የማወቅ ዕድሜአችን እየገሰገሰ ፣ የማመን ልካችን እየረፈደ ፣ የምግባር ሕንፃችን እያጎነበሰ ነውና እባክህ ይቅር በለን ! ስናገኝ ከእጦታችን በላይ መልሰን የምናጣ ፣ ስንደሰት ከሳቅነው በላይ የምናለቅስ ፍርደኞች ነንና አማኑኤል ሆይ ፍታን ! ለማለት የምንል ፣ ካንጀት የማንል ፣ የድሆችን ደረት እየደቃን የምናለቅስ ፣ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ የሆነብን ነንና እባክህ ለተላላነታችን አሳልፈህ አትስጠን ! መሠረት ሲመታ ቤቱ አይፈርስም ብለን የተማመንን ፣ ጣራው ሲናድ አያፈስም ብለን የተኛን ነን ፤ እባክህን ዳግም ስትመጣ ሀኬተኛ ብለህ ከምትጥለን ዛሬ በትንሹ ቀጥተህ ማረን !
ብዙ ነገራችንን ነበር ብለን ሸኘን ፤ ክርስቲያናዊ አንድነታችንን ነበረች ከማለት አቤቱ አድነን ! ከሰማይ ምድር ፣ ከወንጌል ገንዘብ ፣ ከሃይማኖት ወንዝ ሲበልጥብን እባክህን ምን ነካችሁ? በለን ። ቃላቶቻችን ሲያደሙ ፣ የነደደው ላይ ነዳጅ ሲጨምሩ እባክህን ክርስቶስ ሆይ ጥበብን አስተምረን ። ባለው ላይ መጨመር አቅቶን ያለውን በጎ ስንቀንስ ፣ ታሪክ መጻፍ አቅቶን ታሪካችንን ስናሳድፍ እባክህን በደም መፍሰስ አስበን ። ልዩ ነኝ ብለን ስናስብ ፣ እንደ አራዊት ስንነካከስ ልዩ መሆናችንን በመዋደድ እንድንገልጥ አስተምረን ። የወጣው ብርሃን ላይ ጨለማ ስንረጭ ፣ የነጋው ቀን ላይ ምሽት ስናውጅ ፣ ፀሐይ ጠልቃ ለእኔ አይጨልምብኝም ከሚል ተላላነት እባክህ አውጣን ። “እርሱ ነው ፣ እርስዋ” በማለት ፣ አሳልፎ በመሰጣጠት ነውጡ አልቆመምና ፣ እኔ ነኝ ብለን መርከቧን እንድናሳርፍ የትሕትና ልብ ስጠን !
የክህነትን ክብር ደፍረነው አስደፍረናልና እባክህን ነጩን ጥምጥም እንደ ኢያሱ ካህን አልብሰን ! ከሕይወት መዝገብ ራሳችንን እንዳንፍቀው ፣ በወርቀ ደምህ እንደ መዘገብከን እንቅር ! ለኃጢአት ተግተን ፣ ለጽድቅ የተኛንበትን ዘመን እባክህ ይቅር በለው ! ቀኛችንን ለዓለም ሰጥተን ፣ ግራ ሲገባን መጥተናልና ተቀበለን ! ደጁን ብንጸፋው ዝም አልከን ፣ ፀሐይ ያጠቆረውን ፣ ዝናብ መከራ ያበሰበሰውን መልካችንን ካየኸው አያስችልህምና እባክህ አይተህ ክፈትልን ። በልዩ የቀጣኸን በልዩ ብትመክረን ነውና እንደ ልብህ ያልሆንልህን ልጆችህን ይቅር በለን ! አንድ ዕድል ስጠን ፣ እንደገና ለምስጋና አቁመን ! በአማኑኤል ስምህ ፣ በፈሰሰው ደምህ ፣ በማርያም እናትህ ! አሜን !!!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም.