የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንተ ግን ….

በደቂቃ ነገሮች በሚለዋወጡበት ዓለም አንተ ግን በስፍራህ ፣ አንተ ግን በህልውናህ ጽኑ ነህ ። ሰዎች ሥሩልኝ ሳይሆን ልሥራላችሁ ቢባሉ በቅን በማይመለከቱበት ዓለም ፣ አንተ ግን የበደሉህን በፍቅር ታያለህ ። መጠባበቅ በዝቶ ፣ ጣልና ልጣልልህ የሚል የዕቁብ ኑሮ ደርቶ ቢታይም ፣ አንተ ግን ሁሉን በጸጋ ትለቃለህ ። የጸናውን ለመንቀል ፣ ያመነውን ለማስካድ ትግል ባለበት ዘመን ፣ አንተ ግን ፈሪውን ታበረታለህ ። ጻድቁን በሚያረክሰው ዓለም ፣ አንተ ግን ደካማውን ብርቱ ነህ ትላለህ ። ጀርባን እያየ ፣ “ማን አለው?” ብሎ ዙሪያን እያጠና በሚያፈቅረው ዓለም ፣ አንተ ግን የብቸኛው ወዳጅ ነህ ። ጊዜ ከድቶት አንገት ሲደፋ ፣ በወደቀው ላይ ምሣር ሲበዛ አንተ ግን መፍረድ ስትችል ትምራለህ ።

“አንቱ” ያለውን ሰው “አንተ” ለማለት በሚጣደፈው ዓለም ላይ ፣ አንተ ግን ከፍታህ ዝቅታ ፣ ክብርህ ማዋረድ የለበትም ። እጅግ የወደደ እጅግ በሚጠላበት ዓለም ፣ አንተ ግን እስከ መጨረሻው ትወዳለህ ። ያገለገለ ሰው “አህያ” በሚባልበት ዓለም ፣ አንተ ግን የተናቀውን ታከብራለህ ። ሥራን ትቶ ስፍራን በሚሻው ዓለም ላይ ፣ አንተ ግን ዝናን ታስንቃለህ ። ያልፈጠረው ላይ በሚጨክነው ዓለም ውስጥ ፣ አንተ ግን ፍጥረትህ ነውና ለሁሉ ትራራለህ ። የፈተናው ነፋስ የተሰበሰበውን ስንዴ በሚበትንበት ዓለም ፣ አንተ ግን “ትጉና ጸልዩ” ትላለህ ። በአንድ ጆሮ ሰምቶ በሌላው በሚያፈስሰው ዓለም መካከል ፣ አንተ ግን የነገሩህን ላትረሳ ትሰማለህ ። “እርሱ ነው ፣ እርሷ” የሚል ክስ በበዛበት ዓለም ፣ አንተ ግን ሁሉን ለንስሐ ትጠራለህ ።

ቃላቸውን ለመፈጸም ዳተኛ ፣ ለመድረስ ዘገምተኛ የሆኑ በበዙበት ዓለም ፣ አንተ ግን ደመና ጠቅሰህ ፣ ባሕር ተራምደህ ትደርሳለህ ። ለማክበር ተሰባስቦ በሚያዋርድ ፣ ለድጋፍ ሰልፍ ወጥቶ በሚቃወም ዓለም ላይ ፣ አንተ ግን ላታሳንስ ከፍ ታደርጋለህ ።

አንተ እንደ እኔ ፣ አንተ እንደ ሰዎች ፣ አንተ እንደ ጊዜው አይደለህም ። አንተ መግለጫ ፣ አንተ እኩያ ፣ አንተ አምሳያ ፣ አንተ ተቀራራቢ ፣ አንተ ተካካይ ፣ … የሌለህ ብቸኛ ነህ ። ያህዌ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ። የሚወድህ ሁሉ አሜን ይበል !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ሰኔ 23 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ