“በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።” ኤፌ. 1፡9-10።
ይህ ዓለም በክርስቶስ ተፈጠረ ። በክርስቶስ ዳነ ። እርሱ የአብ ክንዱ ፣ የአብ እጁ ነው ። ሰው በክንዱ ቢገለጥ ፣ በእጁ ቢሠራ እርሱ ሠራው እንጂ ማንም ሠራው አይባልም ። እንዲሁም ክርስቶስ የሠራው ሁሉ አብ የሠራው ነው ። የአብ ክንዱና እጁ ነውና ። ክንድና እጅ ከአካል ሳይለዩ ሥራ እንደሚሠሩ እንዲሁም ክርስቶስ ከአብ ሳይለይ ወደዚህ ዓለም መጥቷል ። እርሱ በሠራው ሥራም አብ ምክሩ ፣ መንፈስ ቅዱስም ሕይወቱ ነውና ምስጋናችን ሥላሴያዊ ነው ። በሌላ አነጋገር ሦስቱ ፍጹማን የሥላሴ አካላት በምስጋና አንድ ናቸው ። አብ ባለበት ወልድና መንፈስ ቅዱስ እንዳሉ ሁሉ ወልድ ባለበትም አብና መንፈስ ቅዱስ አሉ ። እርሱ አብ ዓለምን የፈጠረበትና ዓለምን ያዳነበት ልጁ ክርስቶስ ነው ። ሰው አሳቡን የሚገልጠው ልቡን አውጥቶ ሳይሆን ቃሉን ልኮ ነው ። እንዲሁም እግዚአብሔር አብ ልብ ነውና አይታይም ፣ ክርስቶስ ቃል ነውና ሥጋ ለብሶ ተገልጧል ። ቃል አሳብና ሕይወት አለው ። ቃል በአሳብ ውስጥ ሲዋቀር ሕይወትም ለአሳብም ለቃልም አስፈላጊ ነው ። እንዲሁም ወልድ ያለ አብ አልነበረም ። መንፈስ ቅዱስም ከአብና ከወልድ ተለይቶ አያውቅም ። ያለ ቃል መገለጥ እንደሌለ አብም ያለ ልጁ ሥራ አይሠራም ። ሕይወት በሌለበትም ህልውና እንደሌለ መንፈስ ቅዱስ በሌለበትም አብና መንፈስ ቅዱስ መኖር አይችሉም ። መንፈስ ቅዱስ ለራሱ ፣ ለአብና ለወልድ እንዲሁም ለፍጥረት ሕይወት ነው ።
ዓለም ሲፈጠርም ሆነ ሲድን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ምክር ፣ አምላካዊ ቃልና ዘላለማዊ ሕይወት አብረው አሉ ። ይህም ሦስቱ አካላት አሉ ማለት ነው ። ተግባሩ አሳብ ፣ ቃሉም ልብ ያለው ነው ካልን እኛም ከተግባራችን በፊት አሳብን ማስቀደም ፣ ከቃላችንም በፊት ማሰላሰል ይገባናል ። እግዚአብሔር በቃሉ ስህተት ሳይኖርበት እንከን በሌለው ምክሩ ይመክራል ። እኛ ግን በቃላችን አፍራሽነት አለብንና አሳባችንም ያልተጣራ ነውና ማሰብ ያስፈልገናል ። ቃላችን አሳብ ያስፈልገዋልና አስበን መናገር ያስፈልገናል ። ተናግረን ማሰብ ግን ሞኝነት ነው ።
ሐዋርያው እንደ ወደደ ፣ እንደ አሳቡ ፣ የፈቃዱ ምሥጢር የሚሉትን ደገኛ ቃላትን ይጠቀማል ። የእግዚአብሔር ውዴታ ሰውን በመፍጠርና በማዳን ተገልጧል ። ሰው ራሱን መቀበል ቢከብደው ለሰዎችም የማይፈታ ቅኔ ቢሆን እንኳ እግዚአብሔር የወደደው ነው ። የተፈጠረው በስህተት ፣ በወላጆቹም ውዴታ አይደለም ። ሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ውጤት ነው ። በዚህ ዘመን ፣ በዚህ አገር ፣ በዚህ ቤተሰብ ራሴን ሳገኘው ይህ የእግዚአብሔር ውዴታ ነው ። እግዚአብሔር የወደደውን ማንነቴን እኔ መጥላት ፣ እግዚአብሔር የወደደላቸውን እኛ መጥላት ፣ ጥቁር ነጭ ፣ ሀብታም ደሀ እያሉ ሰውን መናቅ ፣ ማሳደድ አይገባም ። ይልቁንም በጎሠኝነት ሰውን የሚገድሉ በቀጥታ ከዚህ አምላካዊ ውዴታ ጋር እየተጣሉ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ እኛ የወደድነው እንጂ አንተ እግዚአብሔር የወደድከው መኖር አይችልም እያሉ ነው ። ሰውን ግዙፍ ሰይጣን ፣ ልቡሰ ሥጋ ጋኔን የሚያደርገው ዘረኝነት ነው ። እግዚአብሔር ፈጣሪነቱን ማንም እንደማይቀማው የአዳኝነቱ ምስጋናም ገንዘቡ ነው ። እርሱ በመውደዱ ታላላቅ ተግባራትን እንደ ፈጸመ ፣ ፍቅሩም ጸጸት የለበትም ። ሰውን ለመፍጠር እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር ጋር መከረ እንጂ ማንም ምክር አላቀረበለትም ።
ቅዱስ በሆነው አሳቡ ከዘላለም በፊት አሰበን ። ቀኑ ሲደርስም አዳነን ። ጊዜ ሳይጀመር ወዶናልና በጊዜ ውስጥ ይጠላናል የሚል ስጋት የለብንም ። ነገ ጊዜ ነውና ነገ ይጠላናል ብለን የማንጠረጥረው እግዚአብሔር ነው ። ፍቅሩ እንደ አካሉ ዘላለማዊ ነው ። እንደ ፈቃዱ ይላል ። ፈቃድ መወሰን ፣ የተግባር ዋዜማ ፣ የመሆን ቁርጥ አሳብ ነው ። እንደ ፈቃዱ አዳነን ። ፈቃዱ ምሥጢር ያለበት ነው ። ይህ ምሥጢርም እስከ ጊዜው የተሸሸገ ሲሆን ዘመኑ ሲደርስ የተገለጠ ነው ፤ ሁለተኛው ትርጉሙ ምሥጢር የተባለው ድንቅ ፣ ሊያዩትና ሊያገኙት የሚያጓጓ ተብሎ የሚፈታ ነው ። ይህ ምሥጢርም ፣ የአበው ተስፋ ፣ የነቢያት ትንቢትና ሱባዔ ፣ የክርስቶስ ሰው መሆንም ግቡ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በእርሱ ለመጠቅለል ነው ። መጠቅለል መግዛትና ማስተዳደር ፣ ሁሉን በእግሩ ሥር ማስገዛት ነው ። ግዛት ከድቶት ወደ ዓለም አልመጣም ፣ ሁሉ ይገዛለታል ። አሁን በሰማይና በምድር ታርደሃልና ተብሎ በሰውና በመላእክት እንዲመሰገን ፣ የአዳኝነቱ የምሥራችም ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክ የሥላሴ ፈቃድ ሁኗል። እግዚአብሔር አብም በክርስቶስ መመስገንን ወዶአልና “በአሐዱ ወልድከ” – በአንድ ልጅህ ብለን እናመሰግነዋለን ። ይህም ሁሉም ነገር በክርስቶስ መጠቅለሉን የሚገልጥ ነው ። የየዕለት ርእስ ፣ የሰማያውያንና የምድራውያን የምስጋና ድምፅ “ታርደሃልና ቅኔ ይገባሃል” የሚል ነው ።
የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /19
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም.
እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት