጡትን በመደገፍና በጤናው መስክ ኤችአይቪ ኤድስን በመከላከል ረገድ ያሳዩት ተግባር በተምሳሌትነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

 

በተወካያቸው በኩል መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን የገለጿቸውለሁሉም ሰብዓዊ ፍጡራን ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ሃይማኖታዊ አባት ነበሩ፤በማለት ነበር፡፡
በሥርዓተ ቀብሩ ላይ የተገኙ የግብፅ፣ የሶርያ፣ የአርመን፣ የህንድ ኦርቶዶክስ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የግሪክ፣ የቫቲካን፣ የኖርዌይ፣ የዓለምና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበራት ተወካዮች ባደረጓቸው ንግግሮች ሐዘናቸውን የገለጹት፣ የአቡነ ጳውሎስን ዓበይት ተግባራትን በማወደስ ነው፡፡ በተለይ በቅርቡ ያረፉት የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ሺኖዳ ሣልሳዊን መንበር በተጠባባቂነት የሚመሩት ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ በአቡነ ጳውሎስ ሞት ቤተ ክርስቲያናቸው ከፍተኛ ሐዘን እንደተሰማት ገልጸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የኦሬንታልም ሆነ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ እንዲሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባዔዎች ላይ ያቀርቧቸው የነበሩት ጥልቅ ሐሳቦች የእርሳቸውን ልዕልናና በጣም አስፈላጊ አባትነትን የሚያንፀባርቁ ናቸው፤በማለትም አክለዋል፡፡

የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ጠቅላይ ጸሐፊ ሪቨረንድ (ቀሲስ) ዶክተር ኦላቭ ቲቨት ባደረጉት ንግግርምቅዱስነታቸው ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያበረከቱት አስተዋጽኦ አስታውሰው፣ በአገሮች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶች በማብረድና ሰብዓዊ ቀውስ ያጋጠማቸው አገሮች በመደገፍና በማጽናናት ከፍተኛ ሥራ የሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ በተለይ ሱዳን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር እልባት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቦታው በመገኘት ይሰጡት የነበረው እጅግ ጠቃሚ አስተያየት የሚዘነጋ አለመሆኑንም አመልክተዋል፡፡

 

የነፍስኄር ፓትርያርኩን የሕይወት ታሪክ ያነበቡት ብፁዕ አቡነ ገሪማ፣ በኤችአይቪ/ኤድስ ደዌ የተያዙት፣ የታመሙት፣ በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ የሚሰቃዩት ድኅነትን እንዲያገኙ እንዲረዱ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ለቅዱስነታቸው መታሰቢያነት በሕይወት እያሉ የተወጠነው የኤችአይቪ/ኤድስ፣ የቲቢና የካንሰር ማገገሚያና የሕክምና ማዕከል ውጥን ከግቡ እንዲደርስ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጎን በመሆን አደራውን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ነሐሴ 10 ቀን 2004 . 76 ዓመታቸው ያረፉት አቡነ ጳውሎስ ነሐሴ 16 ቀን አስከሬናቸው ከቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሚያዝያ 27 አደባባይና የድል ሐውልት ዞሮ ወደ ዘላለማዊ ማረፊያው መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ያመራው በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በካህናት፣ በምዕመናንና በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት፣ በፈረሶች በሚሳብ ሠረገላ፣ መሣሪያ ባነገቡ የፌዴራል ፖሊስ የክብር ዘብና የማርሽ ባንድ ታጅቦ ነበር፡፡
በዕለቱም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገሮች በመጡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናን በተገኙበት ሌሊቱን ጸሎተ ፍትሐትና ማሕሌት ደርሷል፡፡
በሥርዓተ ቅዳሴውም መካከል ከዳዊት መዝሙር (መዝ 64) በዜማ የተሰበከውብፁዕ ዘኀረይኮ ወዘተወከፍኮ ወዘአኅደርኮ ውስተ አዕጻዲከ” (አንተ በረድኤት የመረጥኸው በአደባባዮችህም ለማሳደር የተቀበልኸው ክቡር ምስጉን ነው) የሚለው ነው፡፡
ነሐሴ 17 ቀን በቤተ ክርስቲያኒቱ አጠራር የአቡነ ገሪማ ቀን ዕለት፣ ፊታቸው በግልጽ የሚታይበት የአስክሬን ሳጥኑነዋ ወንጌለ መንግሥት” [እነሆ የመንግሥት ወንጌል] የሚል ቃልና ምስል በሰፈረበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና የሪፐብሊኩ ዓርማ ያለበት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍኖ ነበር፡፡ የቅዱስነታቸው አስከሬን በካቴድራሉ ዓውደ ምሕረት ፊት ለፊት በሚገኘው አፀድ በሦስተኛው ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና የጎንደር ሊቀ ጳጳስ በነበሩት አቡነ ሚካኤል መካነ መቃብር መካከል ባረፈ ጊዜ ስሜቱ ልብን የሚያስረቀርቅ የግብአተ መሬት የመሰናበቻ የሐዘን ጥሩንባ ከአክሱም ጽዮን በመጡ ካህናት የመለከትና የራንጎ (ትራምፔት መሰል መሣርያ) እንዲሁም በፌዴራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ተሰምቷል፡፡  ጥቁር የሐዘን ልብስ የለበሱ ጥቁር ከረባትና ስካርፍ ያሰሩ፣ ያሸረጡ ምዕመናን ከልብ በተፍለቀለቀውና በፈላው የሐዘን ስሜት እያነቡና ሙሾ እያወረዱ ቅዱስ ፓትርያርኩን ተሰናብተዋል፡፡

 

ጥቅምት 25 ቀን 1928 .. (ኖቨምበር 5 ቀን 1935) በዘመነ ዮሐንስ በዘመኑ አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት ዓድዋ አውራጃ መደራ አባ ገሪማ ገዳም አካባቢ የተወለዱት አቡነ ጳውሎስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የቀለም ትምህርት ከመነኮሱበት አባ ገሪማና አባ ሐደራ ገዳማት እስከ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተማሩ በኋላ በአሜሪካ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ግእዝ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ላቲን፣ ግሪክና ዕብራይስጥ ቋንቋዎችን በሚገባ የሚያውቁት አቡነ ጳውሎስ፣ ከቅዱስ ቭላድሚር ኦርቶዶክስ ቴኦሎጂካል ሰሚናሪ፣ ከየልና ከፕሪስተን ዩኒቨርሲቲዎች በነገረ መለኮት የባችለር፣ የማስትሬትና የዶክትሬት ዲግሪዎችን አግኝተዋል፡፡

መስከረም 16 ቀን 1968 .. ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ የተባሉት አባ ገብረ መድኅን ገብረ ዮሐንስ፣ በመንበረ ጵጵስናቸው የቆዩት ከመንፈቅ ላነሰ ጊዜ ነው፡፡ ደርግ ከየካቲት 10 ቀን 1968 .. ጀምሮ ለሰባት ዓመታት አስሯቸው ነበር፡፡ ከእስር በኋላ ከስደት መልስ ሐምሌ 5 ቀን 1984 .. የኢትዮጵያ ፓትርያርክ በመሆን 20 ዓመት ከብሔር አቀፍ እስከ ዓለም አቀፍ ባበረከቱት አገልግሎት ከፍተኛ ዕውቅናን አግኝተዋል፡፡

በሙሉ መጠርያቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንትና የሰላም አምባሳደር ይታወቁ የነበሩት ቅዱስነታቸው፣ ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የናንሰን ሜዳሊያ፣ ከፖርቱጋልና ስፔን መንግሥታት ከፍተኛ ኒሻን፣ ከኢየሩሳሌም ቅዱስ ዮሐንስ የማልታ ክርስቲያናዊ ንቅናቄ ዓለም አቀፍ ድርጅት ታላቁን ባለክንፍ መስቀል ኒሻን ተሸላሚ ነበሩ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለዜና ሰዎች ስለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የተናገሩት አለ፡፡ሰው እንደሚለው፣ አማርኛውም ያጥረኛል እንጂ ጥሩ የቤተ ክርስቲያን አባት ናቸው፡፡ ዘና ብለን አናውቃቸውም፡፡ ገባ ብለን፣ ጠጋ ብለን አናውቃቸውም እንጂ ጥሩ አባት ነበሩ፡፡ በውጭ ሆነን ብቻ እንዲያው የምንሰማውን እንሰማለን እንጂ ጠጋ ብለን አነጋግረናቸው አናውቅም፡፡ የሩቅ ሰዎች ብቻ ሆነን ነው እንጂ፣ ጠጋ ብሎ ላነጋገራቸው ሰው የመጨረሻው ርህሩህ፣ ደግም ነበሩ፡፡ ሳሉ ይኸን አላወራንላቸውም እንጂ ደግ ነበሩ፡፡

 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለአባታቸው አፈ መምህር ገብረ ዮሐንስ ወልደ ሥላሴና ለእናታቸው ወይዘሮ አራደች ተድላ ቤተሰብ ከስምንት ልጆች ሦስተኛው ልጅ መሆናቸውን በማስታወስ የተናገሩት ታናሽ ወንድማቸው ዲያቆን ዶክተር ተወልደ መድኅን ገብረ ዮሐንስ፣ የቅዱስነታቸው ቀብር በታላቅ ክብር እንዲፈጸም መደረጉ በቤተሰባቸው ስም ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ የሽኝቱ ሥነ ሥርዓት በመስቀል አደባባይ እንዲደረግ ቤተሰቡ መጠየቁንና ባለመፈቀዱ ቅሬታ መፈጠሩን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የነፍስኄር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍትን ተከትሎ በነሐሴ 13 ቀን 2004 .. እትማችን ሰፊ ዜና ሕይወት ማውጣታችን ይታወሳል፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ