21. በተመሳሳይ መልኩ አሁንም ሁላችንንም መልካምና ደግ አምላክ እንደ መሆኑ እየታገሠን ነው። ምን ያህል ጊዜ እንደምንበድል እያየ ሰላም ይሰጠናል ። ኃጢአት የሠራው ሰው ራሱን እስኪያቅብ ደግሞ ከመበደል እስኪመለስ ድረስ ይታገሠዋል ። ደግሞም ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ በፍቅርና በደስታ ይቀበለዋል ። መጽሐፉም የሚለው እንዲሁ ነው፡- “እላችኋለሁ ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል” (ሉቃ. 15፥10) “እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም” (ማቴ. 18፥14) ። ነገር ግን በእግዚአብሔር መልካምነትና ትዕግሥት ሥር ያለው ሰው በድብቅ ይሁን በግልጽ ለበደለው በደል ካልካሰ፣ የእግዚአብሔርን ትዕግሥት ኃጢአተኛውን ወደ ንስሐ እንዲመራው ካላወቀ ይህንን ንቆ በኃጢአት ላይ ኃጢአትን ፣ በስንፍና ላይ ስንፍናን፣ በበደልም ላይ በደልን እያከማቸ የኃጢአትን ገደብ ያልፍና በመጨረሻ ድጋሜ ሊነሣበት ወደማይችለው ማንነት ላይ ይደርስና ይሰባበራል ፤ ፈጽሞ ይጠፋም ዘንድ ለሰይጣን ተላልፎ ይሰጣል።
22. ሰዶም ውስጥም የተፈጠረው ይህ ነው ። ንስሐ ሳይገቡ ብዙ ጊዜ በደሉ። በመጨረሻም በከንቱ አሳባቸው መላእክት ላይ የጭካኔ ኃጢአት ሊፈጽሙባቸው ወደዱ ።በንስሐም ሊመለሱ ስላልቻሉ በመጨረሻ ተዋቸው። የኃጢአትንም ልክ አለፉ ፤ በዚህም ምክንያት በመለኮታዊ በቀል በእሳት ጠፉ። በኖኅም ዘመን የሆነው ተመሳሳይ ነገር ነው ። ሁል ጊዜ ንስሐ ሳይገቡ እየበደሉ አሰቃቂና ከፍተኛ የሆነ የኃጢአት ደረጃ ላይ ደረሱ ።ምድርም ፈጽማ ረከሰች ። በግብፃውያኑ ዘንድም የሆነው እንዲሁ ነው ። ብዙ ጊዜ ኃጢአትን ሠሩ ። የእግዚአብሔርንም ሕዝቦች በደሉ ፤ እግዚአብሔር ግን ለእነርሱ መልካም ነበረና ፈጽመው እንዲጠፉ በበሽታ ወረርሽኝ አልመታቸውም ። ነገር ግን ቅጣት እንዲሆናቸውና በንስሐ ወደ እርሱ እንዲመለሱ እየፈለገና እየጠበቀ አነስ ያለ መቅሰፍትን አመጣባቸው ። ነገር ግን እነርሱ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በደሉ ። አሳባቸውንም ቀይረው ባለማመን ለክፉ ዓላማቸው ቆሙ ። የእግዚአብሔርንም ሕዝቦች ጨቆኑ ። እግዚአብሔር ሕዝቡን በብዙ ድንቆች ከግብፅ በሙሴ መሪነት አወጣቸው። ግብፃውያንም የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በመከተል ታላቁን በደል ፈጸሙባቸው። በዚህም መለኮታዊው በቀል ፈጽሞ አጠፋቸውና በላቸው። በውኃም አስጥሞ እንደማይረባ ነገሮች ፈረደባቸው ።
23. ከዚህ በፊት እንዳልነው በተመሳሳይ መልኩ እስራኤላውያንም የእግዚአብሔርን ነቢያት በመግደልና ብዙ ክፉ ነገሮችን እያደረጉ በተደጋጋሚ ኃጢአትን ሠሩ ፤ በደልንም በደሉም ። ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሰላሙን ሰጥቶ በትዕግሥት ንስሐ እንዲገቡ ቢጠብቃቸውም በደሉት ። እርሱም ዳግም እንዳይነሡ አድርጎ ቀጣቸው። እጃቸውንም በጌታ ክብር ላይ አነሡ ። በዚህም ፈጽሞ ተዋቸው ። ነቢይነት ፣ ክህነትና አገልግሎት ከእነርሱ ተወስዶ ለሚያምኑ አሕዛብ ተሰጣቸው ። ጌታም እንዳለው፡- “ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች” (ማቴ. 21፥43) ። እስከዚህ ድረስ እግዚአብሔር ታገሣቸው፤ ለእነርሱም አዝኖ አላጠፋቸውም ። ነገር ግን የኃጢአትን ገደብ አልፈው እጃቸውን የጌታ ክብር ላይ ሲያነሡ እግዚአብሔር ፈጽሞ ተዋቸው ።
24. የተወደዳችሁ እነዚህን ነገሮች ሰፋ አድርገን አይተናል ። ከቅዱሳት መጻሕፍትም ንስሐ በቶሎ መግባትና በመልካምነቱ ከክፉ ሥራችንና መጥፎ ዝንባሌአችን ተላቅቀን እንድንመጣ ወደሚጠብቀን ወደ ጌታ መቅረብ እንዳለብን ተምረናል ። ጌታ ስንመለስ በታላቅ ደስታ ይቀበለናልና አለመታዘዛችን ከቀን ወደ ቀን እንዳይጨምር ፤ በደላችንም እየበዛና እየተከማቸ እንዳይሄድ ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ በራሳችን ላይ እንዳይመጣ እንጠንቀቅ ። ወደ እርሱ በእውነት በተመለሰ ልብ ለመቅረብ በቅንነት እንጣር ። ስለ መዳናችንም ተስፋ አንቁረጥ ። ተስፋ መቁረጥ በራሱ ስህተትና ኃጢአት ነው ። ኃጢአትን ማሰብ ፣ የኃጢአተኛነት ስሜት ተስፋ እስከ ማስቆረጥ ደርሶ ይህን ያህል ከተቆጣጠረን ወደ ኀዘን ፣ ቸልተኛነት ፣ ግድ የለሽነትና ስንፍና እናመራለን ። በዚህም በሰው ሁሉ ላይ ባለው በጌታ ቸርነት ተለውጠን ወደ ጌታ በመቅረብ ድኅነት እንዳናገኝ ያደርገናል።
25. በኃጢአት ቁጥጥር ሥር ስለሆን ይህን ከሚያህል የኃጢአት ቀንበር መመለስ ከባድና የማይቻል ሆኖ ከተሰማን ፣ አስቀድሜ እንዳልኩት ይህ አሳብ ለድኅነታችን ክፋትና መሰናክል ነው የሚል አሳብም ካለን ጌታችን በቸርነቱ ሥጋ ተዋህዶ ሲመጣ እንዴት የዓይነ ሥውሮችን ዓይን እንዳበራ፣ ሽባዎችን እንደ ተረተረ ፣ ሁሉንም ዓይነት በሽታዎች እንደ ፈወሰ ፣ የጠፉትንና የበሰበሱትን ሙታንን እንዳስነሣ ፣ መስማት የተሳናቸውን እንዲሰሙ እንዳደረገ ፣ ሌጌዎን የሆነን አጋንንትን ከአንድ ሰው እንዳወጣና ከእብደት ወደ ጤነኛ ማንነት እንደ መለሰው እናስብ ። እንዲህ ከሆነ እንዴት ወደ እርሱ የተመለሰችን ፣ ከእርሱ ምሕረትንና እርዳታን የምትፈልግን ነፍስ ከኃጢአት አሳብ ተላቃ ደስታ እንድታገኝ ፤ በጸጋውም እንድትኖርና በአሳብ እንድትታደስ ፣ ጤናማና ሰላማዊ ወደ ሆነ አሳብና እይታ እንድትመጣ ፤ ጭፍን ፣ ደንቆሮና ሙት ከሆነ አለማመንና ግድ የለሽነት ወደ ጸጋው ጥበቃና ወደ ልብ ንጹሕነት እንዴት አብዝቶ አይመልሳትም? ግዙፉን ሥጋ የፈጠረ እርሱ ነፍስንም ፈጥሯታል ። በዚህ ምድርም በተመላለሰበት ጊዜ ሰዎች ወደ እርሱ እገዛና ፈውስን ፈልገው ሲመጡ የእውነት ብቸኛ ሐኪም የሆነው እርሱ ልክ እንደ መልካም ሐኪም ኃጢአታቸውን ሳያስብ እንደየፍላጎታቸው ይፈውሳቸው ነበር ። ለመንፈሳዊውም ነገር ልክ እንደዚሁ ነው ።
26. ለሚጠፋውና ለሚሞተው ሰውነት ይህን ያህል ካዘነ ፣ ለጠየቁትም እጅግ በጣም በላቀ መልካምነት የፈለጉትን ነገር ካደረገ ለማትጠፋ ፣ ለማትሞትና ለማትበሰብስ በድንቁርና ፣ በክፋት ፣ በአለማመን ፣ በግድ የለሽነትና በሌሎች የኃጢአት ደዌዎች ለተያዘች ነፍስ በዚህ ሁሉ ውስጥም ሁና የእርሱን እርዳታ በመሻት ወደ ጌታ ስትመጣ ፣ ዓይኗንም ወደ ምሕረቱ ስታዞር ፣ ከእርሱም ከኃጢአት ምኞት መዳኛና የሁሉም ክፋቶች ማስወገጃ የሆነውን የመንፈስን ጸጋ ለመቀበል ስትሻ እርሱ ራሱ እንዴት አብዝቶ አያደርግላትም? ይህንንም እርሱ ራሱ እንዲህ ብሎ በተናገረው ቃል መሠረት መረዳት እንችላለን፡- “እግዚአብሔር እንኪያስ ቀንና ሌሊት ወደ እርሱ ለሚጮኹ ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? ለሚታገሣቸውም ምርጦቹ አይፈርድላቸውምን? እላችኋለሁ፥ ፈጥኖ ይፈርድላቸዋል” (ሉቃ. 18፥7) ። በሌላ ቦታም እንዲህ ብሎ አጥብቆ አሳሰበ ፡- “እኔም እላችኋለሁ ፡- ለምኑ ፥ ይሰጣችሁማል ፤ ፈልጉ ፥ ታገኙማላችሁ ፤ መዝጊያን አንኳኩ ፥ ይከፍትላችሁማል” (ሉቃ. 11:9) ካለ በኋላ መዝጊያው ላይ እንዲህ አለ ፡- “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ ፥ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን ይሰጣቸው?” (ሉቃ 11፥13)።
27. እንግዲህ ባየናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መሠረት በልመና ዘወትር ሳናቋርጥ የጸጋውን ድጋፍ እንድንለምን አሳስቦናል ። እርሱ ወደ ራሱ እንዲመልሳቸውና ቁስላቸውንም እንዲፈውስ ወደ ኃጢአተኞች ነው የመጣው። እኛ ባለን አቅም ሁሉ ከክፉ ነገር ራሳችንን እንጠብቅ ፤ ከዚህ ዓለም ማታለያዎች መጥፎ ምኞቶች ሸሽተን ፣ ለክፋትና ከንቱ አሳቦች ጀርባችንን ሰጥተን ባለን አቅም ሁሉ ወደ እርሱ እንጓዝ ፣ በእርሱ እንጽና ። እርሱም የሚያስፈልገንን እገዛ ይሰጠናል ። ባላቸው አቅም ሁሉ በፈቃድና በፍላጎት ከዓለማዊ ፍቅር ለመነጠል ፣ ከምድራዊም አሳብ ለመላቀቅ የሚጥሩትን በናፍቆትና በመፈለገ እርሱ ላይ ሁሉንም ነገር የሚጥሉትን ፣ ስሙንም ለሚጠሩትና ወደ እርሱ ለሚመለሱት እርሱ መሐሪ ስለሆነ በፍጥነት የማይፈወሱት ደዌዎችን በመፈወስ ያድናቸዋል ። እንዲህ ላለች ነፍስ እርሱ እገዛውን ይሰጣታል ። ሁሉንም ነገር እንደማይጠቅም ለምትቆጥረው በዚህም ዓለም ባለ በየትኛውም ነገር ላይ ለማታርፍ ነገር ግን ሰላሟንና ዕረፍቷን በእርሱ ፀጥታ ላይ የምታደርግ ነፍስ ፣ እንዲህ ባለ እምነትም ሰማያዊውን ስጦታ የተሰጣት በጸጋም ለሚሰጣት ማረጋገጫ እርካታ ታገኛለች ። ከዚህም በኋላ መንፈስ ቅዱስን በፈቃድዋ ዘወትር ካገለገለች ፣ መልካም በሆነ ነገርም በየቀኑ ካደገች ፣ በጽድቅ መንገድም ከኖረች ፣ እስከ መጨረሻውም ወደ ክፉው መንገድ ሳትናወጥና ሳታጉረመርም ፣ መንፈስ ቅዱስንም በምንም ዓይነት ሁኔታ ሳታሳዝን ከኖረች በምድር ሳለች እነርሱን በመምሰል (1ኛ ቆሮ 11፥1) የእነርሱ ወዳጅና ዘመድ ሆና ኑራለችና ከቅዱሳኑ ጋር ዘላለማዊ ድኅነት ታገኛለች ። አሜን።