ይቅር በለኝ አዳምጣለሁ ። ያንተን ቃል አይደለም ፣ አሉታዊ ድምፅን ፣ ከውስጤ የሚያስተጋባውን የአለቀልህን ነጋሪት አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ነፋሱ መንቀሳቀስ ፣ ፀሐዩ መፈንጠቅ ፣ ጨረቃ መድመቅ ፣ ከዋክብት መፍካት አቁመዋል የሚለውን የውሸት ድምፅ እውነት ብዬ ስቀበል ያንተን ቃለ ጽድቅ ግን እጠራጠራለሁ ። የማትጠልቅ ፀሐይ ፣ የማትጠፋ መቅረዝ ፣ የሕይወቴ ሕይወት አንተ መሆንህን ቃልህ ሲነግረኝ አላዳምጥም ። አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ፤ ዘመንህ ገሰገሰ ፣ ዕድሜህ ያለ ብልሃት አለቀ ፣ ወራትህ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ፈጠነ የሆንኸውና ያደረግኸው ነገር የለም የሚለኝን የጠላት ድምፅ ሕሊናዬን የተከራየውን የባላጋራውን የቃል ፍላጻ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። መሆን ይቀድማል ፣ ተግባር ይከተላል ፤ ካልሆነ ማንነት ተግባር ቢወጣ አይፈውስም ። ከማይራራ ልብ ስጦታ ይወጣል ፣ ወይ ጉቦ ወይ ዝና ፍለጋ ይሆናል ። መሆንን ሰጥቶ ማድረግን የሚያስቀድም እግዚአብሔር ነው ። በገባዖን ሰማይ የቀኑን ሠርክ ማለዳ ያደረገ ፣ ባለቀ ቀን ላይ ቀንን የጨመረ ፣ ተፈጥሮ የሚገዛለት ፣ ጨለማ በእርሱ ዘንድ የማይጨልም ፣ ቀን ቢሉት የማይመሽ ዕድል ፣ ብርሃን ቢሉት የማይጨልም እውነት እግዚአብሔር አለልህ የሚለኝን የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ አላዳምጥምና እባክህ ይቅር በለኝ ።
አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ስለ ልደቴ ሳላመሰግን ስለ ሞቴ የሚያስፈራራኝን ፣ እንዴት እዚህ ደረስሁ ? ማለትን ትቼ እንዴት እሆናለሁ ? የሚለኝን ፣ ስለ መኖሬ አስረስቶ ስለ ስኬቴ የሚያዋራኝን ፣ ስለ ጠባቂ መልአኬ አስረስቶ ስለ ከዱ ሰዎች የሚያናግረኝን የጠላቴን ድምፅ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ።
ጠላቴን በሁለት ጆሮ ፣ አንተን በአንድ ጆሮ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በአንዱ ጆሮ ሰምቼህ በሁለተኛው አፈሰዋለሁ ። ቃልህን በምሰማበት ቦታ አልጋዬንና ትራሴን ልዘርጋ ወይ ? ስሰማህ መልአክ ፣ ስወጣ ሰይጣን ሆኛለሁ ። ጌታ ሆይ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስለ ታሪክ እጣላለሁ ፣ ስለ ነገ ሰንፌአለሁ ። ጥያቄዬ እያሳሰበኝ የሌሎችን እንቆቅልሽ አናንቃለሁ ። ለመተኛት አልጋ ገዝቻለሁ ፣ እንቅልፍ ግን ያንተ ጸጋ ነው ። ስትነሣ ብትወድቅስ ፣ ስትቆርብ ብታፈርስስ ፣ ስትቀደስ ብትረክስስ ? የሚለውን ድምፅ አዳምጣለሁ ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ የሚለውን ያንተን ቃል ግን አላዳምጥምና ይቅር በለኝ ። እዚህ የደረስኩት በዕድሌ ሳይሆን ባንተ የአሳቢነት ስጦታ ነው ። ራሴን በቤትህ ያገኘሁት በእረኝነትህ ፍለጋ ነው ። የሚበዛውን ወራት በራሴ አልኖርኩም ፣ የቀረውን ትንሽ ዕድሜ በአቅሜ ለክቼ እፈራለሁ ። ጌታ ሆይ ! የምኖረው እስከ ዛሬ ማታ ሊሆን ይችላል ። የምጨነቀው ግን ለሺህ ዓመት ቀለብ ነው ።
አላዳምጥምና ይቅር በለኝ ። አንተ የራስህ ፣ አንተ የወላጆችህ ዕቅድ አይደለህም ። አንተ የማኅበረሰቡ ሎሌ ሳይሆን አንተ ለጌታ ፈቃድ የተሠራህ ነህ ። አንተ የሚመስልህ የሌለ ልዩ ነህ ። አንተ ከስኬት በላይ የእግዚአብሔር ልጅ ተብለህ የምትጠራ ነህ ። አንተ ርካሽ ቦታ ብትገኝም የሠራህ እጅ ውድ ነው ። አንተ ሰዎች ቢጥሉህም ብርና ወርቅ ዋጋህ አይደለም ። አንተ በወልደ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተዋጀህ ነህ ።
ጌታ ሆይ ! ይህን ድምፅህን አላዳምጥምና ይቅር በለኝ ። ጨው ካልሟሟ ጣዕም አይሆንም ። ድንጋይ ነው ተብሎ ይጣላልና ዋጋውን ያጣል ። ክርስቲያንም ላንተ በመሸነፍ ይከብራል ። ለእኔነቱ በመሞት ጣዕመ ዓለም ይሆናል ። እባክህ ላዳምጥህና ጨው ልሁን ። አሜን !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም.