የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“አቤቱ÷ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ”

(መዝ. 9፥19)፡፡
ቤተ ጳውሎስ ቅዳሜ መስከረም 12/2004 ዓ.ም.
ነቢዩ ዳዊት የዘመራቸው ድንቅ መዝሙሮች የአድማጮችን ጆሮ ለመማረክ የደረሳቸው አልነበሩም፡፡ ጥልቅ ምስጋናውን፣ ብዙ መከራውን ለእግዚአብሔር የገለጠበት፣ የሚያልፍበትን የሕይወት ገጽታ ለታላቁ ዳኛ ያነበበበት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ከታወቀ የብሉይ ኪዳን መምህር እግር ሥር ቁጭ ብሎ እንደ ተማረ አልተጻፈልንም፡፡ ዳዊት እግዚአብሔር በሕይወት ውስጥ እያሳለፈ ያስተማረው የኑሮ ተማሪ እንደሆነ ግን እንረዳለን፡፡ ዝማሬው ዛሬም ድረስ ልብን የመማረክ አቅም ያገኘው ጥልቅ ስሜቱን ለእግዚአብሔር የገለጠበት በመሆኑ ነው፡፡ ጆሮን መማረክና ልብን መማረክ ልዩነት አለው፡፡ የሰውን ስሜት መቆስቆስና የሰውን መንፈስ ማርካት ሰፊ ልዩነት አለው፡፡ የዳዊት ዝማሬ ከነፍሱ የፈለቀ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያወጋበት በመሆኑ ኃይል አለው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት የምናደርገው እውነተኛ አምልኮ ለትውልድ የመትረፍ አቅም አለው፡፡
ነቢዩ ዳዊት ብዙ መከራ፣ ብዙ መገፋትን ያየ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ ጭንቅ ውስጥ ይመኝ የነበረው ቀን አግኝቶ መልካምን ለማድረግ እንጂ ቀን አግኝቶ ለመበቀል አልነበረም፡፡ ገና በምኞቱ እግዚአብሔር ያልታዘበው ሰው ነበር፡፡ በመከራና በፈተና ውስጥ ሆነን የምንመኘው ምንድነው? ይህንን አልፈን በዘበቱብን ሰዎች ላይ ለመዘባበት ይሆን? ባልተጨበጠ ነገር እግዚአብሔርን እንዳንበድል እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡ የተገፋን ከሆንን እግዚአብሔር ለሚገፉት ድንበር ያድርገን! ብድር ስንመላለስ ይኸው ዓለም ሊያልፍ ነው፡፡
ዘማሪ አሳፍ በአንድ ስፍራ ላይ፡- “ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ” ብሏል (መዝ. 74፥2)፡፡ ይህ ሰው ፍርድ የተጓደለበት፣ ፍርድ ሲጓደልም ዓይቶ ያዘነ ነው፡፡ የዚህ መካሻው እንደ ስእለት የሆነው ጸሎትም፡- “ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ” የሚል ነበር፡፡ ጊዜው ሲሰጠን ልንፈተንበትም ተሰጥቶናል፡፡ ያን ቀን ዳኛው በቅን መፍረድ፣ ሐኪሙ በቅን ማከም፣ ሰባኪው በቅንነት መስበክ ይገባቸዋል፡፡ ጊዜን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን ዕድል ታማኞች መሆን ያስፈልገናል፡፡ በዓለም ታሪክ እንዳየነው ሕዝብን ሲበድሉ የነበሩ በደልን ተቃውመው ጫካ የገቡ፣ በከተማ አብዮት ያደረጉ ናቸው፡፡ የሊቢያው መሐመድ ጋዳፊ፣ የኡጋንዳው ኢዲአሚን ዳዳ፣ የኢትዮጵያ መንኖች ጥምረት የሆነው ደርግ እነዚህ ሁሉ ግፍን ተቃውመው ግፍን ሲፈጽሙ የኖሩ ናቸው፡፡ ዛሬም የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ባለርስቶችን ተቃውመው አብዮት ያደረጉ ባለርስቶች ሲሆኑ የፍርድን መዛባት ተቃውመው የታገሉ ፍርድ አጉዳዮች ሲሆኑ ይታያሉ፡፡ ጊዜውን ሲቀበል በቅን ለመፍረድ ዛሬ ብጽዓት/ስእለት/ የሚያደርግ ማነው?
ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር 9 ላይ ያቀረበውን ልመና እንመልከት፡-
“አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ”
(መዝ. 9፥1)፡፡
ለእግዚአብሔር አባትነት የሚቀርብ ትልቅ የአክብሮት ቃል “አቤቱ” የሚለው ነው፡፡ የአባት ጌታ ለሆነው ለእግዚአብሔር ብቻ “አቤቱ” ይባላል፡፡ “ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት” እንዲሉ አቤት የታላቅ ታዛዥነት ድምፅ ነው፡፡ አቤቱ የሚለው ቃል የምገዛልህ ጌታዬ እንደ ማለት ነው፡፡ “አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥” ልብን ሁሉ ለእግዚአብሔር ማቅረብ መታደል ነው፡፡ አሳባችንን የወረሰው የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ከሆነ ትልቅ ዕጣ ነው፡፡ “በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ” ብሏል፡፡ ምስጋናው ከልቡ ሞልቶ በከንፈሩ የሚፈሰስ እንጂ በልቡ የሌለ የተጠና ግጥም አልነበረም፡፡

እግዚአብሔር ተአምራትን የሚያደርግ አምላክ ነው፡፡ ከተፈጥሮ በላይ የሆኑ ተአምራትን በማድረግ ልጆቹን ይታደጋል፡፡ ነቢዩ እግዚአብሔር ያደረገለት ራሱ ለራሱ ሊያደርገው፣ ሰዎችም በደግነታቸው ሊያደርጉለት የማይችሉትን ነገር ነው፡፡ ከተፈጥሮ በላይ በሆነ ኃይል እግዚአብሔር ረድቶታል፡፡ ስለዚህ ተአምራቱ ምስክርነት እያቀረበ ነው፡፡ ዝማሬ ምስጋና ብቻ ሳይሆን ምስክርነትም ነው፡፡ ምስክርነትም የሌሎችን ልብ ለእምነት የሚቀሰቅስ ነው፡፡ በመቀጠልም ነቢዩ፡-
“በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ÷ ለስምህ እዘምራለሁ” (መዝ. 9፥2) ብሏል፡፡
በእግዚአብሔር መደሰት የማያቋርጥ ሰላም ነው፡፡ በእግዚአብሔር የምንደሰተው ደስታ አልፎ አልፎ፣ የሰንበት ቀን፣ ወይም በዓመት በዓል ቀን፣ አሊያም በደመወዝ ቀን ሳይሆን ሁልጊዜ የታዘዘልን በረከት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች የሚያሳዝኑ በሚመስሉበት በዚህ ዘመን በእግዚአብሔር መደሰት መንፈሳዊ መብት ሆኖ ተሰጥቶናል፡፡ እግዚአብሔር ልዑል ነው፡፡ ከፍ ያለ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከጠላቶቻችን በላይ ነው፣ እግዚአብሔር ከወዳጆቻችንም በላይ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከፍ ካሉትም በላይ ከፍ ያለ ነው፡፡ በከፍታው ባስጨነቀን ነገር ላይ እግዚአብሔር ልዑል ነው፡፡
የፍጥረት ስም መጠሪያ እንጂ መለኮታዊ ቅባት የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ስም ግን አምልኮ የሚገባው የሚዘመርለት ስም ነው፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ዳዊት፡- “ልዑል ሆይ ለስምህ እዘምራለሁ” ያለው፡፡
ነቢዩ ዳዊት በመቀጠል፡-
“ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ
ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ፡፡
ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤
ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ፡፡” አለ፡፡
             (መዝ. 9፥3-4)፡፡
ዳዊትን ለመያዝ የሚገሰግሰው ጦር ዳዊት ብቻውን መስሎት እችለዋለሁ ብሎ ታምኖ የመጣ ሠራዊት ነበር፡፡ ሲቀርብ ግን ዳዊትን ከእግዚአብሔር ጋር አገኘው፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ኋላ ሲገሰግስ እግዚአብሔር መመለሻ ነሥቶ አጠፋለት፡፡ መሸሻ የሚገኘውም እግዚአብሔር ሲረዳ ነው፡፡
ዳዊት ለራሱ አልፈረደም፣ የሚገባኝ ይህ ነው አላለም፡፡ ጠላቱንም ለመበቀል አላሰበም፡፡ ለእግዚአብሔር መንገዱን በመልቀቁ እግዚአብሔር በፍርድና በበቀል አለፈ፡፡ ነቢዩ ዳዊት ትግሉ ከጠላት ክፋት በላይ የእግዚአብሔርን እጅ ያየበት ነውና በመኖሩ ደስ ብሎታል፡፡
ዳዊት በሰዎች ትላንት ቆስሎ አላበቃም፡፡ አሁንም መልካቸውን የለወጡ ክፉዎች መጥተውበታል፡፡ የሚሸነፉም አይመስሉም፡፡ በዚህ ጊዜ፡- “አቤቱ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ” ብሎ ጸለየ (መዝ. 9፥19)፡፡
ወደ ራሳችን ዘመን ስናይ ጊዜው የክፉዎች ይመስላል፡፡ ቢነቀነቁ የማይወድቁ፣ ቢከሰሱ የማይፈረድባቸው የሞሉበት ይመስላል፡፡ አንድ ቃል ስንናገራቸው ሺህ አፍ ያላቸው፣ አንድ ርምጃ ስንነሣ ሠራዊት የሚልኩብን፣ ፍርድ ቤት ብንሄድ ቀድመው የሚያስፈርዱብን፣ ሁሉን በዕውቀታቸው ሁሉን በገንዘባቸው የያዙ የሚመስሉ፣ የተንኮላቸው ጦር ረጅም ሆኖ አንጀትን የሚዘረግፍ የሚመስሉ ዛሬም አሉ፡፡ “አባት ዳኛ ልጅ ቀማኛ” እያልን ይሆን? ለእውነት የሚያደላ ጠፍቶ ተክዘን ይሆን?
ይህች ዓለም ለሰው ፈቃድ የተተወች ትመስላለች፡፡ ብዙኃን ከተስማሙ ውሸት እውነት በሚባልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ኃጢአትን ቢያንስ ድካሜ ነው ከማለት ሳይንሳዊ ምክንያት እየፈለግንለት ነው፡፡ ብዙ ነገሮችን ስናይ ሰው የበረታበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ጸሎት ያስፈልጋል፡፡ ሰው ከበላዬ እግዚአብሔር አለ ብሎ ማመን አለበት፡፡ አሊያ ለግፉ ድንበር የለውም፡፡ አይሁዳውያን በአናታቸው ላይ የሚያደርጉት ትንሽ ቆብ አለ፡፡ ትርጉሙና መልእክቱ ከበላይህ ሥራህን የሚመዝን ያህዌ/እግዚአብሔር/ አለ ማለት ነው፡፡
የቀኑ አዛዥ የመሰሉ፣ የተንኰል መንገዳቸው የረቀቀ፣ ሁሉ የሚሰማቸው፣ ወተቱን በቃላቸው የሚያጠቁሩ፣ ማሩን በሐሜታቸው እሬት አድርገው የሚያቀርቡ፣ አትናገሩ፣ አትሥሩ፣ አትጻፉ፣ አትመኑ የሚሉን ቢኖሩ እንደ ዳዊት፡- “አቤቱ፥ ተነሥ ሰውም አይበርታ” በማለት መጸለይ ይገባናል፡፡
ይህችን ዓለም አንተው ምራት፣ ለእኛ አትተዋት ብለን መማለል ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ከተነሣ ብርቱ የለም፡፡ እግዚአብሔር እስኪነሣ ኃያል ነኝ ብሎ የሚፎክር ይኖራል፡፡ በእግዚአብሔር ግርማ ፊት ግን የሚቆም ጽናት የለም፡፡ ለዚህ ነው በሌላ ስፍራ ላይ ይኸው ዳዊት፡- “እግዚአብሔር ይነሣ፥ ጠላቶቹም ይበተኑ፥ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ፡፡ ጢስ እንደሚበንን እንዲሁ ይብነኑ፤ ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ እንዲሁ ኅጥአን ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ፡፡ ጻድቃንም ደስ ይበላቸው÷ በእግዚአብሔርም ፊት ሐሤት ያድርጉ÷ በደስታም ደስ ይበላቸው” ብሏል (መዝ. 67፥1-3)፡፡
                                   “አቤቱ ተነሥ፤ ሰውም አይበርታ”
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ