የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንድ ጠጠር ጣሉ

የእስራኤል ልጆች ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ ከወንዙ 12 ድንጋዮች ይዘው ወጡ ። ከመሬት ላይ ደግሞ 12 ድንጋዮች ይዘው ወደ ወንዙ ገቡ ። ይህ ሁሉ ሲሆን ወንዙ በተአምራት ተገድቧል ። የየብሱ ድንጋዮች በወንዙ መሐል ተቀመጡ ፣ ስውር ምስክሮች ናቸው ። ወንዙ በተመለሰ ጊዜ ይሸፍናቸዋልና። የተሻገሩት ግን ያውቋቸዋል ። የወንዙ ድንጋዮች ደግሞ በየብስ ላይ ሐውልት ሁነው ተተከሉ ። የተገለጹ ምስክሮች ናቸው ። የሚመጣው ትውልድ እነዚህ ድንጋዮች ምንድናቸው ? ብሎ ሲጠይቅ እግዚአብሔር በተአምራት ወንዙን ከፍሎ በደረቅ መሬት ማሻገሩን እንዲመሰክሩ ነው ። የእስራኤል ልጆች ከእግዚአብሔር የተማሩት አንድ ነገር አለ ። እግዚአብሔር መልካም ሲያደርግላቸው መጀመሪያ መሥዋዕት ያቀርባሉ ። ቀጥሎ ሥራው እንዳይረሳ ሐውልት ይተክላሉ ። እነዚህ ድንጋዮች ወንዙን ከፍሎ በደረቅ መሬት ላሻገረው እግዚአብሔር የሥራው መታሰቢያ ናቸው።
እግዚአብሔር ዛሬም በሥራ ላይ እንዳለ ምስክሩ አገልጋዮች ናቸው ። በስውር የተቀመጡ ፣ በአደባባይ የተገለጹ ብዙ አገልጋዮች አሉ ። ከእኛ እንጂ ከእግዚአብሔር ያልተሠወሩ አያሌ ናቸው ። በወንዙም ፣ በየብሱም የሚያስቀምጥ እግዚአብሔር ነው ።
እግዚአብሔር ሰዎችን በሰዎች በኩል ይረዳል ። ሁላችንም ብንሆን የተወለድነው በምጥ ነው ። እኛ እንድንወለድ ያማጡ አሉ ። እንዲሁም እውነት እንዲገባንና ክርስትና በውስጣችን እንዲጠልቅ ዋጋ የከፈሉልን ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ሁለትና ሦስት አይደሉም ። አንድ ሰው ነው ። ብዙ ያስተማሩን ይኖራሉ ። ብርሃን ግን ፍንጥቅ ያለልን በአንድ ሰው አገልግሎት በኩል ነው ። ዓመታት ሊርቁና ልንዘነጋ እንችላለን ። ነገር ግን ወደ እውነት ያቀረቡንን ሰዎች መርሳት የለብንም ። አሁንም ይህን ጽሑፍ ስታነቡ መጀመሪያ አንድ ጠጠር አንሡ ። ያንን ጠጠር የምታስቀምጡት ለማን ነው?
ሕይወታችሁ የተለወጠው ፣ እግዚአብሔር ማለት ለካ ይህ ነው ? ብላችሁ እንድትማረኩ የረዳችሁ በማን በኩል ይሆን ? በሕይወታችሁ አዲስ ምዕራፍ እንድትጀምሩ ፣ የቀድሞ አመለካከታችሁን ለውጣችሁ ሕይወትን በበጎ እንድታዩ የረዳችሁ የትኛው ትምህርት ፣ የትኛው መጽሐፍ ይሆን ? ከሁኔታው በላይ እንድታዩ ሰማይንም እንድታስቡ ያስቻላችሁ የእግዚአብሔር ሠራተኛ ማን ይሆን ? ወደ ኋላ የሚስበውን የዚህን ዓለም ማሰሪያ እንድትቆርጡ የወሰናችሁት በየትኛው ቀን አገልግሎት ይሆን ? ብዙ ነገር ሊረሳ ይችላል ። ይህ ግን መረሳት የለበትም ።
ያንን ሰው ካገኛችሁት ፣ ወደ ትውስታችሁ ከመጣ ፣ ስለ እርሱ ወይም ስለ እርሳቸው እግዚአብሔርን አመስግኑ ። ወደ ክፉ ነገር የወሰዷችሁን እስካሁን አልረሳችሁም ። ወደ እግዚአብሔር የወሰዷችሁን እንዴት ረሳችሁ ? ክፉ ያደረጉባችሁን ተቀይማችኋል ። ከመልካም በላይ የሆነውን መልካም ያደረጉላችሁን እንዴት ረሳችሁ ? ከተቀየማችሁ የተደረገባችሁ ክፉ ነገር ስላለ ነው ። የተደረገላችሁን መልካም ነገር እንዴት በዝምታ ታልፉታላችሁ ?
ጠጠሩን ያስቀመጣችሁለት ያ ሰው ምናልባት ዛሬ የዘራሁት አልበቀለም ፣ የተናገርኩት አልፈወሰም ፣ ወልዶ መሐን ነኝ እያለ ይሆናል ። ከፈተናና ከትግል የተነሣ ነገረ ዓለሙን ትቶ ተቀምጦ ይሆናል ። ምናልባት ብዙዎች ሲሰድቡትና ሲረግሙት እየሰማችሁ በልባችሁ ግን እየተቆጫችሁ ይሆናል ። ያልተገለጠ ፍቅር የተዳፈነ እሳት ነውና አይሞቅም ። ካልተገለጠ ፍቅር የተገለጠ ጥላቻ ይሻላል ። ያ ሰው ግን ስድቡን እንጂ ምስጋናውን መስማት አልቻለም ። የሚሰማው የሰይጣንን ክፋት ብቻ ነው ። ያገለገሉንን ማገልገል ፣ የተሸከሙንን መሸከም የማደግ ውጤት ነው ። ወላጆቻችንን የምንጦረው ለዚህ ነው ። በሥጋ ከወለዱን በመንፈስ የወለዱን ይበልጣሉ ። በሥጋ የወለዱን ለመውለድ ምንም ዓይነት የጠላት ፍላጻ አልገጠማቸውም ። በመንፈስ የወለዱን ግን ብዙ ታግለዋል ። አገልግሎት ምን ማለት መሆኑን ያገለገለ ብቻ ነው የሚያውቀው ።
ዛሬ እነዚህን ሰዎች አስቡና እግዚአብሔርን አመስግኑ ። እነርሱንም ፈልጋችሁ አክብሮታችሁን ግለጡ ። የበለጠ ይሠራሉ ። አዎ አገልጋዩን ማን ያገልግለው ? አጽናኙን ማን ያጽናናው ? ብዙዎች በኀዘንና በትካዜ ሁነው በር እንደ ዘጉ እናውቃለን ። የእናንተ ምስጋናና አድናቆት በር ያስከፍታቸዋል ። ዘመኑ የእውነት እንዲሆን እንትጋ ።
ጌታ ሆይ አንተን ላገለገሉ ብርሃን ይሁን ። አንተ የአንድ ቀንን መታመን እንኳ አትረሳም ። እንደ ሰባራ ገል ተጠቅመህ የምትጥል አምላክ አይደለህም። ለእኛ ግን ውለታ በላ እንዳንሆን ዛሬ አግዘን ።
እግዚአብሔር ያበርታችሁ ።
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ዕለተ ዓርብ ሚያዝያ 19/2010 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ