11. ልክ የሌለውና ከቃላት በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ጥበብ ግዙፍ፣ ስውርና ያማረ የየራሳቸው አካል ያላቸውን ፍጥረታት በፈቃዱ ፈጠረ። እንደ ፈቃዱ የሚያደርገው ይህ አምላክ በማይነገር ስጦታው ፣ ከአእምሮ በላይ በሆነው በጎነቱ ራሱን ወስኖ ከሥጋችን ጋር ተዋሕዷል። የማይታየው ይታይ ዘንድ ፣ የማይዳሰሰው ይዳሰስ ዘንድ ። ነፍሳቸው የታደሰ ሰዎችም መልካምነቱን ይቀምሱና ዘለዓለማዊውን ብርሃን በእውነት ያጣጥሙ ዘንድ እንደየችሎታቸው መጠን ቅዱስና ታማኝ ለሆኑ ለሚገባቸው ነፍሳት ራሱን ይገልጽላቸዋል ። እሱ ሲፈቅድ እሳት ይሆንና ነፍስ ውስጥ ያሉትን የኃጢአት አሳቦች ያቃጥላል ፤ አምላካችን፡- “በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነው” (ዕብ 12፥29፤ ዘዳ 4፥24) ። ሲፈቅድ ከቃላት በላይ የሆነ ዕረፍት ይሆናል ። በዚህም ነፍስ በእርሱ እፎይ ትላለች ። ሲፈቅድ ሐሤትና ሰላም ይሆናል ፣ ይበዛልም፤ ይትረፈረፋልም ።
12. በእውነት ፍጡራኑን ለማስደሰት ከፍጥረቱ እንደ አንዱ መሆን ከፈለገ ይሆናል ። ለምሳሌ የብርሃን ከተማ እንደ ሆነችው እንደ ኢየሩሳሌም ወይም እንደ ሰማያዊቷ ጽዮን መሆን ይችላል ። መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- “ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም” (ዕብ 12፥22) ። ለእርሱ ሁሉም ነገር ቀላል ነው። ለታማኝ ነፍሶች ደስታ ራሱን ወደ ፈለገው ዓይነት ቅርጽ መቀየር ይችላል ። ሰው የእርሱ ጓደኛ ለመሆንና እርሱን ለማስደሰት ብቻ ይጣር እንጂ “ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” የተባሉትን ሰማያዊ የሆኑ መልካም ነገሮችን ፣ ከቃላት በላይ የሆኑ ደስታዎችንና መስፈሪያ የሌላቸውን መለኮታዊ ሀብቶችን በእውነት ይካፈላል ። የጌታ መንፈስም ለተገቡ ነፍሶች ራሱ ዕረፍታቸው ፣ ደስታቸውና ዘላለማዊ ሕይወታቸው ይሆናል ። ጌታ በሥጋና በጽዋውም ራሱን ይገልጻል ። በወንጌል ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና ፡- “ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል” (ዮሐ 6፥58) ። ነፍስን ከመታሰብ በላይ የሆነውን ዕረፍትና በመንፈሳዊ ደስታ ይሞላት ዘንድ እርሱ እንዲህ አለ፡- “የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ” (ዮሐ 6፥35)። እሱ ራሱን በሰማያዊው ምንጭ እንዲህ ሲል ይገልፃል፡- “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል” (ዮሐ 4፥14) “ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና ። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል” (1ኛ ቆሮ 10፥4፤ 12፥13) ።
13. ለሁሉም ቅዱሳን አባቶች እርሱ በፈለገውና ለእነርሱ ምርጥ በሆነው መልኩ ተገለጸላቸው ። ለአብርሃም ፣ ለይስሐቅ ፣ ለያዕቆብ ፣ ለኖኅ ፣ ለዳንኤል ፣ ለዳዊት ፣ ለሰሎሞን ፣ ለኢሳይያስና ለሁሉም ነቢያት በተለያየ መንገድ ተገለጸላቸው ። እኔ እንደማምነው ሙሴ በዚያ ተራራ ላይ በየሰዓቱ ወደ ጠረጴዛው ተጋብዟል ።በዚያም በዓልን አክብሯል ።ሐሤትንም አድርጓል ። ሁሉንም ቅዱሳን ዕረፍትና ድኅነትን ሊሰጣቸው ወደ መለኮታዊም እውቀትም ሊመራቸው እንደ ፈቀደው ሆኖ ተገልጾላቸዋል ። እርሱ የመረጠው ነገር ሁሉ ለእርሱ ቀላል ነው ። እርሱ እንደ ፈቀደ ራሱን ወስኖ ይገልጻል ።የሚያፈቅሩትም በዓይናቸው እንዲያዩት ፣ ለሚገባቸውም ራሱን ከአእምሮ በላይ በሆነው የክብር ብርሃን፣ ታላቅ በሆነው ፍቅሩና ኃይሉ ይገለጽላቸዋል ። በታላቅ ፍላጎት እግዚአብሔርን ለመቀበል የታደለች ነፍስ በእምነትና በፍቅር እግዚአብሔርን የምትጠብቅ ሰማያዊውንም የመንፈስ ፍቅርና ሰማያዊውን የዘላለም ሕያውነት የተቀበለች ነፍስ ከሁሉም ከዓለማዊ ምኞቶች ትላቀቃለች ።ከሁሉም የክፋት ባርነቶችም ነጻ ትወጣለች ።
14. ብረት ፣ እርሳስ ፣ ወርቅ ወይም ብር እሳት ውስጥ ሲጨመሩ እንደሚቃጠሉ ከነበራቸውም ተፈጥሮአዊ ጥንካሬ እንደሚለሰልሱ በእሳት ውስጥ በቆዩ መጠንም ይበልጥ እየቀለጡ እንደሚሄዱ የነበራቸውም ጠንካራ ባሕርይ በጋለው እሳት ኃይል እንደሚቀየር ፤ ዓለምን የካደችና ፍላጎቷን ጌታ ላይ ብቻ ያደረገች ነፍስ በብዙ ፍለጋ ፣ ሕመምና ሁከት ውስጥ እርሱን በእምነትና ተስፋ ያለ ማቋረጥ ትጠብቃለች ።ሰማያዊውንም እሳትና የመንፈስን ፍቅር የተቀበለች ነፍስ ከሁሉም ዓለማዊ ምኞቶች ትላቀቃለች ።ከክፉ ምኞትም ነፃ ትወጣለች። ነፍስ የማያልቅና የማይጠፋ ፍቅር ካለው ከሰማያዊው ሙሽራ አንጻር ለምዳው የነበረውን የኃጢአት ደስታና ሁሉንም ነገሮች እንደ ጉዳት ትቆጥራቸዋለች ።
15. በእውነት እንዲህ ዓይነት ነፍስ ያላቸው በጣም ተወዳጅ የሆኑ ወንድሞች (ነፍስን) ይህን መለኮታዊ ፍቅር ከከለከሏት ፍቅር ከእነርሱ ይሸሻል ። ይህም ፍቅር የነፍስ ሕይወትና ዕረፍት ፣ ከቃላትም በላይ የሆነ ከሰማያዊው ንጉሥ ጋር የሚኖር ምሥጢራዊ ኅብረት ነው ። የምድራዊው ፍቅር ኅብረት (ትዳር) ከአባት ፣ እናት ፣ ወንድምና እህት ይለያል ። በዚህ ዓይነት ግንኙነትም ሁሉም ነገር እንደ ውጫዊ ነገር ይታሰባል ።ካገቡም በኋላም ቢሆን እነዚህ ያገቡ ሰዎች ቤተሰባቸውን ይወዳሉ ። ነገር ግን ከትዳር አጋራቸው ጋር እንዳለው መውደድ ሳይሆን ከዚያ ውጪ በሆነ በተለየ መውደድ ነው የሚወዷቸው ። ወንድ ለሁሉም ነገር ያለው እይታ ከሚስቱ ጋር ባለው ግንኙነት ይወሰናል ።በዚህም ምክንያት መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ፥ በሚስቱም ይጣበቃል ፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” (ዘፍ.2:24) ።ይህ ሥጋዊ ፍቅር ከሌሎች የፍቅር ዓይነቶች እንድንለይ የሚያደርገን ከሆነ በእውነት ሰማያዊና ተወዳጅ ወደ ሆነው ወደ መንፈስ ቅዱስ የፍቅር ኅብረት የገቡት እንዴት አብዝተው ከዓለማዊ ፍቅር አይለዩም ? እነርሱም ሁሉንም ነገር ችላ ይሉታል ።እነርሱንም አንዳች የሚስባቸው ነገር የለም ። ምክንያቱም እነርሱ በሰማያዊው ናፍቆት ድል ስለ ተነሡና ከሰማያዊ ናፍቆት ጋር ሙሉ በሙሉ ኅብረት ስላደረጉ ነው ።
16. እንግዲህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እንዲህ ዓይነት መልካም ነገሮች ከፊታችን ካሉልን እንዲህ ያለም ታላቅ ቃል ኪዳን ከጌታ ከተገባልን እርሱን እንዳናገኝ የሚያደርጉንን እንቅፋቶች ነቅለን እንጣል ። የዓለምንም ፍቅር እንካድ ። ያንን መልካም ነገር በመፈለግና በመናፈቅ ራሳችንን ለጌታ እንስጥ። በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ፍቅርን ተከታተሉ” (1ኛቆሮ 14፥1) ብሎ እንድንከተለው የተናገረለትን ከመናገር በላይ የሆነውን የመንፈስ ፍቅር እንድናገኝ ከግትርነታችንም በገናናው ቀኝ እጅ ተለውጠን ወደ መንፈሳዊ ግለትና ዕረፍት ለመድረስ መለኮታዊ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እንሸነፍ። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ መመለሳችንንና ከእርሱ በተቃራኒ ካሉ ነገሮች ነጻ መውጣታችንን በተስፋ ስለሚጠብቅ ለሰው ልጆች ቸር ነው ። ምንም እንኳን እኛ ታላቅ በሆነው ጭፍንነታችን ፣ በአላዋቂነታችንና ሕይወትን ትተን ለክፉው መንገድ ባለን ዝንባሌ በመንገዳችን ላይም ብዙ እንቅፋቶችን በማስቀመጣችን ፣ ንስሐ ለመግባት ባንወድም እርሱ አሁንም ትዕግሥተኛ ነው ። እርሱ ስለ እኛ ይራራል ፤ ንስሐ ገብተንም ወደ እርሱ እንድንመለስ በተስፋ ይጠብቀናል ። በውስጥ ባለው ሰውነታችን /በውስጣዊ ማንነታችን መንፈሳዊ አብርሆትን አግኝተን በፍርድ ቀን እንዳናፍር ይሻል ።
17. ጸጋን መለማመድ ከባድ ስለሆነና ከዚህም በላይ ሳይታወቅ ውስጥ ውስጡን የሚሠራ የጠላት ምክር ስላለ ይህ ነገር አስቸጋሪ ከመሰላችሁ ይህን አስተውሉ ።እግዚአብሔር እየራራ ፣ እያዘነና ድካማችንን እየተሸከመ መቀየራችንን እየጠበቀ ነው። ኃጢአት ስንሠራም ንስሐ እንደምንገባ በመጠበቅ እጁን ይዘረጋልናል ፤ ነቢዩም እንዳለው፡- “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን? (ኤር 8፥4)። ስንወድቅም እኛን መልሶ ለማንሣት አያፍርብንም ። እኛ መልካም ፍላጎት እንዳለን በማስተዋል ብቻ እንሁን ፤ ከእርሱ እገዛ ለማግኘት እንለወጥና እንሻ። እርሱ ሁል ጊዜ ሊያድነን ፈቃደኛና ዝግጁ ነው ። እርሱ የእኛን ወደ እርሱ መመለስ ከልብ በሆነ ስሜት ይጠብቃል ።ባለን አቅም ሁሉ ከመልካም ዓላማም ከሚመነጭ እምነትና ቅናት የጥረታችን ሁሉ መሳካት እርሱ በእኛ የሚሠራው ሥራ ነው። ስለዚህ የተወደዳችሁ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ክፉ አሳብ ፣ ግድ የለሽነትንና ስንፍናን አስወግደን ደፋር ለመሆንና እርሱን ለመከተል እንጣር ። ከሥጋ መቼ እንደምንለይ አናውቅምና ኃጢአት እንዴት እየጎዳን እንደሆነ ሳንገነዘብ በየቀኑ አናስወግደው ። ለክርስቲያኖች የተሰጠው ተስፋ እጅግ ታላቅና ከመናገር በላይ የሆነ ነው። የሰማይና የምድር ክብርና ውበት ፣ የትኛውም ዓይነት ጌጥና አማራጮች ፤ የሚታየውም ነገር ክብር፣ አስደሳችነት፣ መልካምነትና ብልጽግና ከአንድ ነፍስ ተስፋና ክብር ጋር አይነጻጸርም ።
18. ይህ ከሆነ እንዴት ነው የጌታን ተስፋና ማሳመኛ የማንቀበለው ? ራሳችንን ለእርሱ ሰጥተን ወንጌልም “የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ”(ሉቃ 14፥26) እንደሚለው ራሳችንን ክደን ሌላውን ትተን እርሱን ብቻ የማናፈቅረው እንዴት ነው ? ነገር ግን ከእነዚህ ነገሮችና ከተሰጠን ከታላቁ ክብር ከአዳም ጀምሮ ለአባቶችና ለነቢያት ከጌታ የተሰጣቸውን ቃልኪዳን ትተን ታላቁ ጌታ ምን ያህል ታላላቅ ተስፋዎች፣ ምን ያህል መተማመኛዎችና ከመጀመሪያው ጀምሮ እንዴት የሚደንቅ ርኅራኄ እንዳሳየን እስኪ እናድንቅ። በመጨረሻም በራሱ መምጣት ለእኛ ያለውን ከቃላት በላይ የሆነ ደግነቱን በመስቀል ላይ በመሰቀል እኛን ወደ ሕይወት ጎዳና በመመለስ አሳየን ። ስለዚህ እኛም ወደ ራሳችን ፍላጎቶች ፣ ወደ ዓለም ፍቅር ፣ ወደ ራሳችን ዝንባሌና ልምድ ዳግም አንሄድም ። እኛ እምነት የለሾች አሊያም ጥቂት እምነት ያለን እንደሆን ሕይወታችን ይመሰክራል። ሆኖም ግን እርሱ አሁንም ለእኛ መልካም እንደሆነ ቀጥሏል። በሚታየው መልኩ እንደ ክፋታችን ለኃጢአት ለዘላለም አሳልፎ ሳይሰጠን በዚህ ዓለምም ማታለል እንዳንጠፋ እየተንከባከና እየጠበቀ ፣ ታላቅ በሆነው መልካምነቱም የምንመለስበትን ሰዓት በትዕግሥት ይጠብቃል ።
19. እኛ ከንቱ ከሆኑት አሳቦቻችን ጋር ተጣብቀን ፍላጎታችንንም እየተከተልን “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?”(ሮሜ. 2:4) የሚለው የሐዋርያው ቃል እንዳይፈጸምብን እሰጋለሁ። ነገር ግን እንደ እርሱ ተስፋ ፣ መልካምነትና ትዕግሥት መጠን ካልተመለስን በፋንታውም ኃጢአትን ከጨመርን በቸልተኝነታችንና በግድ የለሽነታችን ለራሳችን ተጨማሪ ፍርድንና ቁጣን እናከማቻለን ።እንዲህ የሚለው ቃልም ይፈጸምብናል፡- “ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ” /ሮሜ.2:5/ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት እጅግ ታላቅና ከቃላት በላይ የሆነ መልካምነትን አሳይቷል ፤ ከመጠን በላይ የሆነ ተስፋም ሰጥቷል። እኛም ራሳችንን ለመቀየር ወደ እርሱም ሙሉ በሙሉ ለመመለስ ከጣርን ብቻ ድኅነትን እናገኛለን ።
20. የእግዚአብሔርን ትዕግሥትና ታላቅ የሆነውን መልካምነቱን ማወቅ ከፈለጋችሁ ከቅዱሳት መጻሕፍት እንማር። አባቶች ከእነርሱ የሆኑትን ፣ ቃል ኪዳንም የተሰጣቸውን ፣ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ የመጣውን፣ ኪዳንና የመቅደስ ሥርዓት ለእነርሱ የሆነውን እስራኤልን ተመልከቱ ። (ሮሜ 9፥5) ። እስራኤል ብዙ ኃጢአት ሠርተዋል ። እግዚአብሔርንም ብዙ ጊዜ ገሸሽ ብለዋል ። ሆኖም ግን እርሱ ከቶ አልተዋቸውም ። ነገር ግን ለራሳቸው ጥቅም ብዙ ጊዜ ቀጥቷቸዋል ። ልባቸውን ሊያለሰልስ ወዶ መቅሰፍትን ልኮባቸዋል ፤ አጽናንቶአቸዋል ። አበረታቷቸዋል ፣ ነቢያትንም ልኮላቸዋል። እነርሱ ብዙ ኃጢአት ሠርተዋል ። ብዙ በደልም በድለውታል ። እርሱ ግን ትዕግሥተኛ ነበርና ሲመለሱም በደስታ ተቀበላቸው። ደግመው ከመንገዱ ሲወጡ አይተዋቸውም ።በነቢያቱ ለንስሐ ይጠራቸው ነበር። እነርሱም በተደጋጋሚ ከመንገዱ እየወጡና እየተመለሱ ሲኖሩ መልካም ሆኖ ይቀበላቸውና በእርጋታ ያኖራቸው ነበር ። በመጨረሻ ከሁሉ በላይ በሆነው መተላለፍ ወደቁ ። ይህም መተላለፍ የአባቶችና የነቢያት ትውፊት ነጻ አውጪአቸውና አዳኛቸው ፣ ንጉሣቸውና ነቢያቸው ብሎ ባስተማራቸው በጌታቸው ላይ እጃቸውን ማንሣታቸው ነው ። በሥጋ ሲመጣ አልተቀበሉትም ።በተቃራኒው ክብረ ነክ በሆነ መንገድ ተቀብለውት በመጨረሻ መስቀል ላይ ሰቀሉት ። በዚህ ታላቅ ጥቃት ይህ የላቀ በደል ኃጢአታቸው ከልክ በላይ ሆነና ሞላ ።በዚህም ለምኞታቸው ተላልፈው ተሰጡ ።መንፈስ ቅዱስም የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከተቀደደበት ጊዜ አንሥቶ ተለያቸው ። በዚህም ቤተ መቅደሳቸው ጌታ፡- “ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም ” (ማቴ 24፥2) ባለው የነቀፋ ቃል መሠረት ለጠላቶች ተላልፎ ተሰጠ ። ፈረሰ ፣ ባዶም ሆነ ። በዚህ ሁኔታ በጠላቶቻቸው እጅ ተላልፈው ተሰጡ ።ቅኝ በገዛቸው ንጉሥም በዓለም ዙሪያ ተበተኑ ። ወደ ሀገራቸውም ድጋሜ እንዳይመለሱ ተከለከሉ ።