የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አባት አለን

“ከእግዚአብሔር ከአባታችን…” /1ጢሞ. 1፡2 ።/
የአዲስ ኪዳን ትልቁ ትምህርት እግዚአብሔር አባት ፣ ክርስቶስ ኢየሱስም ጌታ መሆኑን መናገር ነው ። አይሁዳውያን እግዚአብሔር ልጄ እያለ ቢጠራቸውም ስሜት ባለበት የልጅነት መንፈስ አባ ፣ አባት ብለው ሊጠሩት ተቸግረዋል ። እግዚአብሔርን በኮሬብ መልኩ ፣ በእሳትና በነጎድጓድ አስተርእዮቱ እየሳሉት ሊቀርቡት ተስኗቸዋል ። መልኩን እሳት አድርገው ለማየት ፈርተዋል ፣ ድምፁን ነጎድጓድ አድርገው እግዚአብሔር ሳይሆን ሙሴ ይናገረን ብለዋል ። በዙሪያቸው የነበሩት አሕዛብም እግዚአብሔርን በሚጠፋ ጣዖት ምሳሌ እየሳሉ ፣ ቸግሯቸው መሥዋዕት ያስቀሩ እንደሆነ እንደሚፋጅ እሳት እየቆጠሩት አባት ማለት አቅቷቸዋል ። አፈ ታሪክ የበዛበት የግሪክ ሐተታ አማልክትም ፣ የግኖስቲካውያን ፍልስፍናም አምላክ ለሚሉት የሰጠው ሥዕል ሩቅ ያለ ፣ የሰው ነገር የማይገደው አድርጎ ነው ። አዲስ ኪዳን እግዚአብሔር አባት መሆኑን ያበስራል ። ከሰው ልጆች ጋር ያለው ግንኙነትም ቤተሰባዊ መሆኑን በመናገር ብቸኝነት ቶሎ ቶሎ የሚከበውን የሰው ልጅ ያጽናናል ።

አባት መነሻ ነው ። እግዚአብሔርም መጀመሪያ ሳይኖረው መጀመሪያን የሰጠ ነው ። ዓለም የተፈጠረው ፣ ዘመን የተቆጠረው በእርሱ ነው ። አባት ከልጁ በፊት ነበረ ። እግዚአብሔርም ከዓለም በፊት ነበረ ። ልጅ ያለ አባቱ አልነበረም ፣ አባት ያለ ልጅ ነበረ ፤ ያለ ልጅም ይኖራል ። ሰውም ያለ እግዚአብሔር የኖረበት ዘመን የለም ፤ እግዚአብሔር ግን ያለ ሰው ነበረ ። የሰው ህልውና በእግዚአብሔር ህልውና ላይ ሲመሠረት የእግዚአብሔር ህልውና ግን በፍጥረት ላይ አይደገፍም ። አባት አሳቢ ነው ፣ እግዚአብሔርም ለፍጥረቱ ያስባልና አባት ይባላል ። አባት መመኪያ ነው ፣ እግዚአብሔርም የትምክሕት ወራሽ ሁኖ በሁሉም መንገድ ያስመካናል ። እንደውም ቅዱስ ትምክሕት በእግዚአብሔር ብቻ መመካት ነው ። “አባት ሳለ አጊጥ” ይባላል ፣ እግዚአብሔር ግን የማይኖርበት ዘመን የለም ። አባት ይቀጣል ፣ እግዚአብሔርም የማይታዘዙትን ወደ መታዘዝ እንዲመጡ ይቀጣል ። አባት ለልጁ ያወርሳል ፣ እግዚአብሔርም መንግሥቱን ለልጆቹ ሰጥቷል ። አባት በልጆቹ ስሙ እንዲጠራ ይፈልጋል ፣ እግዚአብሔርም ስሙ በኑሮአችን እንዲቀደስ ጠርቶናል ። አባት የጠፋ ልጁን ይጠብቃል ፣ እግዚአብሔርም የጠፉ እንዲመለሱ ፣ የሞቱ እንዲድኑ ይፈልጋል ። አባት የጠፋ ልጁ በመመለሱ ደስ ይለዋል ፣ እግዚአብሔርም በኃጢአተኞች ንስሐ ይደሰታል ።አባት ለልጁ ይሞታል ፣ እግዚአብሔር ሥጋ ለብሶ ለእኛ ሙቷል ። አባት ልጁን ከሞት በላይ ያፈቅረዋል ፣ እግዚአብሔርም ከሞት በላይ ወዶናል ።
እግዚአብሔር ከምድራዊ አባት ልዩ ነው ። የሥጋ አባቶች ምድራውያን ናቸው ፣ እግዚአብሔር ግን ሰማያዊ አባት ነው ። ምድራውያን አባቶች የሚሞቱ ናቸው ፣ እግዚአብሔር ግን የማይሞት አባት ነው ። ምድራውያን አባቶች ደም መላሽ ልጅ ይፈልጋሉ ፣ እግዚአብሔር ግን በቀልን ለእኔ ተዉ ያለ አባት ነው ። ምድራውያን አባቶች ወልደው ይክዳሉ ፣ እግዚአብሔር ግን የፈጠረውን የማይክድ ነው ። ምድራውያን አባቶች በስህተት ነው የወለድሁት ይላሉ ፣ እግዚአብሔር ግን በእውነት ቃል አስቦ የወለደን ነው ። ምድራውያን አባቶች ከሚጠፋ ዘር ነው የሚወልዱት ፣ እግዚአብሔር ግን ከማይጠፋ ዘር ወልዶናል ።
እግዚአብሔር አባታችን ነው ። አባት ያለበት ቤት ክብር አለው ። እግዚአብሔር የሚያዝዝበት ሕይወትም ክብር አለው ። አባት ያለው ልጅ ልበ ሙሉ ነው ፣ ከእግዚአብሔር የተወለደም በእምነቱ የጸና ነው ። አባት ያለው ልጅ በትግል ውስጥ ያለውን ድል ይማራል ፣ እግዚአብሔርን የተጠጋም በመንፈሳዊ ውጊያ ውስጥ ያለውን ምሥጢር ያውቃል ።
እግዚአብሔር አባት ነው ። እውነተኛ አባት ልጁን ይቅር ይላል ፣ እግዚአብሔርም ዘወትር በምሕረት ዓይን ያየናል ። አባት ተለማኝ ነው ፣ እግዚአብሔርም ለሚጠሩት ሁሉ ቸር ነው ። አባት በደጅ አገሩን ፣ በቤት ጓዳውን ያገለግላል ፤ እግዚአብሔርም የአገር ጠባቂ ፣ የቤት ሠሪ ነው ። አባት ስሙ በልጁ ሲጠራ ይኖራል ፣ እግዚአብሔርም ስሙን አትሞብናል ። አባት ያስፈራንን ያስፈራዋል ፣ እግዚአብሔርም በፈራነው ነገር ላይ የበላይ ሁኖ ይገለጣል ። አባት ቶሎ አይቀየምም ፣ እግዚአብሔርም ይታገሣል ። የአባት ኀዘን ሥር ይነቅላል ፣ የእግዚአብሔርም ቊጣ አጥንት ይሰብራል ። አባት ይመክራል ፣ እግዚአብሔርም ቀጣዩን መንገድ ያመለክታል ፣ አባት ይገሥጻል ፣ እግዚአብሔርም ላለፈው ንስሐ ይሰጣል ። አባት ያስተምራል ፣ እግዚአብሔርም ብርሃን ይሰጣል ። አባት ያቀናል ፣ እግዚአብሔርም ሕፃናትን በለጋነት ይመልሳል ።
እግዚአብሔር አባት ነው ሲባል ክፉችም ደጎችም አባቶች አይመስሉትም ። እግዚአብሔር አባት ነው ሲባል ከክፉዎች ተነጻጽሮ ፣ ከደጎች ተመሳስሎ አይደለም ። እግዚአብሔር ሰማያዊና ልዩ አባት ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ትልቅ ጸሎት አቡነ ዘበሰማያት – በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ በሉ ብሎናል ። ይህ ጸሎት እግዚአብሔርን በአባትነት ቅርበት የገለጠ ሲሆን ጸሎትም ለአንድ ንጉሥ የሚቀርብ አቤቱታ ሳይሆን ለአባት የሚቀርብ ጥያቄ መሆኑን ያስረዳል ።
ልጅ አባቱ ሁሉን እንደሚችል ያምናል ። እኛም በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት አምነን እንጸልይ ።
ከማይጠፋ ዘር የተወለደ ለሚጠፋ ዘር አይጋደልም ።
ወልደው በካዱን አባቶች ስም መጠራት አላሳፈረንም ፣ በክርስቶስ ክርስቲያን መባልም ሊያሳፍረን አይገባም ።
በአባትነቱ ፍቅር ልባችንን ያሳርፍ !!! አሜን ።
1ጢሞቴዎስ /5/
ዲአመ
ኅዳር 4 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ