ክርስቲያኖች ሰማያዊውን ስጦታ ከእግዚአብሔርና ከመላእክት እንዲቀበሉ በዚህ ዓለም ያላቸውን ሩጫ በማስተዋልና በጥንቃቄ መሮጥ እንዳለባቸው የተሰጠ ስብከት
1. እኛ የክርስትና ሕይወትን በጥልቀት መፈጸም የምንፈልግ ሰዎች ከሁሉም ነገር በፊት ባለን አቅም ሁሉ የመለየት አቅም ያለውን የነፍሳችንን ክፍል መንከባከብ አለብን ። በዚህም ጥሩውን ከመጥፎ በእርግጠኝነት የመለየትና ያልተበላሸውን ንጹሕ ተፈጥሮ እንድናገኝ ይረዳናል ። ይህም ሕግ ሳናፈርስ ታማኝና ግልጽ ሁነን መልካም ነገርን መፈጸም ያስችለናል ። ይህንን የመለየት ችሎታ እንደ ዓይን አድርገን ከኃጢአት አሳቦች ጋር ኅብረት ከማድረግ ነጻ እንወጣለን ። በዚህም ለጌታ የተገባን እንድንሆን የሚያደርጉን ሰማያዊ ስጦታዎች ይሰጡናል ። ከሚታየው ዓለም ማሳያ እንውሰድ ። በነፍስና ሥጋ ፤ በግዙፉ ሥጋ ክፍሎችና በነፍስ ክፍሎች ፤ በስሜት ሕዋሶቻችንና በማይታየው ስሜታችን መካከል መመሳሰል አለ ።
2. ሰውነት የሚመራበት ዓይን አለው ። ዓይን በማየት ሙሉ ሰውነታችንን ቀጥ ብሎ እንዲጓዝ ያደርገዋል ። እስኪ አንድ ረግረግና እሾህ በሞላበት ጫካ ውስጥ የሚጓዝ ሰው አስቡ ። ሰውየው በሚጓዝበት ጊዜ እሳት ተነሣ ፤ በሚረግጠው መሬት ላይም የተሰኩ ጎራዴዎች አሉ ። መንገዱ ላይም ብዙ ኩሬዎችና ገደሎች አሉ ። ፈጣን የሆነው በትኩረትና በፍጥነት የሚሄደው ተጓዥ በዓይኑ መሪነት በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎች በትኩረት ያልፋቸዋል ። ልብሱ በእሾህና በቆንጥር እንዳይበጨቅ ፤ በረግረጉ እንዳይቆሽሽ በጎራዴውም እንዳይቀደድ በእጁና በእግሩ ይሰበስበዋል። ሁሉንም መንገዶች ዓይኑ ይመራዋል ። የዓይኑ ብርሃን ወደ ገደሉ እንዳይወድቅ ፤ ውሃው ውስጥ እንዳይሰጥም ወይም በሌላ አደጋዎች እንዳይጎዳ ይጠብቀዋል ። ጠንቃቃና ንቁ የሆነው ሰውዬ ልብሱንም በመሰብሰብ በዓይኑ መሪነት ራሱን ከአደጋ ይጠብቃል ። የለበሰውንም ልብስም ከመቀደድና ከመቃጠል ያድናል ። ነገር ግን አንድ ሰው እንዲህ ባለ ቦታ ሲያልፍ ሰነፍ ፤ ግድ የለሽ ፤ ገልጃጃና ፈዛዛ ከሆነ ልብሱን ሰብስቦ መያዝ ስለማይችል ልብሱ እየዋለለ በእሾሁና በቁጥቋጦው ይቀደዳል ። አልያም በእሳት ይቃጠላል ። ወይም በየቦታው በተሰኩ ጎራዴዎች ይበጫጨቃል ። በረግረጉም ይቆሽሻል ። በአንድም በሌላም መንገድ ሰውየው ጥሩ ልብሱን በፍጥነት ያበላሸዋል ። በስንፍናውና በግዴለሽነቱ ዓይኑ የሚያሳየውን በአግባቡ ማድረግ ካልቻለ ራሱ ወደ ገደል ይወድቃል ። አሊያም ውኃ ውስጥ ይሰጥማል ።
3. ልክ እንደዚሁ በሥጋ ልብስነት የምትሸፈነው ነፍስ ራሷን የምትመራበት ነገሮችን የመለየት ችሎታ ያለው ክፍል አላት ። ነፍስ ከግዙፉ ሥጋ ጋር የሕይወት እሾሆች ፤ ቁጥቋጦዎች፤ ገደሎች፤ ረግረጎች በተባሉት በዚህ ዓለም ምኞቶችና ፍላጎቶች መካከል ስታልፍ ራሷንና ልብስ የሆናትን ሥጋ በሁሉም በኩል በንቃትና በማስተዋል በማክበርና ቅንነት መሰብሰብ አለባት ። ራሷንም እሾህና ቁጥቋጦ ከሆነው ከዓለማዊ አሳብ ፣ ከምድራዊ ረብሻና ከምኞት እሳት መጠበቅ አለባት ። በዚህ ሁኔታ ከለበሰ/ከተጠበቀ ዓይንን ክፉ ከማየት ፣ ጆሮን ሐሜት ከመስማት ፣ እጅና እግርን ከመጥፎ ሥራ ይጠብቃል ። ነፍስ የሰውነትን ክፍሎች ከጥፍር እስከ ፀጉር ክፉና አሳፋሪ ከሆነ ድምፅ ፣ ብልግና ከሆኑ ቃላት ፣ ዓለማዊና ክፉ ከሆነ ምኞት የመጠበቅና የመከልከል ፈቃድ አላት።
4. ለነፍስ ራሷን ከርኩስ የኑሮ ዘይቤ የልብንም አሳብ ከዓለማዊነት የኑሮ ዘይቤ እንዲላቀቅ ታደርጋለች ። በዚህም በመጣርና ከቀድሞ በበለጠ በመታገል በታላቅ ማስተዋልም የሰውነት ክፍሎችን በሁሉም አቅጣጫ ከክፉ ነገር በመግታት መልካም የሆነውን ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ልብስ ሳይቀደድ ፣ ሳይቃጠልና ሳይቆሽሽ እንዲኖር ይጠብቀዋል ። ነፍስ ራሷ በማወቅ ፣ ክፉን ከመልካም በሚለይ ፈቃድዋና በእግዚአብሔር ኃይል በእርሱም ታላቅነት ባላት ብርታት ሁሉ ራሷን አንድ አድርጋ ከዓለማዊ ምኞት ታሸሻለች ። በዚህም ምክንያት በጌታ እየታገዘች ከተነገሩት መቅሰፍቶች ትድናለች ። ጌታ ማንኛውንም ሰው ለሕይወት ምኞትና ሁከት ፣ ለቁሳዊ ሀብት ፍላጎት ፣ ለዓለማዊ ፍቅር ፣ በከንቱ አሳብ መዋጥ ላይ በጥንካሬ ጀርባውን አዙሮ ሲያየው የጸጋውን እርዳታ ይሰጠዋል። ያቺ ነፍስም እንዳትወድቅ ይጠብቃታል ። ድንቅ በሆነ ሁኔታ “ክፉ በሆነው በአሁኑ ዓለም” (ገላ 1፥4) ውስጥ በማለፍ ነፍስ ከእግዚአብሔርና ከመላእክቱ ሰማያዊውን ስጦታ ትቀበላለች ። ምክንያቱም የራሷንና የግዙፉን ሥጋ ልብስ ስለ ጠበቀች፣ በተሰጣት ኃይልም እስካለች ከዓለማዊ ምኞት ስላመለጠችና ጌታ እገዛ የዚህ ዓለም ሩጫዋን በሚደንቅ ሁኔታ ስለፈጸመች ነው ።
5. ነገር ግን አንድ ሰው ሕይወቱን ቸልተኛና ግድ የለሽ ሁኖ ያለ ሥርዓትና ማስተዋል ራሱን ለማስደሰት ከኖረ ከዚህ ዓለም ምኞት ራሱን ሊያርቅ ሆነ ጌታን ብቻ ሊፈልግ አይችልም። በምኞቶቹም ምክንያት በዚህ ዓለም እሾህ ይወጋል ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጠው የአካሉም ልብስ በምኞት እሳት እዚህም እዚያም ይቦጫጨቃል። እንዲህ ያለችው ነፍስ የተሰጣትን ልብስ በንጽሕና ስላልጠበቀች ነገር ግን በዚህ ዓለም ማታለል ስላሳደፈችው በፍርድ ቀን በራስ በመተማመን አትቆምም ። በዚህም ምክንያት ከመንግሥተ ሰማያት ትጣላለች ። ራሱን በፈቃዱ ለዚህ ዓለም የሰጠውን ፣ በምኞቱም የተታለለውንና ከእውነተኛ መንገድ በቁሳዊ ፍቅር የወጣውን ሰው እግዚአብሔር ምን ያደርገዋል ? እግዚአብሔር የሚረዳው ራሱን ከቁሳዊ ደስታ ያራቀውን ፣ ድሮ የነበረውን ጥፋቱን የተወውን፣ ሁልጊዜም አሳቡን ወደ ጌታ የሚያደርገውንና ሲፈልግም ሳይፈልግም የፈለገው ወይም ያልፈለገው አሳብ ቢሆንም ራስን ክዶ ጌታን ብቻ የሚፈልግን ሰው ነው። ይህ ጌታ ከእቅፉ ሥር የሚያደርገው ሰው በሁሉም አቅጣጫ ከቁሳዊ ዓለም ወጥመድና ጥልፍልፍ ራሱን የሚጠብቅ ፣ ደኅንነቱንም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚፈጽም (ፊልጵ 2፥12) ፤ የዚህን ዓለም ወጥመዶች መሰናክሎችንና ምኞቶችን በጥንቃቄ የሚያልፍ በጌታ ቸርነት በጸጋው እንደሚድን ተስፋ የሚያደርግ ነው ።
6. እነዚያ ልባም የሆኑትን አምስት ደናግላን እስኪ አስቧቸው ። በልባቸው ማጠራቀሚያ ውስጥ የራሳቸው ተፈጥሮ ያልነበረውን ዘይት ማለትም ከላይ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ይዘው ከሙሽራው ጋር ወደ ሰማያዊው ሰርግ ቤት መግባት ችለዋል ። ነገር ግን እነዚያ ባላቸው ነገር የረኩ ፣ ራሳቸውን ያላዩትና በሥጋ ሳሉ በልባቸው ማጠራቀሚያ “የደስታ ዘይትን” (መዝ45፥7) ለመቀበል ባተሌ የሆኑትን ፣ በስንፍና በቸልተኝነትና በግድ የለሽነት የተኙትን ፣ በድንቁርናና በውሸት/ሕልም ጽድቅ ውስጥ ያሉትን ፣ ሙሽራውን ማስደሰት ስላልቻሉ ከሰማያዊው የሰርግ አዳራሽ ውጪ የተጣሉትን ፣ ሰነፍ የሆኑ አምስት ደናግላን ደግሞ አስቧቸው ። በዚህ ዓለም ስሜትና ፍቅር ተይዘው ሙሉና ጥልቅ የሆነውን ፍቅራቸውን ለሰማያዊው ሙሽራ አልሰጡምና ዘይት አልተሰጣቸውም ። ከራሳቸው የማድረግ አቅም በላይ የሆነውን በመንፈስ ቅዱስ መቀደስ የሚፈልጉ ነፍሳት ያላቸውን ፍቅር ሁሉ ለጌታ ይሰጣሉ ፤ ሲራመዱ ይጸልያሉ ፣ አሳባቸውንና ፊታቸውን ከሁሉም ዓለማዊ ነገር በመመለሳቸው ሰማያዊ የሆነውን የጸጋ ዘይት ለመቀበል የተገቡ ሁነው ተገኝተዋል። ሰማያዊውንም ሙሽራ ሳያንቀላፉ በመጠበቅ ፍጹም ደስ አሰኝተውታል ። ባላቸው ነገር ብቻ የሚደሰቱ ነፍሳት ግን በዚህ ዓለም አሳብ ውስጥ ይማቅቃሉ ። አሳባቸውም ስለዚህ ዓለም ብቻ ነው ። በራሳቸው ግምት በሙሽራው ሰርግ ቤት ያሉና በሥጋቸውም ያጌጡ ይመስላቸዋል ። ነገር ግን ከመንፈስ አልተወለዱም ፣ የደስታን ዘይትም አልተቀበሉም ።
7. አምስቱ የነፍስ ምክንያታዊ ሕዋሶች ከላይ ጸጋን ከተቀበሉና በመንፈስ ቅዱስ ከተቀደሱ ከላይ የጥበብን ጸጋ ተቀብለው ልባም ደናግል ይሆናሉ ። ነገር ግን በተፈጥሮ በተቀበሉት ነገር ብቻ ከረኩ ሰነፎችና የዚህ ዓለም ልጆች ይሆናል። ምንም እንኳን በውጫዊ መልክና በማስመሰል በሃሳባቸውም የዚህን ዓለም መንፈስ ያወለቁ ቢመስላቸውም አውልቀው አልጣሉትም ፤ ነገር ግን ራሳቸውን እያታለሉ ለሙሽራው ሙሽሪት አድርገው ያቀርባሉ ። ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለጌታ የሰጡ ነፍሳት አሳባቸው ፣ ጸሎታቸው ፣ እርምጃቸው ሁሉ የጌታን ፍቅር የተከተለ ነው ። ልክ እንደዚሁ ከዚህ ዓለም ፍቅር ጋር የተዛመዱና በዚህ ዓለም ፍቅር የተወሰኑ ፤ ቆይታቸውንም በዚህ ዓለም ለማድረግ የፈቀዱ ነፍሳት የሚኖሩትና የሚራመዱት አእምሮአቸውም የሚኖረው እዚሁ ነው። በዚህም ምክንያት መልካም ከሆነው ከመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ጋር መስማማት አይችሉም። ወደ ሰማያዊው የሰርግ አዳራሽ ለመግባትና ዘላለማዊ ድኅነት ለማግኘት ከእኛ ውጪ የሆነው ሰማያዊው ጸጋ ከእኛ ባሕርይ ጋር መዋሐድና መጣመር አለበት ።
8. የእኛ ተፈጥሮ ካልሆኑት ውስጥ አንዱ አደገኛ የሆነውን የኃጢአት ስሜት በአንዱ ሰው አለመታዘዝ በኩል ተቀብለናል ። ይህም ኃጢአት በረዥም ልምድና በተፈጥሮ ዝንባሌ ተፈጥሮአችን መስሏል ። ይህ ከእኛ ተፈጥሮ ውጪ የሆነው ነገር መወገድ ያለበት የቀድሞውም ንጽሕና መመለስ ያለበት ከእኛ ተፈጥሮ ውጪ በሆነው በሰማያዊ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው ። ከሰማይ የሆነውን የመንፈስ ቅዱስ ፍቅር በጸሎት ፣ በልመና ፣ በምልጃና በእምነት አሁን ካልተቀበልን ለዓለማዊነትም ጀርባችንን ሰጥተን በክፋት የተበከለው ተፈጥሮአችንም ወደ ጌታ ፍቅር ካልተሳበና በመንፈስ ቅዱስ ፍቅርም ካልተቀደሰ ፤ እስከ መጨረሻውም እንዳንወድቅ ተግተን ካልተጋደልን ፣ በሕግጋቱም መሠረት ካልተጓዝን ሰማያዊውን መንግሥት መውረስ አንችልም ።
9. ባለኝ አቅም ሁሉ ጥልቅና ስውር የሆኑ ቃላትን ልናገር ስለሆነ በንቃት አዳምጡኝ ። የማይወሰነው ፣ የማይደረስበት ያልተፈጠረው እግዚአብሔር በማይወሰነውና ከአሳባችን በላይ በሆነው ቸርነቱ ሥጋ ለብሶ ወይም እንዲህ ማለት እችላለሁ የሚታዩት ፍጡራኑ ከመለኮታዊ ሕይወት ተካፋይ እንዲሆኑ እነርሱን ከእርሱ ጋር ለማዋሐድ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከማይደረስበት ክብር ራሱን አዋረደ ። ነፍስ ትሑን መላእክት አሊያም ሰይጣን ዓይነታቸው ይለያይ እንጂ አካል አላቸው ። እንደ እኛ እንደሚዳሰሰው ግዙፍ አካል ባይሆንም እነዚህ አካላት እንደየ ረቂቅነታቸው የራሳቸው የሆነ ማንነት ፣ ፀባይና መልክ አላቸው ። ከዚህም በተጨማሪ በጣም ረቂቅ የሆነችው ነፍስ የምታይበት ዓይን ፣ የምትሰማበት ጆሮ ፣ የምትናገርበት ምላስ ፣ የምትዳስስበት እጅና ሁሉም አካላት ያላት ሲሆን የሕይወት አገልግሎትንም በእነርሱ ትፈጽማለች ።
10. ልክ እንደዚሁ የማይወሰነውና የማይደረስበት ከመታወቅ በላይ በሆነ ክብር የሚኖረው እግዚአብሔር ራሱን ወስኖ ሥጋን ተዋሐደ። ለሰው ባለው ርኅራኄና ፍቅር ሥጋችንን ነሥቶ ተዋሐደው ። ቅዱሳን ከሆኑ ፣ እምነት ካላቸውና ደስ ከሚያሰኙት ነፍሳት ጋር ራሱን አዋሕዶ ከእነርሱ ጋር አንድ መንፈስ ሆነ ። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ፡- “ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው” (1ቆሮ 6፥17)። ይህንንም እንዲህ ማስቀመጥ ይቻላል ። ነፍስ ብቁና ፈቃደኛ ከሆነች አዲስ ፣ የማትሞትና ከማያልፈውም ክብር ተካፋይ እንድትሆን ሥጋን ተዋሐደ ። እርሱ በሚታየው ዓለም ያሉትን እንደ ምድር፤ ተራሮችና ዛፎች ያሉ ቁሶችን ከምንምነት እንዲፈጠሩ፤ በመሐላቸውም ወንዞች እንዲፈስሱ፣ አስቀድመው ከተፈጠሩት ፍጥረቶች የሰማይ አእዋፍ እንዲፈጠሩ፤ ከዚህም በላይ በዓይን ለማየት ስውር የሆኑ እንደ እሳትና ነፋስ ያሉ ፍጥረታት እንዲፈጠሩ ካደረገ ።
ይቀጥላል