የዘመናት እርጅናህን ጥቁረትህ ይናገራል። ብዙ ዋዕይና ጎርፍ የቻለው ጣሪያህ እውነተኛ መልኩን አጥቷል። አንተ ዘመኑን የማትመስል የጥንት ነህ። ሰውን የምትመስል የአፈር ቤት ነህ ። ማዝመም ሲያንስህ ነው ወይ? ስንቱን ጦርነት አሳልፈህ ያለኸው አንተ ነህ። ሰዎች ገመናዬ የሚሉህ የንስሐ አባታቸው አንተ ነህ። ብዙ ምሥጢር የተሸከመ ማዝመሙ ፣ ባለ ታሪኩ በድጋፍ መቆሙ ወጉ አይደለም ወይ? ሽማግሌን ይኩሉታል፣ ጡረታም ሰፍረው ይንከባከቡታል። አረጀ ብለው አፍነው አይገድሉትም። አሮጌነት ብዙ የማየት ውጤት ነው። ፍሬ ያለው ዘንበል ይላል እኮ! አገዳዎቹ አጠገብህ ቀጥ ብለው ቆመዋል። ያንተን ያህል ዕድሜም ታሪክም የሌላቸው እዩኝ እዩኝ ብለዋል። የልጅ ልጅን ያሳደከው አንተ ጎጆ ስንቱን ችለኻል። ሰዎች ያላዩትን ሲናገሩ አንተ አይተህ ብዙ ሸፍነሃል። የሰማኸውን አላሰማህም ። እንደ አዲሶቹ አታስተላልፍም ። ድምፅ ማጉያ ሳይሆን ድምፅ ማፈኛ ተገጥሞልሃል ። አንተ ጎጆ ግዴለም ሙት። ሞት የተፈረደበት እንዲናገር ይፈቅድለታልና እባክህ ተናገር ። ጆሮ ጠገቦች አይለፍልፉ አንተ ተናገር። በልቶ ካጆች አሮጌ ነው ቢሉህ አንተ ግን ተናግረህ ሙት ።
ያደግንብህ ልጅ ያሳደግንብህ አንተ ጎጆ ተናገር ። ማርያም ማርያም እየተባለ ሲወለድ አይተሃል፣ ሬሳው ሲገነዝ እዚያው ነበርህ ። ጣሪያህ ቢያፈስም ፣ መሠረትህ ቢጎዳም ፣ የሠሩህ ባይኖሩ ፣ ዋጋ ያወጡብህና የሚቆጩልህ ጥርኝ አፈር ቢሆኑ አንተ ተናገር ። ይህን ቤቴን ለልጄ ሰጥቻለሁ ብለው ኑዛዜ ሲያጽፉ ዝም ብለህ ትሰማ ነበር። ገና ቆመህ ለመኖር ፣ ለማገልገል ፊትህ አልጠቆረም። ሰው ሲተኛ አንተ ቆመህ ነበር ። ዝናቡን ላንተ ሙቀትህን ለሰው ሰጥተህ ነበር ። በቀስታ ተሠርተህ በቅጽበት ፈረስህ። ባለሙያ ሠርቶህ ያለ ሙያ ፈረስህ። እንደ እኛ አንተም አይሞላልህም ፤ በርህ ሲጠገን ጣራህ ያፈሳል፣ ጣራህ ሲሠራ አፈርህ ይናዳል ።
አንተ የዘመን ምስክር በዝምታ የምትናገር ፣ ክቡር ዘበኛና ጦር ሠራዊት ሲታገሉ፣ ወታደርና ፖሊስ ሲናናቁ ፣ የእናት ልጆች በሁለት ጎራ ቆመህ ሲታኰሱ አንተ ምስክር ነህ። አፈር ነህና ወደ አፈር መመለስ ግድ ቢሆንብህም አንተ የታሪክ ማኅደር ዝም አትበል ። ካንተ በዕድሜ የሚያንሱት ሰዎች ምርኩዝ ጨብጠዋል፣ ተንጋደው ይሄዳሉ፣ እያነከሱ ይገዛሉ ። ያንተ ማርጀት ያንተ ማዝመም ምንም አይደንቅም ።
ልጆች ለየብቻ መኝታ ክፍል ሳይሠራላቸው አንተ ጠባቡ በግድ ታፋቅር ነበር። በአንተ ውስጥ ያደጉ እስካሁን አልተለያዩም። ስንቱን ረሀብ ስንቱን ችግር በሆድህ ይዘህ አንድ ቀን ሳትተነፍስ ለአፈር በቃህ። ማሞቂያ አይለኮስም ፣ የከሰሉ ፍም፣ ከበው የሚሞቁት ምድጃ፣ የሚጠበሰው እሸት ያንት ትዝታ ነው ። ባንተ ውስጥ የቁም ሻወር የለም፣ ያደለው ወንዝ ወርዶ፣ ሌላውም በርሜል ዘርግቶ ይታጠባል። በአሻራ የሚከፈት በር አንተ አታውቅም። ሳትዘጋ አድረህ ሌባ አይደፍርህም። የአሻራው በር ፣ ባለ ካሜራው ቤት ይደፈራል። የስፖንጅ ፍራሽ፣ የውኃ ፍራሽ ዛሬ መጥቷል። አልጋው ሲገኝ እንቅልፍ ጠፍቷል። አንተ ውስጥ ግን መደብ ላይ ተኝቶ እንቅልፍ ይወስዳል። ልክ ነው የሚቆረቁረው አሳብ እንጂ መኝታው አይደለም። ባንተ ውስጥ እንቅልፉን የተኛው ተቀስቅሶ እንጀራ ብላ አልጠገብህም ይባል ነበር። በዛሬው ጌጠኛ ቤት ግን እራት መብላት ጥሩ አይደለም ተብሏል። ገንዘብ ፍቅርን አያመጣም፣ ፍቅር ግን ገንዘብን ያመጣል። ባንተ ውስጥ ቶሎ የማይበርድ የፍቅር ፍም ነበረ። ሰውን ሁሉ በሽተኛ ያደረገው ሴራሚክ በአንተ ዘመን አልነበረም። በእበት ተለቅልቆ ፣ ሳንቃ በሰም ተወልውሎ ኑሮ ያምር ነበር።
እንኳን የሚሞት የሚታመም ብዙ እንዳልነበረ አንተ ጥቁር ጎጆ ፣ በእኛው ጭስ ጠቁረህ የናቅንህ እስኪ ተናገር። ባማረው ቤታችን የማያምር የበሽታ ዝርዝር እየሰማን ነው። ባንተ ውስጥ 120 ዓመት የሚኖር ሰው ብዙ ነበር። ባማረው ቤት ግን ዕድሜ አልተገኘም። አይ ጉድ የዛሬው ኩራት በዛ። የድሀ ልጅ ያልነበረ ባለጠጋ፣ የሀብታም ልጅ ያልነበረ ድሀ የለም። ቡና ፈልቷል እገሌን ጥሩ ይባል ነበር፣ በትንሽ ገቢ ትልቅ ግብዣ ነበር። ዛሬ ገቢው ብዙ ስስቱም ልክ የለውም። አንተ ደሳሳ ጎጆ የትላንቱን ተናገር። ጎረቤቶች ሲጣሉ ይውሉብሃል፣ መልሰው አብረው ቡና ይጠጡብሃል። ለካ የሚያጣላቸው ፍቅር ነበር ። የአንዱን ልጅ አንዱ አጥብቶ በሽታ አልነበረም፣ ዛሬ ልጅ ለመሳም አስፈቅዱ ተብለናል ግን ሞት በዝቷል። ልጅ የወላጅ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰቡ ነበር ። ዛሬ ግን ልጅ ብቸኛ ነው ።
የመጣውን ሁሉ ጉልበት ሳሙ የተባለብህ አንተ ዕድሜ ጠገብ ጎጆ ተናገር ። የመጣው ሁሉ ወንዱን አጎትህ ፣ ሴቱን አክስትህ እየተባለ ያደገ ልጅ አይተሃል። ዛሬ ግን እንደ ጋኔን ወንዝ ለወንዝ መቁጠር ደክሞናል። እኮ መሰልጠን መሰይጠን ነው ወይ? እስከ ተናገር። በጋ ሲሆን የምትቀዘቅዘው ፣ ክረምት ሲሆን የምትሞቀው የትኛው ባለ ወረቀት ምሁር ሠርቶህ ነው? ለሰው የሚሆነውን አውቀሃል። ሞቋልና ልሙቅ ቀዝቅዟልና ልቀዝቅዝ አትልም ። የአሁኑ ቤት አይቋጥርም። የመጣውን ያሰራጫል። አየሁ አላየሁም ሰማሁ አልሰማሁም የሚሉ ሰዎች ኖረውብሃል። ሰው ወገን እንዳይዝ ክብ አርገው ሠሩህ፣ መለያየት እንዳይመጣ እንጀራው ክብ ሆነ። ማስተዋል እንዳይጠፋ ብዙ ዓይኖች ያሉትን እንጀራ አብረው ይቆርሱት ነበር :: ምናገባኝ እንዳይኖር አንዱን ቤት ሌላኛው ቤት ተሸክሞት ነበር።
አንተ ጎጆ ተናገር ! አህያ በወለደች ታርፋለችና አንተ ዕረፍ ። እኛንም አሳራፊው ጌታ ያሳርፈን! አሜን።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም.