“ቅዱሳን የሆኑ ነፍሳት የሚንቀሳቀሱትና የሚመሩት ልጓማቸውን በሚይዘው በክርስቶስ መንፈስ ነው።”m /አባ መቃርስ/
… መሥዋዕቱ በመጀመሪያ በካህኑ ታርዶ መሞት አለበት ። በመቀጠል ተቆራርጦ በጨው ከተቀመመ በኋላ በእሳት ይጠበሳል። ካህኑ በመጀመሪያ በጉን ካላረደውና ካልሞተ የመሥዋዕቱ በግ በጨው አይቀመምም ። ብሎም ብሎም እንደ መሥዋዕት ለአምላክ አይቀርብም ። ልክ እንደዚሁ ነፍስም እውነተኛ ሊቀ ካህን በሆነው በክርስቶስ መሠዋት (መታረድ) አለባት ። በዚህም ከራሷ የአስተሳሰብ መንገድና ክፉ ከሆነው የኃጢአት መንገድ ተለይታ መሞት ትችላለች። የመጥፎ ፍላጎት ጥርቅም የሆነው ሕይወት ማለፍ አለበት። ልክ ሥጋችን ነፍሳችን ተለይታት ስትወጣ እንደሚሞት፤ እንደ ቀድሞው እንደማይኖር፤ እንደማያዳምጥና እንደማይራመድ ሰማያዊ ሊቀ ካህናችን ክርስቶስም በኃይሉ ጸጋ ለዚህ ዓለም ያለንን ኑሮ አርዶ ሲገድለው ከዚህ በፊት ይኖርበት ለነበረው ክፉ ሕይወት ምውት ይሆናል። ከዚህ በኋላ መስማት፣ ማየት ወይም በጨለማ ኃጢአት ውስጥ ዜጋ አይሆንም። ምክንያቱም የሕይወት ጸር የነበሩት መጥፎ ስሜቶች በጸጋው ስለ ተወገዱ ነው ። ሐዋርያውም እንዲህ እያለ ይጮኻል ፡- “ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት” (ገላ.6:14)። በዚህ ዓለም በኃጢአት ጨለማ የምትኖረው ወደ ፈጣሪዋም በሞት ያልተጠቀለለችው ነፍስ ነገር ግን አሁንም በውስጧ ክፋት ማለትም የጨለማው ዓለም የክፋት ስሜት በውስጧ አለ እሱም ይገዛታል። ይህም የክርስቶስ አካል አይደለም። የብርሃንም አካል አይደለም ። ነገር ግን የጨለማው አካል ነው። ነገር ግን የብርሃን ነፍስ ማለትም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያላቸው የብርሃን አካል ናቸው።
ነገር ግን አንድ ሰው እንዲህ ሊል ይችላል ፡- ነፍስ የተፈጠረችው ከጨለማ ሳይሆን እንዴት የጨለማ አካል ነች ይባላል? ሊል ይችላል ።ተከታተለኝ በትክክልም ተረዳኝ ። አሁን የለበስከው ሹራብ ሌላ ሰው ሠርቶት አንተ እንደለበስከው ቤትህም ሌላ ሰው ገንብቶት አንተ እንደምትኖርበት እንዲሁ አዳም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሲተላለፍና ክፉውን እባብ ሲያዳምጥ ራሱን ለክፉው መንፈስ ሸጠ ። ክፉውም መንፈስ በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረችውን የአዳምን ነፍስ ክፋቱን አለበሳት። ይህንንም ሐዋርያው እንዲህ ሲል ገለጸው ፡- “አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው” (ቆላ 2፡12)። የጌታ መምጣት ዋና ዓላማም ይህ ነበር ። ይህንን ጨለማ ገፎ ማደሪያውና ቤቱ የሆነውን ሰው መመለስ ። ነፍስ ነፍስ የጨለማው ክፋት አካል ነች ያልንበት ምክንያትኃጢአት በውስጧ ስላለ ነው ።የምትኖረው በጨለማው ቁጥጥርና ለጨለማው ስለሆነ ነው ። ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ የኃጢአት አካል፣ የሞት አካል ሲል እንዲህ ብሎ ይጠራዋል ፡- “የኃጢአት ሥጋ ይሻር ዘንድ” “ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” (ሮሜ 6፥6፤ ሮሜ 7፥24)። በሌላ በኩል በእግዚአብሔር ያመነች ፣ ከኃጢአትም የዳነችና ለጨለማው ዓለም የሞተች ነፍስ የመንፈስ ቅዱስን ብርሃን እንደ ሕይወት ተቀብላለች በዚህም መንገድ በእውነት ወደ ሕይወት መጥታለች ። በዚህም ሕይወት ለዘላለም ትኖራለች። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ብርሃን ቁጥጥር ስር በመዋሏ ነው። ነፍስ የተፈጥሮ ባሕርይዋ ከእግዚአብሔር አልያም ከክፉው ጨለማ አይደለም ።ነገር ግን ተመራማሪ ፣ ውብ፣ ታላቅና ድንቅ መጠነኛ የእግዚአብሔር መልክና አርአያ ያላት ፍጡር ነች። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፏ ነበር የጨለማው ክፋት ወደ እርሷ የገባው ።
ነፍስ የእግዚአብሔር ብርሃን ኑሯት በዛው በብርሃን ጸጋ ከብርሃን ጋር አብራ ትኖራለች ።አልያም የኃጢአት ጨለማ ኖሯት ፍርድ ያገኛታል ። ከእግዚአብሔር ጋር በዘላለማዊ ብርሃን በእረፍት ውስጥ አብራ መኖር የምትሻ ነፍስ አስቀድመን እንደ ተናገርነው እውነተኛ ሊቀ ካህናት ወደሆነው ክርስቶስ መጥታ መታረድ (መሠዋት) በዚህም ለዓለም ፣ አስቀድማ ትኖርበት ለነበረው የጨለማ ክፋት ሞታ ለሌላ ማለትም መለኮታዊ ወደሆነው ሕይወት መቀየር አለባት ። ልክ አንድ ሰው የሆነ ከተማ ውስጥ ሲሞት በዚያ ከተማ ያሉትን ሰዎች ድምፃቸውን ፣ ወሬአቸውን አሊያም የሚያወጡትን ድምፅ አይሰማም ። ነገር ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሙቶ ድምፅና ልቅሶ ወደ ሌለበት ወደ ሌላ ክልል ተሸጋግሯል ። ለነፍስም ልክ እንደዚሁ ነው ። አንድ ጊዜ ከታረደች (ከተሠዋች) አስቀድማ ትኖርበት ለነበረው የክፋት ከተማ ስሜቶች ከሞተች የጨለማውን ድምፅ ፣ ከንቱ የሆነውንም ክርክርና ልቅሶ ወይም የጨለማውን መንፈስ ግርግር አትሰማም ። ነገር ግን በጎ ነገር ፣ ሰላምና የእግዚአብሔርን ብርሃን ወደ ተሞላ ከተማ ትሸጋገራለች ። በዚያም ትኖራለች። ትሰማለች የከተማውም ዜጋ ስለምትሆን ትናገራለች ፣ በጋራ ትኖራለች ፣ በዚያም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያለው መንፈሳዊ ሥራ ትሠራለች ።
ስለዚህ በእርሱ ኃይል ተሠውተን ለጨለማና ለክፉው ዓለም እንድንሞት ፣ የኃጢአትም መንፈስ ከውስጣችን እንዲጠፋ የሰማያዊውንም መንፈስ እንድንቀበልና እንድንለብሰው ፣ ከክፉውም ጨለማ ወደ ክርስቶስ ብርሃን እንድንሸጋገር በሕይወትም ለዘለዓለም እንድናርፍ እንጸልይ ። በሠረገላዎች ውድድር ላይ እንዳለው ከፊት ሆኖ የሚቀድመው የተከታዩን መንገድ እንደሚዘጋበት ወደ ፊት እንዳይጓዝ ድል እንዳይደረግ መሰናክልም እንደሚሆንበት የኃጢአት አሳብም ሰውን ይይዘዋል ። የኃጢአት አሳቦች መነሣት ከጀመሩ ነፍስን ወደ ፊት ተጉዛ ወደ እግዚአብሔር እንዳትጠጋ ድልንም ከእርሱ እንዳትወስድ መሰናክል በመሆን መንገዷን ይዘጉባታል ። ነገር ግን ጌታ የነገሠበት የነፍስንም ልጓም በእጁ የያዘበት ሁልጊዜ ድል ያደርጋል ። ምክንያቱም በጥበብ እየመራና እያስተዳደረ የነፍስን ሠረገላ ወደ ሰማያዊና ወደ ተነቃቃ መንፈስ ስለሚወስደው ነው ። እርሱ እግዚአብሔር ከክፋት ጋር አይጣላም ። ነገር ግን በራሱ ከፍ ያለ ሥልጣንና ኃይል ስላለው ድልን ለራሱ ያደርጋል ። ስለዚህ ኪሩቤል መሄድ ወደ ፈለጉበት ሳይሆን የሚጓዙት ሠረገላ ነጂው ወዳዘዛቸው ነው ። እርሱ ወደ ፈቀደው ይሄዳሉ እርሱም ይረዳቸዋል ። መጽሐፉም ፡- “በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ” (ሕዝ 1፥8) ይላል። ቅዱሳን የሆኑ ነፍሳት የሚንቀሳቀሱትና የሚመሩት ልጓማቸውን በሚይዘው በክርስቶስ መንፈስ ነው። ክንፍ ለአእዋፍ እንደ እግር እንደሚሆንላቸው ሰማያዊው የመንፈስ ብርሃን የነፍስን የአሳብ ክንፍ ይዞ መልካም በሚባለው ጎዳና ይመራታል ።
ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ስትሰሙ በእውነት እነዚህ ነገሮች በነፍሳችሁ እንዳሉ ራሳችሁን ተመልከቱ። እነዚህ በቃላት ብቻ የሚነገሩ ተራ ነገሮች ሳይሆኑ በነፍስ የሚሠሩ የእውነት ተግባሮች ናቸው ። እንደ እነዚህ ያሉት በጎ መንፈሳዊ በረከቶች ከሌሉህ ለመንግሥተ ሰማያት ሙት ስለምትሆን ሁልጊዜ ንዴት ፣ ኀዘንና ችግር ይኖርብሃል ። ይህን እውነተኛ ሕይወትም እንዲሰጥህ እንደ በሽተኛ ሰው ወደ ጌታ አልቅስ ፤ በእምነትም ለምን ። እግዚአብሔር የእኛ የሆነውን ይህንን አካል (ሥጋ) ሲፈጥረው ከራሱ (ሥጋ) ባሕርይ ወይም አካላችን በራሱ ሕይወት እንዲኖረው አድርጎ አልፈጠረውም ። ሰውን ሲፈጥር እርቃኑን አድርጎ በመፈጠር ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ከእርሱ ውጭ ካሉ ነገሮች (ከተፈጥሮ) እንዲያገኝ አደረገው ። ይህም አካላችን ከራሱ ሌላ (ከተፈጥሮ) ካሉ ነገሮች ውጪ መኖር አይሆንለትም ። ማለትም ከምግብ ፣ ከመጠጥና ከልብስ ተለይቶ መኖር አይችልም ። ከውጪው አንዳች ሳይወስድ በራሱ ተፈጥር ብቻ መኖር ከሞከረ ይሞታል ፣ ይጠፋል ። ይህ ነገር በተመሳሳይ መልኩ ለነፍስም ይሠራል ። በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረች ብትሆንም የመለኮት ብርሃን የላትም። እርሱም ከእግዚአብሔር እንጂ በራሷም ሕይወት እንዳይኖራት ወድዶ ስለ ጠባይዋ ወስኗል ። የእርሱ መንፈስ የእርሱ ብርሃን ለነፍስ እውነተኛ የሆነ ሕይወት ፣ መንፈሳዊ መጠጥ ፣ መንፈሳዊ ምግብና ሰማያዊ ልብስ በመሆን እውነተኛ ሕይወትን ሰጥቷታል ።
እስካሁን የአካላችን ሕይወት በራሱ እንዳልሆነ ነገር ግን ከውጭ ማለትም ከመሬት (ከተፈጥሮ) ሁኖ ውጫዊ ከሆኑት ነገሮች ተለይቶ ሕይወት እንደሌለው አይተናል ። ልክ እንደዚሁ ነፍስም “በሕያዋን ምድር” ካልተወለደች ከሕያዋንም ምድር መንፈሳዊውን ምግብ ተመግባ ወደ ጌታ ካላደገች ከቃላት በላይ በሆነው መለኮታዊ ውበትም ካልተዋበች ነፍስ እነዚህን ካልተመገበች በደስታና በዕረፍት በራሷ መኖር አትችልም ። መለኮታዊ ባሕርይ እንዲህ የሚሉትን የሕይወት እንጀራ ይዟል ። እኔ የሕይወት እንጀራ፣ የሕይወት ውኃ ነኝ (ዮሐ 6፥35፤ 4፥10) ፤ የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኘው ወይን (መዝ 104፥15)፤ የደስታ ዘይት (መዝ 45፥7) ሁሉም የሰማያዊውም መንፈስ የምግብ ዓይነቶችንና ከእግዚአብሔር የሚመጣውን ሰማያዊ ውብ ብርሃን። በእነዚህ ምግቦች የነፍስ ዘላለማዊነት ይቀጥላል። አካል (ሥጋ) በራሱ ተፈጥሮ መደገፍ ሲጀምር ወዮለት። ነፍስም በሌላ ነገር ሳይሆን በራሱ ተፈጥሮ ሲቆም ፣ መታመኑንም በራሱ ሥራ ላይ ሲያደርግ ፣ ከእግዚአብሔር መንፈስም ጋር ሕብረት ካላደረገ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ዘላለማዊ ሕይወት ሳያገኝ ይሞታልና ወዮለት ። አንድ ሰው ታሞ ምንም ዓይነት ምግብ አልወስድም ሲል ሰዎች በሕይወት ስለ መኖሩ ተስፋ ይቆርጡበታል ። ዘመዶቹና ጓደኞቹ ሁሉ በዕንባ ይሞላሉ ። በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔርና መላእክቱም ነፍስ ከመንፈስ በሚገኘው ሰማያዊ ምግብ ሳትመገብ ወደማያልፈውም ሕይወት ሳትመጣ ስትቀር ያለቅሳሉ ። እነዚህ ነገሮች አስቀድሜ እንደ ተናገርኩት ዝም ብለው የሚነገሩ ተራ ቃላት ሳይሆኑ የመንፈሳዊ ሕይወት ሥራ ፣ በነፍስ ላይ የተሠራ ትክክለኛና የእውነት ሥራዎች ናቸው ።
ከእንግዲህ የእግዚአብሔር ዙፋን ከሆንህ ፣ ሰማያዊውም መሪ ከከተመብህ ፣ ሙሉ ነፍስህም ዓይን ከሆነች፣ ነፍስህም ሙሉ ብርሃን ከሆነች፣ ከመንፈስ ቅዱስም ምግብ ከተመገብህ ፣ ከሕይወት ውሃም ከጠጣህ ፣ ከቃላት በላይ ውብ የሆነውንም የብርሃን ልብስ ከለበስህ ፣ ውስጣዊ ማንነትህም የቆመው በእነዚህ ነገሮች ህልውና ከሆነ ሕይወትህ ዘላለማዊ እንደሆነ ነፍስህም በጌታ ዕረፍት እየኖረች እንደሆነ እወቅ ። እነዚህን ስጦታዎች ከጌታ እንደ ተቀበልካቸውና በእውነትም ከተጠቀምህባቸው እውነተኛ ሕይወት እንደምትኖር አስተውል ። ነገር ግን እነዚህ ጸጋዎች እንደሌሉህ ካወቅህ ዘላለማዊውንና ሰማያዊውን ስጦታ አላገኘህምና እያዘንህ በፀፀት አልቅስ ። አንተ ጎስቋላ ችግር ውስጥ ስለሆንክ ጌታን ሌት ተቀን ለምነው ። ምክንያቱም አሰቃቂ በሆነው የኃጢአት ድህነት ወድቀሃልና ። ምክንያቱም አንድ በጽኑ የተቸገረ ጌታንም ሁልጊዜ የሚጠይቅና የሚፈልግ ሰው ወዲያውኑ ወይም ቆየት ብሎ ቤዛነትንና ሰማያዊ ሀብቶችን ያገኛል ። ይህ ማለት ጌታ ስለ ክፉው ዳኛና ስለ መበለቷ ባስተማረው ትምህርት መጨረሻ ላይ እንዳለው መደምደሚያ ነው። “እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል” (ሉቃ 17፥7-8)። ለእርሱ ክብርና ኃይል ይሁን። ለዘላለሙ አሜን።