“ደግሞም ኢየሱስ፦ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው ።” ዮሐ. 8፡12።
“ተው አንጋው ተው አንጋው ብታነጋው ምነው ፣
ለተጨነቀው ሰው ቀኑም ጨለማ ነው ።”
ከዛሬ ነገ ይሻላል ብሎ ተስፋ ያደረገው ሰው ፣ ሌሊቱ አልፎ ቀን ይመጣል ብሎ የሚጠብቀው ፣ ከአራዊቱ ሰዓት ፣ ከሌባው ምጽአት መትረፍ የሚፈልገው ፣ ጨለማው ረዝሞበት ብርሃን የናፈቀው ፣ በጽልመት ውስጥ ሆኖ ጉንዳን የሚነክሰው ፣ ሚስቱ ምጥ ተይዛ የሚያቀብለው መፍትሔ ያጣው ፣ ልጁ ከእንቅልፍ ነቅቶ የሚበላ ቢለው የሚሰጠው መና የሌለው ፣ ቢጮህ የሚደርስለት ፣ ቢጣራ አቤት የሚለው ያጣው ፣ ራሱንም ዙሪያውንም ለማየት ውድቅቱ የከለከለው ፣ ፍጥረተ ዓለም አሸልቦ እርሱ የነቃው ፣ በተለመደው ሌሊት ሳይሆን በሕይወት ጨለማ የተጨበጠው ፣ እግር እያለው የማይራመደው ፣ እጅ እያለው ማጉረስ የማይችለው ፣ የኋላውም የፊቱም አልታይ ያለው ፣ አጠገቡ ማን እንዳለ ማስተዋል የተሳነው ፣ አለሁ እያሉት የሌሉ ሰዎች ያደከሙት ፣ መስጠትን አውቆ የሚያበድረው ያጣው ፣ ለሁሉ አልቅሶ የእርሱ ልቅሶ ግን አጋዥ የሌለው ፣ ትዳሩ ያመለጠው ፣ ተበድሮ ያሳደጋቸው ልጆቹ በደለኛ ያደረጉት ፣ የኖረላት አገር ሞት የፈረደችበት ፣ ያስተማረው ሕዝብ ስም የሰጠው ፣ የዘመድ ምቀኛ ፣ የወዳጅ ሸረኛ ያስጨነቀው ፣ ውኃ ይዞ ትን የሚለው ፣ ነገር ገብቶት ብቻውን የሚያወራው ፣ እምነቱ ቀዝቅዞበት ፣ ፍቅሩ የተፈተነበት ፣ ተስፋው እንደ ኩራዝ መብራት ጭል ጭል የሚልበት ያ ወገን የሚለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡-
“ተው አንጋው ተው አንጋው ብታነጋው ምነው ፣
ለተጨነቀው ሰው ቀኑም ጨለማ ነው ።”
የቀን ጨለማ ከሌሊት ጨለማ ይከፋል ። በአገሩ ብዙ ጠብቆ ተስፋው የተሰበረ ፣ ክዶ የማይክደው ቤተሰቡ ያስጨነቀው ፣ የአካሉ ክፋይ ልጆቹ ባዕድ ያደረጉት ፣ የገዛ ጉልበቱ ሲከዳው የተበሳጨው ፣ እንዴት ይህን ያደርጋል ? ብሎ በሰው የፈረደው ነገር ሁሉ እርሱን ሊገዛው የመጣበት መንጋቱን ይለምናል ። የቀን ጨለማ ወራሪ ሆኖ የመጣበት ፣ ሰዉ እየሳቀ እርሱ ያለቅሳል ። የልቤን ለማን ልንገረው ? ብሎ ከስምንት ቢሊየን ሕዝብ አንድ ሰው ያጣል ። ጠላቶቹ ጉልበታም እየሆኑ እርሱ ግን እየኮሰሰ የመጣ ይመስለዋል ። የሚያስፈራ ነገር ሳይሆን ራሱ ፍርሃት መንገድ ዘግቶ አላስወጣ አላስገባ ይለዋል ። ልቡ በድንገት ይመታል ፣ ፍጥረት ሥርዓቱን ጠብቆ እየተጓዘ ቢሆንም የተንገዳገደ መስሎ ይሰማዋል ። ሰው በራሱ ፣ በቤተሰቡና በአገሩ ሊያየው የሚፈልገው ነገር አለ ። የሚኖረውም ይህን ለማየት ነው ። ጸሎቱም፡- “ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢየሩሳሌም – የኢየሩሳሌምን ጥፋት ፣ የአገሬን ውድመት አታሳየኝ የሚል ነው ። ራሱ ታጥቦ ጭቃ ሲሆንበት ፣ እየከፈለ ሲታወክ ፣ ክብሩን በማይመጥን ስፍራ ሲውል ፣ የሚመራቸው ሕፃናት ሲመሩት ብስጩ እየሆነ ይመጣል ። ያናደደውን ሰው መራቅ የቻለ ያናደደውን ኃጢአት ግን መለየት አይችልም ። በወጣትነቱ የጸናው ቤቱ ፣ ልክ ሳይሆን ልክ ነህ ይለው የነበረው ትዳሩ አሁን ጉልበቱ ሲደክም ወቃሽ ሲሆንበት በድንገት ሊወድቅ ያህል ይንገዳገዳል ። አገር መጠሪያ ፣ መኖሪያ ፣ መቀበሪያ ናት ። አገሩ ያልተረጋጋች ቤቱ ቢረጋጋም የውሸት ነው ። ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ ይባላል ። መቆሚያው አገር ነው ። አገር የተስፋ ዳቦ እየገመጠች ስትኖር ፣ ሚሊየኖች እንደ አንድ ሰው በአንድ ዓይነት ችግር ሲያልፉ ፣ ሰንሰለታማው መከራ መቁረጫ ሲያጣ አንጋው ከማለት የበለጠ ልመና የለም ። ማንበብና መጻፍ አይችልም የምንለው ያ የገጠሩ ሰው አንጋው እያለ የቀኑን ጨለማ ለአምላኩ ያስረክባል ።
ሊያጠቁት ያሉት ኑሮ መልሶ ሲያጠቃ ፣ ራእይ እሰጣለሁ ብለው ወጥተው ራእይን ሲነጠቁ ፣ ክፉዎችን ደግ አደርጋለሁ
ብለው አቅደው እንደ እነርሱ ክፉ ሲሆኑ ብዙዎችን እናያለን ። የክፋቱ ስበት የወጣውን ሁሉ እያወረደ ፣ የጽድቅ ደቀ መዛሙርትን እያሳነሰ ፣ የኃጢአት ግብረ አበሮችን እያበዛ ይስተዋላል ። የወደቀ አስተሳሰብ የነበራቸው ግለሰቦች ጥንትም ነበሩ ። የሚበዛው ማኅበረሰብ ግን ደግ ነበርና በእነርሱ ይሸፈን ፣ ይገሠጽ ነበር ። ዛሬ የማኅበረሰብ ውድቀት እያጋጠመ ሲመጣ ተው ባይም እየጠፋ ነው ። አዎ ነግቷል ብዙ ሰው የመሰማራት አቅም የለውም ። የሚታየው ብርሃን ወጥቷል ፣ የማይታየው ጽልመት ግን ቀኑን አጨልሞታል ። ቀኑን ለመግፋት ሰው ሁሉ ሲፈርድ ይውላል ። በሥልጣኑ ሊገቡበት የማይወደው አምላክ ፍርድ የእርሱ ገንዘብ ናትና የሚፈርዱትን ሰዎች ሳይቀጣ አይቀርም ። የሚገርመው ፈራጆቹን ጥሎ የተፈረደባቸውን ያነሣል ። በዚህ ሁሉ የቀን ጨለማ ፣ ንጋትን በሚያስናፍቀው ጽልመት እውነተኛው ብርሃን ማን ነው ? ቦግ ብሎ የማይጠፋው ፣ ቀጥሮ የማይቀረው ፣ መጣሁ ብሎ የማይረሳው ፣ አስጠብቆ እልም የማይለው ፣ ቃል ገብቶ ቃሉን የሚፈጽመው እውነተኛው ብርሃን ማን ነው ? የቀኑን ጨለማ የሚዋጋው ፣ በተስፋ የሚባርከው ፣ ንጋትነቱ የማይመሸው ፣ ለልብም የሚያበራው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።
አንተ የሕዝብ ንጋት ሆይ ድመቅ ፣ አንተ የብርሃን ትንታግ በየሰው ቤት ላይ እረፍ ፣ አንተ የምታድን እሳት ገለባነታችንን አስወግድ ። ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታችን ሆይ እንወድሃለን ። አሜን ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም.