የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አዳምጣለሁ -2

ይቅር በለኝ አዳምጣለሁ ። የሰዎችን ፊት ዓይኔ አትኩሮ ያያል ። ጠንቋይ መዳፍን ሲያነብ ፣ እኔ ፊት እያነበብሁ ራሴን አሰቃያለሁ ። ዛሬ ፊታቸው ጠቆረ ፣ ምን አስበው ነው? እላለሁ ። የምታኖረኝን ትቼ የማያኖሩኝን እፈራለሁ ። መኖሬ በሰው ፍቅር ላይ የተመሠረተ ይመስለኛል ። ዓለሙ ሁሉ ቢያድም አንተ ካልፈቀድህ ማንስ ይነካኛል ? ጌታ ሆይ የሰዎችን የድምፃቸውን መጠን በጆሮዬ እለካለሁ ። ሰላምታቸው ቀዘቀዘ ደግሞ ምን ሊሉኝ ነው ? እላለሁ ። ስሜቴ ከፍና ዝቅ ይላል ። ቋሚ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ደስታዬን መሥርቼ ስወጣና ስወርድ እውላለሁ ። አዎ አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ። አንተ በእውነት ስትወደኝ ምንም አይመስለኝም ፣ ሰዎች በሽንገላ ሲያፈቅሩኝ ልቤ ይዘላል ። ቀድሞም ያልወደዱኝ ሲጠሉኝ ግራ ይገባኛል ። የሰው ፍቅር ከሞት አያድንም ፣ “ወዶኛልና አዳነኝ” የተባለልህን አንተን ፣ የነፍስ አብነቴን ችላ ብያለሁና ይቅር በለኝ ። የእግር ኮቴዎች ምን ይዘው መጡ ? የሚል ጥርጣሬ ፣ የስልክ ጥሪዎች ምን ሊሉኝ ነው ? የሚል ስጋት ይጥልብኛል ። ትላንት ሰላም ያሉኝ እንዲህ ብለው ነው ፣ ዛሬ ደግሞ ይህን ቃል ቀነሱ እያልሁ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በብሉይ በሐዲስ ፣ በእውነት ምስክሮች የጸናውን ፣ አንተ ለእኔ ያለህን በጎ አሳብ አቃልያለሁና ይቅር በለኝ ።

አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ። ስሜን ሲያቆላምጡ ደስ ይለኛል ፣ ውለታ መስሎኝ ካልከፈልሁ ያሰኘኛል ። ለስም አጠራሬ የምከፍል ብቸኛ ሰው የሆንሁ ይመስለኛል ። በሙሉ ስሜ ሲጠሩኝ ደግሞ ደስታዬ እንደ ካባ ወደ ኋላ ይወድቃል ። ሰዎች ሥራቸውን ስለ ሠሩ ከማመስገን በላይ ለእኔ ልዩ ውለታ ያደረጉልኝ መስሎ ያሳቅቀኛል ። ቁመናዬ በነፋስ ሽውታ ይነቃነቃል ፣ ቆዳዬ ትንሽ ሲነካ የሚቆስል ስስ ሆኗል ። እንኳን ችግር መጥቶ ፣ ሊመጣ ነው እያለ ይርዳል ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። አንተን ሳይሆን ወደዚህ ዓለም ያላመጡኝን ፣ ከዚህ ዓለም የማይወስዱኝን ፤ እንደ እኔ ፈሪ የሆኑትን አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ሰዎች ቃላቸውን ሲያጥፉ ፣ የትላንት ንግግራቸው ከዛሬው ሲዘባረቅ አዳምጣለሁ ፣ ለምን ? ብዬ በቀጭን መርፌ ነፍሴን እወጋጋታለሁ ። አዎ አዳምጣለሁ ሰዎች ለሌላው ሰው መርዛም ዱለታ ሲዶልቱ ፣ እኔን ባይነኩኝም አዳምጣለሁ ። ሲያሙ ቆይተው ፣ ያሙት ሲመጣ አቅፈው ሲስሙት እታመማለሁ ። ወላጅ ቀብረው በሠልስቱ ስለ ውርስ ሲያወሩ አዳምጣለሁ ፣ ስለዚህ እደቅቃለሁ ።

በአካሌ ላይ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ነገር አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ገና ሞት እያለ መታመምን እፈራለሁ ። በመገናኛ ብዙኃኑ ስለ በሽታ ሲወራ እኔ እንደ ታመመ ሰው እንቅስቃሴ ማድረግ እጀምራለሁ ። አዎ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ትንሣኤና ሕይወት መሆንህን አምናለሁ እያልሁ በሽታን እሰጋለሁ ። ጠቢብ አልቻለም ሲባል በጆሮዬ የምሰማው እግዚአብሔር አልቻለም ብዬ ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። እያንዳንዱን ቃል አጠራለሁ ፣ እንዲህ ያለው እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው እያልሁ አሰላስላለሁ ። እኔ እንደ ልቤ እየተናገርሁ ሰዎች ግን ችሎት ላይ ቆሞ እንደሚናገር ሰው በሰቀቀን እንዲያወሩኝ አደርጋለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። አሰቡትም አደረጉትም ፣ ተናገሩትም ዝም አሉትም ያው ነው ብዬ አረፋ መትቼ ፣ በሺህ አባዝቼ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በሁለት ጆሮ እየሰሙ ከሰው ጋር መኖር እንደማይቻል ባውቅም ፣ በትዕግሥት ማጣት የካብኩትን ብንድም አሁንም አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ምን ይሉኛልን ፈርቼ ሥራዬን ፣ ሐሜትን ተሳቅቄ ራእዬን ትቻለሁና ይቅር በለኝ !

ልጆቼ ስለ እኔ ያላቸውን የፍቅር ሙቀት አዳምጣለሁ ። “ብሞትስ ምን ትላላችሁ” ብዬ የቅኝት ፍተሻ አደርጋለሁ ፣ ገና ሳልሞት አላለቀሱም ብዬ ተስፋ እቆርጣለሁ ። ማዳመጥ አስክሮኝ ብሶትን እወልዳለሁ ። ከሰው ጋር በጨዋታ በሳቅ ውዬ ፣ ወደ ቤቴ ስመለስ የተናገርኩትን ሌሊት ሙሉ ከልሼ አዳምጣለሁ ። አስቀይሜ ቢሆንስ ብዬ እሰጋለሁ ፣ ደስታዬን ሳበላሽ አድራለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስልክ ደውዬ በመጀመሪያው ጥሪ ካልተነሣ አዳምጣለሁ ። የመጀመሪያው ጥሪ በእኔ ትርጉም ፍቅር ነው እላለሁ ፣ ሦስተኛው ጥሪ ላይ ካልተነሣ ስላልፈለጉ ነው እላለሁ ። ደስታዬን ጨቁኜ ለራሴ አለቅሳለሁ ። ባልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ ኀዘን ውስጥ እገባለሁ ። ሰዎቹን ሳገኛቸው ያን ጊዜ ስልክ ያላነሣሁት ታስሬ ፣ ታምሜ ነበር ሲሉኝ በራሴ አፍራለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስብከት ስሰማ አዳምጣለሁ ፣ ሰባኪውን ካወቅሁት የእኔን ምሥጢር እያወጣ ነው ብዬ ቃልህን ለመስማት እንኳ እፈተናለሁ ። እኔን ሊናገር ፈልጎ ነው እያልኩ አደባባይህን ፣ የንስሐ ድምፅን እጋፋለሁ ። አዳምጣለሁና እባክህ ይቅር በለኝ ።

ሰዎች የትዳር ውድቀታቸውን ሲናገሩ የእኔም ጉድ ባልሰማው ነው እንጂ ይህን ይመስላል እያልሁ ቤቴን አውካለሁ ። ኑሮዬን አፈርሳለሁ ። ለእልህ ስላደረግሁት አልቆጭም ። ጉልበቴ በማይረባ ነገር ያልቃል ። ቃልህ ተተርጉሞ እንኳ አይገባኝም ፣ የሰዎችን ነጠላ ቃል ግን ተርጕሜ እጣላለሁ ። ትላንት የሰማሁት ቃልህን ረስቼዋለሁ ፣ የሃያ ዓመት ቂም ግን በውስጤ ሕያው ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ደግ ቃል ቶሎ አይገባኝም ። ትምህርትም ጎበዝ አይደለሁም ። ክፉ ቃል ግን ያለ አስተማሪ ይገባኛል ፣ ፈነካክቼ – አብጠርጥሬ እጋተዋለሁ ። አቤቱ ያን ጊዜ መተንተን ይሆናል ፣ የማይጠቅም መተንተን ነው ፤ ያን ጊዜ ሁሉም ነገር ብልጭ ይልልኛል ፣ የማይጠቅም ብርሃን ነው ። ያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል ፣ የማይጠቅም ልቅሶ ነው ። ማዘንስ ሰዎች ስለበደሉኝ ሳይሆን ሊያስቀይሙህ የማይገባውን አንተን በማሳዘኔ ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ።

ተፈጸመ

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ