መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » አይደክምህም ወይ?

የትምህርቱ ርዕስ | አይደክምህም ወይ?

ሁልጊዜ በሥራ ላይ ነህ ፣ የማትሠራበት ቀን፣ የማትሠራለት ፍጥረት የለም። ሰውና እንስሳው አንተን ይጠባበቃል። ለሁሉ አንዱ ትደርሳለህ። ሁሉን በአንዱ ክንድህ ትጋርደዋለህ ። ይህን ሁሉ ስትከውን አይደክምህም ወይ? ዘላለም እንቅልፍ የለብህም፣ ከፀሐይ ይልቅ በሁሉ አገር ሰልጥነሃል፤ በመንግሥተ ሰማያትም ራስህ ታበራለህ። የፀሐይ ፀሐይ አንተ ነህ። የማትጠልቅ ጀምበር፣ እንደ ተወደድህ የምትቀር አንተ ብቻ ነህ። ሰው ሁለት ቃል ያናግራል፤ የፊት ምስጋና ለኋላ ሐሜትም ያስቸግራል። ሁለት ቃል የማታናግር የሰዎች ሰው አንተ ነህ።

ሁሉን ስትወድ አይደክምህም ወይ? ሰዎች ክፉ የሚሉት ዘንዶም ምግቡን ካንተ ያገኛል። ከመልካምነትህ የወጣ ነውና ተፈጥሮ ቅዱስ ነው። ምርጫው ካረከሰው በቀር የሰው ትንሽ የለውም። ድሀ ባለጠጋን እኩል መውደድ ትችላለህ፣ ሁሉም በፊትህ ነዳይና ለማኝ ነውና። በራሱ ይኑር ብለህ ፍጥረትን ያለቀቅኸው በራሱ መኖር ስለማይችል እንጂ አንተ ጨቋኝ ስለ ሆንህ አይደለም። ፍጥረት ያላንተ አንካሳና አቅመ ቢስ ነው። ሁሉን በቃልህ የደገፍከው አንተ ነህ።

ስንቱን አደፋፍረህ ከቤት ታወጣዋለህ፣ ስንቱን አባብለህ ታስተኛዋለህ። ለበሽተኛው አልጋ ታነጥፋለህ። ያንተ ስፍራ ፣ የተወሰንህበት ክልል የት ነው? ከብሶተኛው ጋር ተበድለሃል፣ ከዳኛው ጋር ፍትሕ ትሰጣለህ። የት ነው አገርህ? ያንተ ያልሆነ ሕዝብስ የትኛው ነው? አንተ የማታስፈልገው በራሱ የቆመ ኩሩ ማነው? አንድ ቀን ውኃ ካላገኘ የሚበላሽ ፍጡርስ እንዴት በአንተ ላይ የድፍረት ቃል መናገር ይችላል?

አንድ ሆነህ ሁሉን ታጠግባለህ። ሁሉ የእኔ ሲልህ ለሁሉ ትበቃለህ። እባክህን ዕረፍ አይደክምህም ወይ? አንድ ሰው መሸከም አቅቶን ደክመናል፣ ይህን ሁሉ ፍጥረተ ዓለም ለሆዱ እንጀራን፣ ለኃጢአቱ ይቅርታን፣ ለመንፈሱ እርካታን ትሰጠዋለህ። ለእኔም እዘኑልኝ ደክሞኛል አትልም። እያንዳንዱ የዝናብ ጠብታ ባንተ ይታወቃል፣ ለበረሃውም ታዝንለታለህ። በረዶ ላይ ለሚኖረው ፀጉር ታለብሰዋለህ፣ የበረሃውን እንስሳ መላጣ ታደርገዋለህ። ማንን የት ቦታ መላክ እንዳለብህ ታውቃለህ። አክባሪዎች እንጂ አማካሪዎች የሉህም። ያልከውም ይሆንልሃል፤ ጅምርህ ይፈጸማል። ይህን ስፍራ ሳትለቅ የምድር ጥግ ትገኛለህ። ጠፈርን ለመንካት መንጠራራት የለብህም፣ ሰንበትን ለሰው የሰጠህ ሰንበት የለብህም። አይደክምህም ወይ?

እኛ ለአንድ ሰው ምግብ ለመሥራት ይደክመናል። አንተ ግን ለሁሉ ታበስላለህ። እጅግ የተዋብህ ብትሆንም ኃጢአት ያጎሳቆለንን እኛን ትወደናለህ። ብዙ ወደኸን ትንሽ ብንወድህም አትጠላንም። የነገሥታት ምክር ላይ ተገኝተህ ታዳምጣለህ፣ ከተመራማሪዎች ጋ በቤተ ሙከራ ትገኛለህ ። ጠባቂዎችን ትጠብቃቸዋለህ። ቤተ ሠሪ አንተ ነህ ፣ ቤቱንም ሰውየውንም የሠራኸው አንተ ነህ። ያንተ ሥራ ግሩም ነው። ቤትን ያለ ምሰሶ ታቆማለህ፣ ምድርን ያለ መሠረት ታጸናለህ። ባንተው ሀብት ነዳጅና ወርቅ፣ እህልና መድኃኒት በውድ ይሸጣል። ሁሉ ነዳይ ሳለ ባለጠጋና ድሀ አገራት ይባባላል። ሁሉን ሳትታዘብ ታኖረዋለህ። የሰውን ድካሙን አንተ ታውቀዋለህ። እኛ የሰው የቁንጅናው፣ የጉልበቱ፣ የሥልጣኑ ወዳጅ ነን። አንተ ግን ራሱን ሰውዬውን ትወደዋለህ። ወርቅ አይደልልህ ፣ ጎበዝ አያሸንፍህም። የተጣላህን ታባብለዋለህ፣ ምንም ላታገኝ ላድንህ ብለህ ትለምናለህ። አፍቃሪ ነህ ግን ተለማማጭ አይደለህም። መሐሪ ነህ፣ ዓመፀኞችን ግን ትቀጣለህ። ትመለሳለህ፣ ከሄድህ ግን አትጸጸትም። ታኖራለህ ግን ምክንያት አትሻም። ትሰጣለህ፣ ግን አትቆጥረውም።

ክረምትና በጋውን ስታፈራርቅ አይደክምህም ወይ! ተኝተን ትጠብቀናለህ። እንቢ ብለን ስንርቅህ ብዙ ዘመን ደጅ ደጁን ታያለህ። በገዛ በረከትህ ስንክድህ አሁንም ታፈቅረናለህ። ጠባያችን እንዴት አላደከመህም?!

አይደክምህም ወይ? !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 3 ቀን 2018 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ