ኃጢአት የመንገድ እንቅፋት ሊሆን ይችላል ፣ የሕይወት ግብ ከሆነ አደገኛ ነው ፡፡ ቁሳቁስ ስኬት ሊሆን ይችላል ፣ ሕይወት ከሆነ አደገኛ ነው ፡፡ ወዳጆች የሚያስደስቱ ሊሆኑ ይችላሉ ፣ እግዚአብሔርን የሚተኩ ከሆኑ ግን አደገኛ ነው ፡፡ በሥራ መትጋት መልካም ነው ፣ ቤተሰብን መበተን ግን አደገኛ ነው ፡፡ ትምህርት አስፈላጊ ነው ፣ ሳይማር ያስተማረን ወገን የምንንቅበት ከሆነ ግን አደገኛ ነው ፡፡ በሰው አገር መኖር ምቾት ሊኖረው ይችላል ፣ የወገንን ፍቅር በምቾት መለወጥ ግን አደገኛ ነው ፡፡ ፖለቲከኞችን መቃወም ጊዜው የፈቀደው ሊሆን ይችላል ፣ አገርን መጥላት ግን አደገኛ ነው፡፡ ከዝሙት ለመራቅ ከተቃራኒ ጾታ ጋር በገደብ መኖር መልካም ነው ፣ ተቃራኒ ጾታን መጥላት ግን ተገቢ አይደለም ፡፡ ገንዘብ ለማግኘት መትጋት ተገቢ ሊሆን ይችላል ፣ ያለ ገንዘብ አልኖርም ብሎ ማሰብ ግን አደገኛ ነው ፡፡ ኑሮን በሥርዓት መምራት ተገቢ ነው ፣ ቤተሰብን እያስራቡ ገንዘብ ማጠራቀም ግን አደገኛ ነው ፡፡ ሰውን ማስደሰት መልካም ነው ፣ ሰውን ሁሉ ማስደሰት ግን አደገኛ ነው ፡፡
ንግግር መቻል ጸጋ ነው ፣ ተናጋሪ ብቻ መሆን ግን አደገኛ ነው ፡፡ እውነትን መያዝ የማይገኝ ዕድል ነው ፣ ሌላውን መቃወም ግን አደገኛ ነው ፡፡ ማፍቀር መልካም ነው ፣ ማምለክ ግን አደገኛ ነው ፡፡ ተስፋ መስጠት መልካም ነው ፣ መልሶ መቆጨትና ማዘግየት ግን አደገኛ ነው ፡፡ ትዳር መልካም ነው ፣ መውረጃ ፌርማታ መፈለግ ግን አደገኛ ነው ፡፡ ምንኩስና ዘመንን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው ፣ ከነቆብ መዝለል ግን አደገኛ ነው ፡፡ አንድን ነገር ከልብ መያዝ መልካም ነው ፣ ከእርሱ ውጭ ሌላ ማሰብ አለመቻል ግን አደገኛ ነው ፡፡ ራስን መካድ ክርስትና ነው ፣ ራስን መጣል ግን አደገኛ ነው ፡፡ ሰውን ማዳመጥና ማማከር መልካም ነው ፣ የሰውን ምሥጢር መሰርሰር ግን አደገኛ ነው ፡፡ አለመበደል መልካም ነው ፣ ካፈርኩ አይመልሰኝ ማለት ግን አደገኛ ነው ፡፡
የደስታ ቋጠሮ/11
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 5/2010 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን