የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንድ

 

“በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት ፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ ።” አፌ. 4፡4-6።

አንድ የቍጥር ሁሉ መነሻ ነው ። አንድ ሁለት ሊከተለው ይችላል ። አንድ ግን መነሻም መደምደሚያም ሊሆን ይችላል ። እናት አንድ ናት ፣ አገርም አንዲት ናት ። አንድ በመሆናቸው ማነስን ሳይሆን ከብዛትም መብለጣቸውን ያሳየናል ። ከብዙ ወንድሞች አንዲት እናት ትበልጣለች ። አንድ ውድ ነገር ነው ። አንድ ሳያወላውሉ የሚያምኑትና የሚወዱት ነው ። እግዚአብሔር አንድ ነው የሚለው የሃይማኖት አንቀጽ ፣ መንፈሳዊ መፈክር ነው ። አይሁዳውያን እግዚአብሔር አምላካችን አንድ ነው ይላሉ ። እስላሞችም አላህ አንድ ነው ይላሉ ። ክርስትና እግዚአብሔር አንድ ነው ይላል ። ክርስትና እግዚአብሔር አንድ ነው ሲል ስለ አንድ አካል ሳይሆን ስለ አንድ አምላክ እየተናገረ ነው ። ስለ ሦስትነት በአንድነት እየተናገረ ነው ። በአይሁድና በእስልምና የአንድ አምላክ አስተምህሮ የአንድ ገጽ አስተምህሮ ነው ። እግዚአብሔር አንድ ነው ። አንድ የሚለው የአምላክን ብቻነት የሚገልጥ ነው ። 

ሐዋርያው በዚህ ክፍል ላይ ስለ አንድ ተስፋ ፣ ስለ አንድ አካል ፣ ስለ አንድ መንፈስ ፣ ስለ አንድ ጌታ ፣ ስለ አንድ ሃይማኖት ፣ ስለ አንድ ጥምቀት ፣ ስለ አንድ አምላክ ወይም የሁሉም አባት እየተናገረ ነው ። ክርስቲያኖች ሁሉ በተስፋ ያመኑ ናቸው ። ተስፋቸው የሚፈጸመው በዕለተ ምጽአት ነው ። አንድ ተስፋ አላቸው ፣ እርሱም ርስተ መንግሥተ ሰማያት ነው ። ተስፋቸው ሁለት ሲሆን መለያየት ውስጥ ይገባሉ ። አንድ ተስፋ ቆራጥ ያደርጋል ። አንዲት አካል የተባለችም ቤተ ክርስቲያን ናት ። አንድ ራስ ክርስቶስ አለና አንዲት አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን አለችው ። ለአንድ ራስ ሁለት አካል የለውምና ። አንድ መንፈስ አለ ። ብዙ ቅዱሳንና ርኵሳን መናፍስት አሉ ። እነዚህ ሁሉ ፍጡራን ናቸው ። አምላክ የሆነው መንፈስ ግን መንፈስ ቅዱስ ነው ። መንፈስ ወይም ነፋስ ነውና ሕይወት ነው ። ሕይወትነቱ ለአብና ለወልድ እንዲሁም ለፍጥረታት በሙሉ ነው ። መወለድ ከሕይወት ውስጥ የሚገኝ ሀብት ነው ። መንፈስ ቅዱስም ውሉደ እግዚአብሔር አድርጎ ይወልደናል ። ብዙ ጌቶች በዓለም ላይ ቢኖሩም በመግደል አሸንፈው ፣ የሌላውን ንብረት የራሳቸው አድርገው ነው ። ሞቶ ያሸነፈን ፣ የባሕርይ ገንዘቡ ጌትነት የሆነ አንድ ጌታ ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። 

አንድ ሃይማኖት አለ ። የሚታመነው እግዚአብሔር አንድ ነውና ሃይማኖት አንድ ነው ። ጥምቀትም ከሥላሴ የምንወለድበት በመሆኑ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንጠመቃለን ። ከአብ የሚወለደው ወልድ ብቻ ሲሆን ከሥላሴ ግን በጸጋ የምንወለደው እኛ አማኞች ነን ። ከእናት ከአባት አንድ ጊዜ እንደምንወለድ ጥምቀትም አንድ ነው ። ጥምቀትን ሁለት ጊዜ መውሰድ በእግዚአብሔር ምሥጢር ላይ ማላገጥ ፣ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ማለትም አንድ ጊዜ የሆነውን መሥዋዕትነትና ድል ማቃለል ነው ። አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ ። ብዙ አማልክት በዓለም ላይ አሉ ። እግዚአብሔርም የአማልክት አምላክ ይባላል ። አማልክት የተባሉት ግን ቃሉ የመጣላቸው ቅዱሳን ናቸው ። ቅዱሳን በጸጋ አማልክት ወይም ገዥዎች ተብለዋል ። ሙሴን ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ እንዳለው ነው ። እግዚአብሔር የቅዱሳን አምላክ ወይም የአማልክት አምላክ ነው ። የእኛ አባት የጥቂት ልጆች አባት ሊሆን ይችላል ። የሁሉም አባት ግን እግዚአብሔር አብ ነው ። 

ብዙ ተስፋ በማበጀታችን ልባችን ፍርክስክስ እያለ ነው ። አንድ ተስፋ ብቻ እናብጅ ፣ እርሱም የሚመጣው ሕይወት ነው ። ብዙ አካል አበጅተናል ። ከአጥቢያ አጥቢያ በመንከራተታችን ወጥ ቀማሽ ሆነናል ። አንዲት አካል ቤተ ክርስቲያንን አጥብቀን መያዝ አለብን ። ስለ መናፍስት በእጅጉ በሚወራበት ዘመን ፈሪዎች ሆነናል ። ሰይጣንንም ከእግዚአብሔር በላይ አክብረነዋል ። እኛ የምናምነው አንድ መንፈስ አለ ፣ እርሱም ጰራቅሊጦስ የሆነው የእውነት መንፈስ – መንፈሰ ጽድቅ መንፈስ ቅዱስ ነው ። አዋቂዎችን ጌቶች አድርገናል ። እነርሱ ጥሩ ነው ያሉንን ምግብ እንሻማበታለን ፣ መጥፎ ነው ሲሉን መልሰን እንኮራመታለን ። አንድ ጌታ ክርስቶስ ግን የልብ ሰላም ይሰጣል ። ሃይማኖት አንድ መሆኑን ዘንግተን እንደ አዲስ ምግብ ቤት ስንቀላውጥ እንደ ገበቴ ውኃ ዋለናል ። የሃይማኖት በሽታ በቀላሉ የሚታከም አይደለምና በአንድ ሃይማኖት ፣ በርትዕት መንገድ መጽናት አለብን ። ጥምቀትም ኃያል ምሥጢር ነውና በየመታጠቢያ ቤቱ ፣ በየወንዙ የወጣቶች መለማመጃ በመሆን ልንዋረድ አይገባንም ። ጥምቀትን ብቁ የሚያደርገው የቄሱ ንጽሕና ሳይሆን የሥላሴ ስም ነው ። አንድ ገዥ ፣ አንድ አባት እግዚአብሔር አለንና አባት ያደረግናቸው ዞር አሉብኝ ብለን መተከዝ አይገባንም ። 

አንድ ብሎ የሚያምን ጽኑ ነው ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ