“እሾሁን ውኃ የምናጠጣው ለጽጌረዳው ብለን ነው ።”
ሕይወት የምታሳሳ አበባ፣ የምታደማ እሾህ ናት ። ውበት አጥሩ እሾህ ነው ። አገልጋይ እንኳ ጸጋ አለኝ ብሎ እንዳይኮራ የሥጋ መውጊያ ይሰጠዋል። ያንዳንዱ ሰው መውጊያ እንደ ሶቅራጥስ ትዳሩ፣ የሌላው ሰው መውጊያ እንደ ጳውሎስ በሽታው ነው ። መውጊያ በሁሉ ሙሉ ነኝ እንዳይሉ ያሳስባል። እጅግ ቆንጆ የሆኑ ንግግር ላያውቁ ይችላሉ። ጠባያቸው እንኳን ሰው ወፍ የሚያለምድ አይቆረቍሬ ተብለው የሚጠሩ ሰዎች መልከ ቀና አይደለሁም ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። አገሩን የገዙ ቤታቸው ያመልጣቸዋል። ደጎችም ለራሳቸው ክፉ ናቸው። ምንም ባይኖረኝ እናቴ አለችልኝ ይላሉ፣ ሀብቱ ሲገኝ እናት ትሞታለች። እንጀራ ያገኘሁበት አገር ነውና አሜሪካን እወደዋለሁ ይባላል፣ ቀጥሎ አገሬ ናፈቀኝ የሚል ልቅሶ ይጀመራል። ወላዶች ለልጆቻቸው መመገብ አቅቷቸው መንገድ ላይ ይጥላሉ፣ የልጆች መኝታ ቤት አዘጋጅተው የሚጠብቁ ሳይወልዱ ይቀራሉ። ሴትዬዋ:— “አልጋው ሲገኝ ባሉ አይገኝ” ብላለች ። ዓለም ሙሉ ብትሆን ስሟ መንግሥተ ሰማያት ይባል ነበር።
እንቅልፍ ያላቸው አልጋ የላቸውም፣ ከውጭ አገር አልጋ ጭነው ያስመጡ እንቅልፍ ርቋቸው ሲባዝኑ ያድራሉ። ጤና ያላቸው ገንዘብ የላቸውም፣ ገንዘብ ያላቸው ጤና ፍለጋ በሰው አገር ላይ ናቸው። ቁመናቸው ሸበላ የሆነ ልብስ የላቸውም፣ ልብስ ያላቸው ቁመና ያንሳቸዋል። በደጅ የወደቁ ለቤት አብቃን፣ ጠላቴ ቤት ያግኝ ይላሉ፣ ቤት ያገኙ በየሆቴሉ ሲዞሩ ያድራሉ። ትዳር ያልያዙ መሰብሰብ ያምራቸዋል፣ ትዳር የያዙት የመወጪያው በር ይናፍቃቸዋል። ድህነት አንድ ያደረገውን ቤተሰብ ማግኘት ይበትነዋል። በጭንቅ ልጆቻቸውን ያሳደጉ ጭንቁ ሲያልፍ ልጆቻቸው ለሞት ይፈላለጋሉ። ድሀ እናቴን ትኩስ እንጀራ በበላኋት የሚል ልጅ አለ፣ ሀብታም ወላጅ ያለው እናቱ ሞታ ለመውረስ ያቆበቆበ በቅርባችን አለ። ዓለም ሙሉ ብርሃን አይደለችም። ማሩ እሬት፣ ወተቱ ጥቁረት አለው። ማኪያቶ የምንወደው ዓለም ብርሃንና ጨለማ፣ ሕይወት የውበትና የእሾህ ድብልቅ መሆኗን ስላወቅን ነው።
ጽጌረዳን ብንወዳትም የማንወደው እሾህ ግን አጠገቧ አለ። እሾሁን ለማጥፋት እሳት ብንለኩስ ጽጌረዳዋም አብራ ትቃጠላለች። ሕይወት ከትግል ጋር ከተዋሐደች ቆይታለች። ተዋሕዶ ነውና ትግሉ እንዳያጠፋት፣ እርስዋም ትግሉን እንዳታጠፋው በመጠባበቅ ይኖራሉ። ሕይወት ጽጌረዳ ነበረች፣ እሾህ ይብቀል የሚል ርግማን የተሰማው ከአዳም በደል በኋላ ነው። የሰው ልጅ በደል ይጣፍጠዋል ፣ ውጤቱ ግን ይመረዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሕይወትን ያለ ትግል፣ ጽጌረዳን ያለ እሾህ ማግኘት አልተቻለም። እሾሁ ባይኖር ጽጌረዳን ሁሉ ቀጥፎ ይጨርሳት ነበር። ሰውን ረጅም ዘመን የሚያቆየው ፈተና ነው። ፈተና ደረጃንና ቊጥርን ይጨምራል።
ከምንወደው ነገር አጠገብ የሚገጥመን እሾህ የልቅሶ ርእሳችን ሆኗል። የምንወዳቸው ሰዎች የራሳቸው እሾህ አላቸው። የእኛን እሾህ እንደ ታገሡት የእነርሱንም እሾህ መታገሥ አለብን ። በሚገርም ሁኔታ የምንወዳቸው በእሾህ መካከል የተቀመጡ ናቸው፣ እነርሱን ለማግኘት ስንል የሚወጋን እሾህ አለ።
ሕፃን ልጅን አጥበው ያወጡታል እንጂ ከእጣቢው ጋር አብረው አይደፉትም። ሕይወትንም ጣዕሟን ለማግኘት ምሬቷን መቋቋም ይገባል። ፈተናውን ደፋሁ ብለን ሕይወትን አብረን እንዳንደፋ መጠንቀቅ ይገባናል። እሾሁ ከወጋን ጽጌረዳዋ ጋ ደርሰናል ማለት ነው። መወጋት የመድረስ፣ የማደግ ምልክት ነው።
ለሕይወት ብለን፣ ያስቀመጠንን እግዚአብሔር ላለማሳፈር ብለን የምንታገሠው ነገር አለ። እሾሁን ውኃ የምናጠጣው ለጽጌረዳው ብለን ነው። ልጃችንን ያገተውን የምናባብለው ለልጃችን ብለን ነው። ሁልጊዜ ድል በመግፋት ብቻ አይገኝም። ዘወር ማለትም የድል ምሥጢር ነው። ቍጣ ካፋችን ሊወጣ ሲል ቤቱን ለቀን እንውጣ። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ቁጣ አፍሮ ይሄዳል። “ወንድ ወደሽ ጢሙን ጠልተሽ” እንዲሉ ሕይወትን ወዶ ትግሉን ጠልቶ አይሆንም።
“በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፥ በርቱ ልባችሁም ይጥና ።” መዝ. 30:24
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም.