መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » አያሳዝንህም ወይ ?

የትምህርቱ ርዕስ | አያሳዝንህም ወይ ?

ወጥቶ መግባት ያቃተው ያንተው ፍጡር አይደለም ወይ ? አስገባሪዎች በዝተውበት ለመኖር እየከፈለ ያለው ያንተው ወገን አይደለም ወይ ? ይመጣል እያሉ ሲጠብቁት መንገድ የቀረው ፣ ማዶ እየተያየ አባት እናቱን መቅበር ያቃተው ፣ እንደ ደራሽ ውኃ ዘመኑ የለየው ፣ ቅርቡ ሩቅ የሆነበት ፣ ምን ይመጣ ይሆን ? እያለ በስጋት ባሕር የሚዋኘው ፣ ከጉድለቱ የሚሰጠው ያ ምስኪን አያሳዝንህም ወይ ? ብቅ ሲል ፣ ለማየት ሲያሳሳ በጦርነት ሰይፍ የሚቆረጠው ወጣት ያንተው ቡቃያ አይደለም ወይ? በሚጫወቱበት ዕድሜ በጥይት ድምፅ የሚሸበሩት ፣ ከትምህርት ቤት የቀሩት ፣ ከቤት አትውጡ ተብለው ዓለም የጠበበባቸው ፣ የፍርሃት ብዛት የሚሰሙት ለጋ ሕፃናት ያንተው አትክልት አይደሉም ወይ ? ፍጡር ቢጨክን ባይፈጥር ነው ። አንተ እኮ ፈጣሪም አባትም ነህ ። በዋለበት ልብሱ የሚያድረው ፣ መንጋቱን የሚጠራጠረው ፣ ልጆቼን ምን ውስጥ ልክተታቸው ? የሚለው ፣ በቁሙ የሚቃዠው ፣ ጨርቅ ሳይጥል የሚለፈልፈው ፣ ዕድሜ ለመከራ የጻፈው ያ ገበሬ ያንተው ምጽዋተኛ አይደለም ወይ ? አያሳዝንህም ወይ ? ችግር ጅራፍ ይዞ ሌትና ቀን የሚለበልበው ፣ ቀኑ እሳት ሁኖ የሚያከስለው ፣ ጠፊውን እንጀራ አጥቶ የሚሳቀቀው ፣ በገዛ ወገኑ ወገን አልባ የሆነው ምስኪን ያንተው አይደለም ወይ ?

አያሳዝንህም ወይ ?

ቀኑ እንደ ተለቀቀ አውሬ የሆነበት ፣ እንደ ደራሽ ውኃ ጭንቅ የሚያሰጥመው ፣ ለራሱ ትቶ ለወለደው የሚጨነቀው ፣ በሞቱት እየቀና ቀኑን የሚጠብቀው ያንተ አይደለም ወይ ? ምድርና ሞላው የእግዚአብሔር ነው ተብሎ ተጽፎአል ። ሰው ግን የእኔ ነው እያለ መሰሉን ይገፋዋል ። መንገድ የእግዚአብሔር ነው ሲባል ኖሯል ። ሰው ግን የእኔ ነው እያለ ያግተዋል ። አያሳዝንህም ወይ ? ይህ ሁሉ ያንተ ተስፈኛ አይደለም ወይ ? ምድር ከከዳች ማን ያርፋል ፣ ወገኑ ከገፋው ወዴት ይሰደዳል ? አላቃሽ ያጣው ፣ ብቻውን የሚቆዝመው ፣ የባሰ አታምጣ እያለ ነገን የሚፈራው ያንተው የእጅህ አዳሪ አይደለም ወይ ? ይመጣል ያለው ተስፋ የዘገየበት ፣ አዲስ መከራ የሚጫንበት ፣ ባሳደገው ልጅ ፣ በሳመው ብላቴና የሚጨነቅ ያንተው አይደለም ወይ ? ቀኑን እንደ ተራራ ፣ ኑሮን እንደ ቋጥኝ የተሸከመው ፣ የጠገበው እንብላ የማይለው ፣ መሰላል ላይ የወጣው ቁልቁል የሚያየው ፣ አበባው ፍሬ ላይ ያልደረሰው ፣ ሁሌ የምትመኝ አገር የያዘው ያንተ አይደለም ወይ? በሰጠኸው ቀለም ፣ ሁን ባልከው ማንነት የሚሰደደው ያንተው አይደለም ወይ ? የባዕድን ድንበር ገፍቶ የማያውቀው ፣ አትንኩኝ ብቻ የሚለው ፣ በባዕዳን ሞት የሚደገስለት ፣ መኖሩ የማይወደድ ፣ ያ እየራበው ነጭ የሚለብስ ፣ እየተሰቃየ ለዝማሬ እልል የሚል ጎበዝ ወገኔ ፣ የአገሬ ሰው ያንተ አይደለም ወይ?

አያሳዝንህም ወይ?

ተመኝቶ አፈር የሚታቀፈው ፣ ጠብቆ ጠብቆ በአዲስ አለንጋ የሚገረፈው ፣ ሰማይ የጠቆረበት ፣ ምድር ከድታው በሰው አገር በረሃና ባሕር የሚሰጥመው ያንተ አይደለም ወይ ? በውስጡም በውጩም የሞትን ድምፅ የሚሰማው ፣ በሰው በረሃ አገር ምን ልትሠራ መጣህ ተብሎ ገመድ የሚፈረድበት ፣ ሞቱ ተቆርቋሪ ፣ መገፋቱ ፍትሕ ያላገኘው ፣ የረሀብ መዝገበ ቃላት ሁኖ ስሙ የተጻፈው ፣ ኖሮ ያልደላው ፣ ተሰዶ ማነህ የሚባለው ፣ ሞቱ ዕረፍት ያጣው ያንተው አይደለም ወይ? የጠገበ ጠግበሃል የሚለው ፣ ያገኘ ምን አለብህ ብሎ በቍስሉ የሚስቅበት ያንተው አይደለም ወይ ? ያከበረው የሚያዋርደው ፣ የቆረሰለት ሞት የሚደግስበት ፣ የገዛ ትውልዱን የባዕድ ነውር ጠርጎ የወሰደበት ፣ ከሁሉ ሳይሆን የቀረው ፣ ወይ ሃይማኖቱን አሊያም ሥልጣኔውን አንዱን መያዝ አቅቶት በነፋሳት የሚንገላታው ያንተው አይደለም ወይ ?

አያሳዝንህም ወይ ?

ወላጆቹ የእነርሱ ያልሆነውን ልጅ ልጄ ብለው ያሳደጉ ፣ እንግዳን ጠቦት አርደው የተቀበሉ ፣ ከትርፋቸው ሳይሆን ከጉድለታቸው የሰጡ ፣ የወደቀ ሲያዩ የእኔ ልጅ ቢሆንስ ብለው ደረት መትተው ያለቀሱ ፣ የሞተውን አልረሳም ብለው ተዝካር ያወጡ ፣ ይሉኝታ ይዟቸው የበሉት አንቋቸው ለሌሎች የኖሩ ነበሩ ። ወላጆቹ ባርነትን ለትውልድ አናወርስም ብለው ነፍሳቸውን የሰጡ ፣ ዓይናቸው ባያይም በጨለማ ወደ ቤተ ክርስቲያን የገሰገሱ ፣ ከአውሬ ጋር ታግለው ለምድር የጸለዩ ነበሩ ። ባካናው ትውልድ ፣ ፍቅርን በገንዘብ የለወጠው ምስኪኑ ወጣት ፣ ሃይማኖት ካላቸው የተወለደው ሃይማኖት አልባ አያሳዝንህም ወይ ? በልቶ የሚክድ ፣ የራሱን የግሉ ፣ የሌላውን የጋራው የሚያደርግ ከእነዚያ ቡሩካን አብራክ ሲገኝ አያሳዝንህም ወይ ? ኢትዮጵያዊ መልኩን ፣ የሚያምረውን ብዙህነቱን እንደ መቅሰፍት ሲቆጥር ፣ እኔ ብቻ ልኑር ብሎ ሲያስብ ፣ ስፋቱን በመጥበብ ፣ ደግነቱን በሴራ ሲለውጥ አያሳዝንህ ወይ ? ከምድሩ አልጠበበን ፣ ከአየሩ አልበደለን ፣ ሁሉ እያለን ሁሉም የሌለን ስንሆን አያሳዝንህም ወይ( የታመመው አይድን ፣ የተጣላው አይታረቅ ፣ የወጣው አይገባ ፣ የተዋደደው አይዘልቅ ፣ የነገደው አያተርፍ ፣ ያመነው አይጸና እባክህ ይህን ዘመን ለውጥ!

በል አንተ ጌታ ነህ ። ከሎሌ ስህተት ከጌታ ምሕረት አይታጣም ። አንተ ትልቅ ነህ ፣ ከእኛ ጋር ወርደህ ሒሳብ ለመተሳሰብ ክብርህም አይፈቅድም ። የእኛን ተወውና ያንተን አድርግልን ። የበረሃው ጉዞ ፣ የሲናው መንገድ ይጠርልን ። መሪን የምንበላ ፣ የወጣው የማይገባ አይሁንብን ። ሊቅን የምንቀብር ፣ ካህንን የምንወግር መሆን ከእኛ ይራቅ ። እንዲህ ስንሆን አያሳዝንህም ወይ ? እባክህ ታረቀን ።

ግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ