የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አዋቂ ነህ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ግንቦት 5/2007 ዓ.ም.
አንተ አዋቂ ነህ፣ ያለፈውን፣ ያለውን፣ የሚመጣውን ታውቃለህ። ላለፈው ምሕረት፣ ላለው ጽናት፣ ለሚመጣው ተስፋ ትሰጣለህ። የተሸፈነውን ሳትገልጥ ታያለህ፣ ልብን ሳታስፈቅድ ትመረምራለህ። ለሰው የተሸፈነ ለአንተ ግን የተገለጠ ነው። የማትፈታው ቋጠሮ የማትለየው ቅኔ የለም። መጨረሻውን አይተህ ትጀምራለህ። የሚገዳደርህን ትጥላለህ። አታልፍም ብሎ በር የሚዘጋብህ፣ አታውቅም ብሎ የሚሸፍንብህ ማንም የለም። ሁሉን ትመረምራለህ፣ ሁሉን ትገዛለህ። ብዙ የሚያውቁ ሁሉን አያውቁም። የሚያውቁ ማድረግ አይችሉምና ሀዘነተኞች ናቸው። አንተ ግን ማድረግ የምትችል አዋቂ ነህ። ዓይናችንን ብንገልጥም ብንጨፍንም ከምናየው የማናየው ይበዛል። አንተ ግን ታይልናለህ። ሁሉን ብንጎረጉር ከምንሰማው የማንሰማው ይበልጣል። አንተ ግን ትሰማልናለህ። ከሞት ጉድጓድ፣ ከጥፋት ሸለቆ ትመልሰናለህ። ከብዙ ዘመናት በፊት ዛሬን አይተህ ለቀኑ የሚሆነውን ያዘጋጀህልን በእውነት አዋቂ ነህ። የሚወዱን ከሚጠሉን የተሻሉ ስለሆኑ አይደለም፣ አንተ ፍቅርን ስለሰጠሃቸው ነው። አንተ አዋቂ፣ አንተ ስንዱ ጌታ፣ የዘላለም ምክር ያለህ፣ የማትነካው ጥልቀት፣ የማትደርስበት ከፍታ የለም። ከእውቀትህ ያመለጠ አልሰማንም፣ ከአድማስ አድማስ ዓይኖችህ ያያሉ።
አንተ አዋቂ ነህ። መጠየቅ ሳያሻህ ሁሉን ታውቃለህ። ድፍድፉን አሳብ ከልብ ላይ፣ ያልተጣራውን ማንነት ከኩላሊት ላይ ታያለህ። አንተ ልብና ኩላሊትን ትመረምራለህ። በእርግጥ አዋቂ ነህ። ጨለማ ባንተ ዘንድ አይጨልምምና፣ የተሰወረው በፊትህ አደባባይ ነውና፣ ጣራና ልብስ አይሸፍንህምና፣ ሽንገላ አያታልልህምና፣ በርና ዘበኛ አይመልስህምና፣ ከልባችን የምትልቅ አዋቂ ነህ። ከድሃ ጎጆ እስከ ቤተ መንግሥት ታንጎዳጉዳለህ። የኮራብህን አውርደህ ምስኪኑን ደግሞ እስከ ጊዜው ትሞክረዋለህ። ጽዋን ስታለዋውጥ የማይከብድህ፣ ብይን ስትሰጥ ቀኑ የማይመሽብህ፣ በፀሐይ የማትቆጥረው ራስህ ፀሐይ የሆንከው ጌታ ነህ። አዋቂ ነህ፣ የምንፈልገውን ሳይሆን የሚያስፈልገንን ትሰጣለህ። የሰማነውን ሳይሆን ለተሰማን ነገር ማጽናናት ትልካለህ። አንተ አዋቂ የብዙ ምክር መገኛ ነህ። ሲያልቅ እንዳንጀምር፣ ሳያልቅ እንዳናቆም በእውቀትህ አድነን። በበጋው እንዳንዘራ፣ በሰኔ በሬ እንዳንፈታ እባክህ አዋቂ አድርገን። በእኛ የምትሠራውን ሥራ ከፈጸምህ እባክህ ሰብስበን። አንተ ጨርሰህ ከኖርን የተሠራውን ለማፍረስ ነው።
ምክር ሳትሻ ሁሉን የፈጠርህ፣ በእውቀትህ የተመሰገንህ ሆይ ስለሚሆነው ምን ትላለህ? አንተ አዋቂ ነህ ሁኔታን ሳይሆን እውነትን ትናገራለህ። ምክር ሳያሻህ የፈጠርህ፣ ምስክር ሳትሻ የምትፈርድ፣ ትምህርት ቤት ሳትከፍት የምታስተምር፣ ሳትቸገር የምታሳልፍ፣ ለምን? ሳትባል ሁሉን የምታደርግ ኃያል አዋቂ ነህ። ያስጨነቀንን ዘመን በመልካም ዓመት ትተካለህ። ራስህን ያለ ምስክር አልተውህም። ሰው ዝም ቢል ክረምትና በጋ ሌሊትና ቀን ያንተን አስተዳዳሪነት ይናገራሉ። ለማላውቀው ለእኔ አዋቂ ነህ፣ ባውቅም ለማልለውጠው ለእኔ ኃያል አዋቂ ነህ። በእውቀትህ ጽናት ትራመዳለህ፣ በእውቀትህ ዋስትና ትሰጣለህ። በእውነት አንተ ታውቃለህ ማለት የሁሉም ጥያቄ መልስ ነው። ጌታ ሆይ በእውቀትህ አሳርፈኝ። አንተ ሳታውቅ የሚሆን አንዳች የለም፣ አንተ ካወከው የሚያስፈራ አንዳች ነገር የለም። ሳያውቁ የሚጠሉን ባሉበት ዓለም በእርግጥ አውቀህ የምትወደን አንተ ልዩ አዋቂ ነህ። ስለ እውቀትህ ምስጋና እናቀርባለን። ለዓለምና ለዘላለሙ አሜን።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ