የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አትፍራ

“አሁንም ያዕቆብ ሆይ ፥ የፈጠረህ ፥ እስራኤልም ሆይ ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ ።” ኢሳ. 43፡1
አንድ ሰው፡- “ሁልጊዜ የሚጠጡ ፍጹም አያጣጥሙም ፤ ሁልጊዜ የሚናገሩ ፍጹም አያስቡም” ብሏል ። እግዚአብሔር የሚናገረንን የማናስበው ለምንድነው ? ካልን ሁልጊዜ ስለምንናገር ነው ። አስበን እንናገራለን ፣ የተናገርነውንም እናስባለን ። በዚህ ዙረት ውስጥ ስለምንሆን በምናየው በምንሰማው ተወስነን እንታወካለን ። የተጨማደዱ የሰዎች ፊት ፣ የቀዘቀዙ ሰላምታዎች ፣ ለየት ያሉ የሰዎች እንቅስቃሴዎች ደግሞ ምን እየታሰበብኝ ነው ? እያልን እንድንጨነቅ ያደርጉናል ። እግዚአብሔር የሰጠን የተስፋ ቃል ግን ከሰማይና ምድር ማለፍ የሚበልጥ ነው ። የገዛ ጥላችን የሚያስደነብረን ፣ እያንዳንዱ ኮሽታ የሚያስበረግገን ከሆነ እግዚአብሔር የነገረንን ተስፋዎች ማሰብ አልቻልንም ማለት ነው ። መናገር ብዙ ጊዜ ውጤታማ የሚያደርገን ይመስለናል ፤ ለእግዚአብሔር መናገር ሳይሆን ለሰው መናገር ድል የሚሰጠን ይመስለናል ። መናገራችን ግን እያቀጣጠለን እንጂ እያበረደን አይመጣም ። እግዚአብሔር የሰጠንን ተስፋ ስናስብ ግን መልሰን መበርታት እንጀምራለን ። “ተማሪ የለም እንጂ አስተማሪው ብዙ ነው” ይባላል ። ማኅበረሰቡ ፣ ቀኑ ፣ ክሰተቱ ፣ አደጋዎች ፣ ሰዎች የሚያልፉበት ምጥ ፣ ስህተታችን የሚያመጣብን ቊስለት ፣ ምቀኛ ጎረቤቶች የሚስገዙን ዕቃ ፣ ያለፈው ዘመን ጠባሳ ፣ ትኩሱ የኑሮ ቊስል ፣ የሞቱት ወገኖቻችን እነዚህ ሁሉ አስተማሪዎች ናቸው ። የሚማር ግን እያነሰ ነው ። በዓለም ላይ ከትምህርት ነጻ የሆነ ቀን ፣ ሰውና ክስተት የለም ። ብንማር ስጋትን እናሸንፍ ነበር ። ከልኩ አያልፍምና ።
የሰው ልጅ ፍርሃቶች ዕለት ዕለት እየጨመሩ ነው ። መኪናውን ከፍቶ የሚነዳ ፣ ቤቱን በርግዶ የሚቀመጥ ፣ ሰው አፍጥጦ ሲያየው የሚረጋጋ እየጠፋ ነው ።ፍርሃት በማያቋርጥ ሁኔታ ያዋራናል ። ለተቀመጥንበት ቤት ዋስትና ማጣት ፣ ለምንጓዝባቸው ከተሞች ያለን አመኔታ ዘወትር ይበጠብጠናል ። ሰውን መፍራት ሲጠቃለል ራስን መፍራት በመሆኑ ራሳችንን በመፍራት ተይዘናል ማለት ነው ። የእግዚአብሔር ቃል ግን “አትፍራ” ይለናል ። በቅዱስ መጽሐፍ ላይ “አትፍራ” የሚል ቃል 365 ጊዜ ተጠቅሶአል ። የዓመቱ ቀኖች 365 ናቸውና በየቀኑ አትፍራ ማለት ነው ። “አትፍራ” የሚል ድምፅ ከተሰማባቸው የቅዱስ መጽሐፍ ክፍሎች አንዱ የነቢዩ የኢሳይያስ መጽሐፍ አንዱ ነው ።
እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ላይ በስም የሚጠራ ወዳጅ ፣ የፈጠረ ፣ የሠራ፣ የተቤዠ እንደሆነ ተጠቅሷል ።
እግዚአብሔር በስም የሚጠራ ወዳጅ ነው ። “ሰው ሁሉ በምድር ላይ ሊሰማው የሚወደው ሙዚቃ ቢኖር የገዛ ስሙ ነው” ይባላል ። ሰዎች በስማቸው ስንጠራቸው ከፍ ያለ ደስታ ይሰማቸዋል ። የጠራቸው ሰው እንዳልረሳቸው ፣ በልቡ እንደ ጻፋቸው ፣ ዋጋ እንደ ሰጣቸው ይረዳሉ ። እግዚአብሔር በስማችን ይጠራናል ። ያውቀናል ፣ በልቡ ጽፎናል ፣ በእኛም ደስ ይለዋል ።ሰዎች በስማችን ካልጠሩን እንደ ተቀየሙን ይሰማናል ። እግዚአብሔር በስማችን ሲጠራን እንደሚወደን እንገነዘባለን ። ሰዎች በስማችን ካልጠሩን ፍርሃት ውስጣችን ይጸነሳል ። እግዚአብሔር ግን በስማችን ጠርቶናልና ልንፈራ አይገባንም ።
እግዚአብሔር የፈጠረን ነው ። ፍጡር ፈጣሪ እንዳለ ፣ ፈጣሪም ፍጡር እንዳለው ያስረዳል ። መድረክ ላይ ቆምን ባንሰብክም ህልውናችን ብቻውን እግዚአብሔር አለ ብሎ የሚመሰክር ነው ። እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ፍጥረትን አምጥቶአል ። በራሳችን ምክር ሳይሆን በእግዚአብሔር ምክር ይህን ዓለም ተቀላቅለናል ። የፈጠረ ከወለደ በላይ የሚወድ ነው ። እግዚአብሔር በጸጋ የወለደን አባታችን ብቻ ሳይሆን ያስገኘን ፈጣሪያችን ነው ። ሰዎች በማመን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ባይኖራቸውም በፍጡርነትና በመግቦቱ ግን የእርሱ ጥገኞች ናቸው ። የፈጠረን አለና መፍራት አይገባንም ። የፈጠረን ሳንፈጠር ያየን ነው ። የማይወደውንም የሚፈጥር የለምና ዓለም ሳይፈጠር ወዶናል ። ስለዚህ አትፍራ ይለናል ።
“የሠራህ” ይላል ። መሬት ላይ ዝቅ ብሎ ከአፈር ቅርጽ አውጥቶ የሠራን ፣ በእስትንፋሱ ሕይወትን ለግሶ ያቆመን ፣ ከአፈርነት በአፉ ትንፋሽ ያነሣን እግዚአብሔር ነው ። ያ እስትንፋስ ባያገኘን ኑሮ አፈር ሁኑን እንቀር ነበር ። የሰማይ ወራሽ የሆነው ደግሞም ቆመን የምንሄደው በአፉ እስትንፋስ ነው ። ዓይናችን በቦታው ፣ እጃችንን በቦታው ያስቀመጠ እርሱ ነው ። የሠራን የዳሰሰን ነው ። ሌሎች ፍጥረቶች ሁሉ በቃሉ ጥሪ ካለ መኖር ወደ መኖር መጥተዋል ። ሰው ግን በእጁ ተሠርቷል ። ይህንን አካሌን መለኮታዊ እጆች አበጃጅተውታል ፣ ነክተውታል ብለን ስናስብ ፍርሃትን ድል እንነሣለን ።
“የተቤዠህ” ይላል ። የሚቤዥ ዋጋ ከፍሎ የሚገዛ ነው ። እስራኤልን በዋጋ ከግብጽ ገዝቷታል ። መላውን ዓለም ራሱን በመስቀል ላይ በመስጠት ዋጅቶታል ። የተገዛ ነገር ገዥው የጥበቃ ዋስትናም ያደርግለታል ። የተገዛ ነገር እንደውም አይፈራም ፣ ገዥው ግን ሊፈራ ይችላል ። እግዚአብሔር ግን የሚሰጋው የሌለው ገዥ ነው ። እኛም ተገዝተናል ፣ ባለቤት አለንና ልንደፍር ይገባናል ።
“አንተ የእኔ ነህ” ይላል ። የእግዚአብሔር መሆን ትልቅ ነገር ነው ። የራሳችንና የሰዎች ሁነን እናውቀዋለን ። የእግዚአብሔር መሆን ግን ትልቅ ነገር ነው ። እግዚአብሔር ይህን ማንነት የእኔ ነው ሲለው ደስታ ሊሰማን ይገባል ። እኛ ራሳችን ለመቀበል የከበደንን ማንነት ፣ ይቅር ልንለው ያልቻልነውን በደለኛነታችንን እግዚአብሔር የእኔ ነው ይለዋል ። በዚህ ዓለም ላይ የእኔ የምንለውና የእኔ የሚሉን እያነሱ ነው ። እግዚአብሔር ግን የእኔ ነህ ይለናል ። እኛ የዓለምም ፣ የቤተሰብም ፣ የሰይጣንም አይደለንም ፣ የእግዚአብሔር ነን ። ስለዚህ ልንፈራ አይገባንም ። በብዙ ነገር ራሳችንን እንፈራዋለን ። እግዚአብሔር ካልሰለጠነበት ይህ ማንነታችን የሚሆነውን ነገር ገና በመስጋት እንደነግጣለን ። እኛ ግን የእኛ አይደለንም ፣ እኛ የእግዚአብሔር ነን ።
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ” ይለናል ። 1ቆሮ. 6፡20 ። የራስ መሆን ከባድ ነው ። ሥጋችን ወደ ገደል የሚነዳን ነው ። እኛ የእግዚአብሔር ነን ። ይህን የተረዳን ቀን በሥጋችን እርሱን ለማክበር እንነሣለን ። ብዙ ሰው በሥጋው እግዚአብሔርን ማክበር እንደማይችል ፣ ይህን ዓለም ካለቀቀም የእግዚአብሔር እንደማይሆን ያስባል ። መንፈስ ቅዱስ ግን ማኅደረ ሥላሴ ሊያደርገን መጥቷልና በሥጋችን እርሱን ልናከብር ይገባናል ። ዛሬ ብንወድቅም ብንነሣም የእግዚአብሔር ነንና ልንፈራ አይገባንም ። ፍርሃታችንን ድል የምንነሣበት ቀን ይሁንልን ።
የወደቀን የምታነሣ ፣ የቆሰለን አልፈህ የማትሄድ ፣ እረኛ ለሌለው እረኛ ፣ ሰሚ ላጣ አድማጭ የሆንህ እግዚአብሔር ሆይ አመሰግንሃለሁ ። ብዙ ልመና በፊት አቅርቤአለሁ ፣ የአንተን ቃል ግን በልቤ መጻፍ አልሆነልኝም ። እየተናገርከኝ እፈራለሁ ። ባትናገረኝ ምን ልሆን ነው ? ይህን ማንነቴን ውሰደውና አዲስ ልብ ፍጠርልኝ ። አንተን በማመን አጽናኝ ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 27
ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ