እበላለሁ ብለህ የምትበላው ፣ አገኛለሁ ብለህ ተዘርፈህ የምትገባው ፣ ለአንድ አንቱታ ሺህ ከፍለህ የምትወጣው አንተ ሞኙ እባክህ ተመከር። ለመቶ ብር ጉዳይ መቶ ሃምሳ ብር ጉቦ የምትከፍለው፣ መብትህን ገዝተህ የምትዘፍነው አንተ ሞኝ እባክህ ተመከር ። ሁለት ጆሮ ኖሮህ የምትባለውን ከሰማህ ሺህ ጆሮ ያለው መንግሥት የሚባለውን አይሰማም ብለህ የምታስብ አንተ ሞኝ ተመከር። ከቢጤዬ ጋር ልዋል ብለህ የክፉ ቀን ሚስትህን ፣ የጨለማ ቀን ወዳጅህን፣ ቀዶ ያለበሰህን ፣ ቆርሶ ያጎረሰህን ያንን የራብ መድኃኒትህን የካድህ ቤትህን በገደል አፋፍ ላይ ሠርተሃልና አንተ ሞኝ ተመከር ። ለኔ ቢጤ እየሰጠህ ሠርቶ ለሚያድረው ጉርሻ መስጠት የሚቆረቁርህ ከሆነ ፣ የዘመድ ጠላት እንዳለው ረስተህ ባዳ ፣ ባዳ ነው የምትል፣ “ከባዳ ጋር የበሉት በሶ ይወጣል ደም ጎርሶ” የሚባለውን ረስተህ ዘመድ የምትገፋ አንተ ሞኝ እስቲ ልምከርህ:- ወዳጅ የሆነው እግዚአብሔር ወዳጅ ይሰጣል። የሚጠላህን ታውቃለህ ፣የሚወድህን ግን አታውቅም። በሚጠላህ ሰው ትናደዳለህ በሚወድህ ሰው ግን ደስ አይልህም። እውነተኛ ዘመድና ወዳጅ የችግር ቀንህ ያልፈተነው ፣ ሕመምህ ያላራቀው ነው ። እንኳን የወዳጅ የውኃም ጡር አለውና አክብረህ ያዝ።
ስፖርተኛ ነኝ ሕመም አያገኘኝም አትበል። የጤና በረከት የእግዚአብሔር ነው። ጤነኛ ነኝ አልሞትም አትበል። አንተ ሞኝ ተመከር። ሞት ጥሪ ነው ። ስፖርትም ለተክለ ቁመና እንጂ ሞትን ለማስቀረት አይደለም። ዛሬ ያወቅኸው ሰው አይጥለኝም ብለህ ተስፋ አታድርግ ። ፍቅር ጊዜ ይፈልጋል፤ ተፈትኖ ማለፍ ያሻዋል ።
የምታምነው አምላክ በሽታን የሚገሥጽ ፣ ሞትን በትንሣኤ የሚረታ ነውና አሞኛል ብለህ ተስፋ አትቍረጥ። ያቆላመጠህ ሁሉ ወዳጅህ አይደለም። የፊት ወዳጅህንም እንደ ቀላል አትቍጠር ።
ጥሩ ሰላምታ የሰጠህን፣ አክብሮህ የደረሰልህን፣ ስታናግር ያደመጠህን፣ ስትልከው አለሁ ያለህን፣ ስታፈቅረው ለፍቅርህ ዋጋ የሰጠውን አንተ ሞኝ አታቃለው። ዕቃም ቀኑ ሲደርስ ይሰበራልና ወዳጅም ከዚህ ቀን በኋላ ቢቆይ አደጋ ሊሆን ይችላልና ሰው ከዳኝ ብለህ አንተ ሞኝ አትዘን። የማይከዳው አምላክ ካንተ ጋር ነውና አሁን ብድግ ብለህ፣ በልብህ ጉልበት እየሰገድህ አክብረው።
የወደድከውን ወገን በደንብ ሳታውቀው ከቤተሰብህ አታስተዋውቀው ። ቤተሰቧን ብረዳ አትለየኝም ብለህ ፍቅርን በጉርሻ ለማጽናት አትሞክር ። አንተ ሞኝ ዘርን ዝራ እንጂ አትበትን።
ዕርቃኑን ብታየው ሁሉም ድሀ መስሎ ይታይሃል፤ ዕርቃኑን የተወለደው ሰውም ዕርቃኑን ይሄዳልና በልብስ ሰውን አታክብር። ትልቅ ሰው መሆን እንጂ ከትልቅ ጋር መዋል ትልቅ አያደርግምና አንተ ሞኝ እባክህ ተመከር። ከእገሌ ጋር ፎቶ ለመነሣት በመንጠራራት አንገትህን አትቅጨው። የማስተዋል ጉዞ አያፀፅትምና ለልብህ ልብ ግዛለት። በትላንቱ እንቅፋት ዛሬ አትመታ። በመምህርም በመከራም ተምረህ የማትለውጥ ሰው አትሁን! አንተ ሞኝ እባክህ ተመከር።
የግል ጉዳዩ ነውና ለምን አታገባም? ብለህ ሰውን አትነዝንዝ ። ራሱ ካልነገረህ በቀር ልጆች አሉህ ወይ? ብለህ መጠየቅ አይገባም። አንተ ሞኝ በተከፈተ አፍ ራስ ይታያልና ተጠንቀቅ። ወሬ ነፋስ ነው ፣ ነፋስ አስጥላለሁ ብሎ ሲነፍስ ሰዎች የበለጠ እየለበሱ ይመጣሉ። ውስጣቸውን ለማወቅ ወሬ ስትጠማ ሰዎች የበለጠ እየተደበቁ ይመጣሉ። ወዳጅነትህ ግን ያለ ካህን ያናዝዛቸዋልና ፍቅርህን አስቀድም። ከጎረቤት ጋር እፍ አትበል፣ የተጣላህ ቀን መሄጃ ታጣለህና። ጎረቤትህን ግን በፍቅር ያዝ። ከሩቅ ዘመድ ስትጮህ የሚደርስልህ የቅርብ ጎረቤት ነውና አንተ ሞኝ ተመከር። ሞኝ ከሁሉ ይጣላልና ጠብ ቀንስ! ሁሉ ወዳጄ ነው፣ ሁሉ ጠላቴ ነው አትበል ። ማግኘትህ የሚያስደስተው ሌባን ብቻ ነው ይባላል። እርሱም ሊሰርቅህ ነውና አንተ ሞኝ አገኘሁ ብለህ አትለፍፍ :: አንተ ጋ ያለውን ክቡር ሰው ቶሎ ዕወቀው:: የሩቅ እያከበረው አንተ አትናቀው። ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል እንዲሉ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም