የጨለማው ገዥና የክፋት ንጉሥ የሆነው የሰውን ልጅ ምርኮኛ አድርጎ ልክ አንድ ሰው ሌላውን ልብስ እንደሚያለብሰው ነፍሱን በጨለማ ኃይል ከቦ ጨለማ አለበሳት። አንድ ልዑል ንጉሥ ይሆን ዘንድ ከእግር እስከ ራሱ ንጉሣዊ ልብስ እንደሚለብስ የክፋት ንጉሥ ነፍስን ኃጢአት አለበሳት ። ይህ የክፋት ንጉሥ ነፍስን አረከሳት ። በመንግሥቱ ግዛት ምርኮኛ አደረጋት ። አንዳችም ክፍሏን ነጻ ሳያደርግ አሳቧን ፣ ማስተዋሏን ፣ አካሏን ፣ አንዳች ሳያስቀር የጨለማ ካባ አለበሰው ። አንድ ሰው ሲታመም ሙሉ ማንነቱ ይታመማል እንጂ ተለይቶ አንድ አካሉ ብቻ ታመመ እንደማይባል ነፍስ ደስታን በማጣትና በኃጢአት ሁለንተናዋ ታመመ ። ይህ ክፉ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሰው አካል የሆነችውን ነፍስ የእርሱ በሆነው ኃጢአት ሲያለብሳት የሰው ግዙፍ አካል (ሥጋ) ለሥቃይና ለመበስበስ እጁን ሰጠ ።
ሐዋርያው ፡- “አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና” (ቆላ 3:11) ሲል ሙሉ ማንነትን ለመግለጽ ነው ። ይህም አሮጌውን ዓይን በአዲስ ዓይን ፣ አሮጌውን ጆሮ በአዲስ ጆሮ ፣ አሮጌውን እጅ በአዲስ እጅ ፣ አሮጌውን እግር በአዲስ እግር ፣ አሮጌውን ልብ በአዲስ ልብ ሁሉን በአዲስ መተካት ነው ። የክፋት ንጉሥ ሙሉውን የሰው ማንነት ሥጋውንና ነፍሱን በክሎ ከነበረው ክብር በማውረድ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረውን ሰው “አሮጌ ማንነት” የተበከለ ፣ ንጹሕ ያልሆነ ፣ ለእግዚአብሔር ሕግ የማይገዛ ማንነት አለበሰው ። ይህን ያደረገበት ምክንያት ሰው እግዚአብሔር እንዳቀደለት ማየትን ትቶ በተሳሳተ መንገድ እንዲያይ ፣ በተሳሳተ መንገድ እንዲሰማ ፣ ወደ ክፋት የሚፋጠኑ እግሮች ፣ ኃጢአትን የሚሠሩ እጆች ፣ ርኩሰትን የሚያመነጭ ልቡና እንዲኖረው ነው ።
ስለዚህ ይህን አሮጌ ማንነት ከእኛ ይገፈው ዘንድ እግዚአብሔርን እንለምነው። ምክንያቱ እሱ ብቻ ነውና ኃጢአታችንን ማስወገድ የሚችለው ። እኛን የማረከን በመንግሥቱም የተቆጣጠረንና ያሰረን የጨለማው ንጉሥ እጅግ ከእኛ የሚልቅ ኃይል አለው ። እርሱን ማሸነፍ በእኛ አቅም የሚሆን አይደለም ። ነገር ግን እርሱ እግዚአብሔር ከዚህ መራራ ባርነት ነጻ እንደሚያወጣን ቃል ገብቶልናል ። ፀሐይ ከርራ በምትወጣበት ኃይለኛ ነፋስም ሲነፍስ ፀሐይዋም ነፋሱም የየራሳቸው አካልና ባሕርይ አላቸው ። ነገር ግን እግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ማንም ነፋሱንና የፀሐዩን ሙቀት ሊለይ የሚቻለው የለም። እግዚአብሔር ብቻ ነው ነፋሱን ከመንፈስ ሊያቆመው የሚችለው ። ልክ እንደ ፀሐይና ነፋስ ኃጢአት ከነፍስ ጋር ተዋህዷል ። ነገር ግን ሁለቱም የየራሳቸው ባሕርይ አላቸው ። ነፍስን ከኃጢአት መለየት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው ። እግዚአብሔር ይህንን በነፍስና በሥጋ ላይ ያደረውን ክፉ ነፋስ (ኃጢአት) ካላስቆመውና ካላስቀረው በስተቀር በማንም ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ነው ።
አንድ ሰው ወፍ ስትበር አይቶ መብረርን ቢመኝ አይሆንለትም ። ምክንያቱም ክንፍ ስለሌለው መብረር አይችልም ። ሰውም ከኃጢአት የመላቀቅና የመንጻት ፣ ያለ ነቀፋ የመሆን ፣ ያለ መቆሸሽ ፣ ያለ ርግማን የመሆን በተቃራኒው ሁል ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የመሆን ፈቃድ (ሮሜ 7፡18) እና ፍላጎት አለው ። ኃይል ግን የለውም ። ስለዚህ እግዚአብሔር የርግብን ክንፍ (መዝ 54(55)፡6) እንዲሰጠን እንለምነው። ወደ እርሱ እንድንበር ወደ ዕረፍታችንም እንድንደርስ ። እርሱም ክፉውን ነፋስ ከነፍሳችንና ከሥጋችን ይለየዋል ። ይህም ክፉ ነፋስ በሥጋችንና በነፍሳችን ያደረው ኃጢአት ነው ። ይህንንም ኃጢአት ከእኛ መለየት እሱ ብቻ እንጂ ማንም የሚችለው አይደለም ። መጽሐፍ ፡- “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ 1፡29) ይላል ። እርሱ ብቻ ለሚያምኑት ምሕረትን አሳይቷቸዋል ። ከኃጢአታቸው ዋጅቶ ሁልጊዜ ለሚጠብቁት ፣ ተስፋ ለሚያደርጉት ፣ ሳያቋርጡ ለሚፈልጉት ድንቅ የሆነውን መዳን ሠራ።
በሚያስፈራ የጨለማ ምሽት ነፋስ እንደሚነፍስ አትክልቱንና ዛፎቹን እንደሚወዘውዝና እንደሚያውክ ፤ የሰው ልጅም በጨለማው ኃይል ሲወድቅ ኃይለኛ ሆኖ በሚነፍሰው የኃጢአት ማዕበል ታውኳል ፣ ተንቀጥቅጧል ። በማንነቱ ሁሉ ውስጥ ነፍሱ ፣ አሳቡ፣ መረዳቱ ፣ የሰውነቱ ብልቶች ሁሉ ታውከዋል ።ከነፍሱ አልያም ከአካሉ ከኃጢአት ነጻ የሆነና በኃጢአት ያልተደፈረ ክፍል የለም ። በተመሳሳይም ደስ የሚል የብርሃን ቀን አለ ። በዚህ ቀን መለኮታዊ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ነፋስ ይነፍሳል ። ይህም ነፋስ በጌታ ቀን (ሥራ 2፡20) በጌታ ቀን ያሉትን ነፍሳት ብርታት ይሰጣቸዋል ።አዲስም ያደረጋቸዋል ። ይህ ነፋስ የነፍስ ውስጣዊ ማንነቷና ተምኔቷ ባለበት አሳቧ ውስጥ ይሰራጫል። ይህ ቅዱስ ነፋስ ነፍስ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የግዙፉ የሥጋ ማንነት ውስጥ ዘልቆ በመግባት ሥጋና ነፍስን በማደስ ከቃላት በላይ በሆነው በመለኮታዊ ዕረፍት ያሳርፋቸዋል ። ሐዋርያው ፡- “ሁላችን የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁ። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም” (1ኛ ተሰ 5፡5) ሲል እየገለጸ ያለው ይህንን ነው ።
በጨለማው መንግሥት የነበረው አሮጌው ሰው ሙሉ በሙሉ አሮጌ ማንነት ያለው ነው ። ይህ አሮጌ ሰው የጨለማውን መንግሥት ልብስ ለብሷል ። ይህ ልብስ የእግዚአብሔርን ስም የሚሳደብ ነው ። በተጨማሪ ይህ ልብስ ያለማመን ፣ የግድ የለሽነት ፣ የግብዝነት ፣ የኩራት ፣ የንፉግነት ፣ የዝሙት ፣ ንጹሕ ያለ መሆን ባጠቃላይ ፀያፍ የሆኑ ማንነቶች ልብስ ነው ። ስለዚህ እዚህ ጋ ከመሬት የሆነው አሮጌውን ሰው ገፈው የጣሉት ፣ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ የጨለማውን መንግሥት ልብስ ያወለቀላቸው ሰዎች አዲሱንና ከሰማይ የሆነውን ሰው ለብሰውታል ። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ይህም ማለት ከላይ እንዳየነው በተመሳሳይ መልኩ አዲሱን ሰው መልበስ ማለት ዓይንን በአዲስ ዓይን ፣ ጆሮን በአዲስ ጆሮ ፣ ልብን በአዲስ ልብ በመቀየር ነው ።ይህም ሙሉ በሙሉ ንጹሕ ለመሆንና አዲሱን ሰማያዊ ሰው ለመልበስ ነው ።
ጌታ እርሱን የሚጠብቁትን ነፍሶች ከቃላት በላይ የሆነውን የመንግሥቱን ብርሃን ያለብሳቸዋል ። ይህንን ብቻ አይደለም የእምነት ፣ የተስፋ ፣ የልግስና ፣ የሰላም ፣ የደግነት ፣ የርኅራኄ ሌሎችንም ሕያው የሆኑትን ልብሶች ያለብሳቸዋል ። እግዚአብሔር በባሕርይው መገለጫዎች ፍቅር፣ ሰላም ፣ ሐሴት ፣ ርኅራኄ ፣ የዋህነት … እንደ ሆነው አዲሱም ሰው በጸጋው እንደ እርሱ ይሆናል ። የጨለማው መንግሥትና ኃጢአት እስከ ትንሣኤ ድረስ በኃጢአተኛው ነፍስ ውስጥ ተደብቀው ይኖራሉ ። ከትንሣኤው በኋላ የኃጢአተኛው አካል አሁን በነፍስ ውስጥ በተደበቀው ጨለማ ትዋጣለች ። ልክ እንደዚሁ የብርሃን መንግሥት ሰማያዊ መልክ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ አሁን ረቂቅ በሆነ መንገድ ለነፍስ አብርሆትን ሰጥቷታል ።በጻድቁም ነፍስ ይነግሣል ።ነገር ግን ከሰው ዓይን (ከሥጋዊ ዓይን) የተሰወረ ነው ። ክርስቶስ በነፍስ ዓይን ብቻ ነው የሚታየው ። ይህም የሚሆነው እስከ ትንሣኤ ድረስ ነው ። ከትንሣኤ በኋላ ግን የሰው ሰውነት በጌታ ብርሃን ይዋጣል፤ ይከብራል (ፊል. 3፡21) ። ይህም ብርሃን አሁን በጻድቃን ነፍስ ያለ ብርሃን ነው ። ሥጋችንም የክርስቶስን መንግሥት ከተቀበለችው ዘላለማዊ ብርሃን ከበራላትና በዘላለማዊ ብርሃን ካረፈችው ነፍሳችን ጋር አብሮ ይነግሣል።