የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አገልግሎቱ ባለቤት አለው

 “ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ” 1ጢሞ. 1፡12
አገልግሎት የአገልጋዮች ሳይሆን አገልግሎት የእግዚአብሔር ነው ። አገልግሎት የእግዚአብሔር ነውና ለአገልጋዮች ብቻ የምንተወው አይደለም ።አገልግሎት የእግዚአብሔር ነውና በአገልጋዮች ማንነት የምንመዝነው አይደለም ። አገልግሎት የእግዚአብሔር ነውና ዋጋ ከፋዩ ሰማያዊ አምላክ ብቻ ነው ። አገልግሎት የእግዚአብሔር ነውና ማንም ሊያቆመው አይችልም ። አገልግሎት የእግዚአብሔር ነውና አንድ ቀን ሂሳብ ይተሳሰበናል ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እኛ አገልግሎቴ አላለም ። “አገልግሎቱ” አለ እንጂ ። እኛ አገልግሎቴ ስንል እንደ አራስ ነብር ስንቱ በቊጣ አሳደድነው ። እኛ አገልግሎቴ ስንል ስንቱን ገድለን ለመኖር አቀድን ። እኛ አገልግሎቴ ስንል ወንድማችንን እየጠላን እግዚአብሔርን እንወዳለን አለን ። እኛ አገልግሎቴ ስንል ስንቱን በቁም ለመቅበር ተነሣን ።

አገልግሎቴ የሚሉ ክልሌ እያሉ እንደሚፋጁ በግዛታቸው ለገባው ምሕረት የላቸውም ። አገልግሎቴ የሚሉ ቀረጥ የማይከፍሉበት ሱቃቸው አድርገው ስለሚመለከቱት ሌላውን አገልጋይ እንደ ደመኛ ያዩታል ። አገልግሎቴ የሚሉ ምእመኑን እንደ ደንበኛቸው ሲያዩ አገልጋዩን ደግሞ እንደ ተቃዋሚ ያዩታል ። ለዘመናት መነኩሴ ለመነኩሴ ፣ ቄስ ለቄስ ያግዛል እየተባለ ይተች ነበር ። የእኛ ደግሞ እኛን የሚመስለውን ካላጠፋሁ የሚል መሆኑ የሚገርም ነው ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አገልግሎቱ ለመናገር የፈለገው ለምንድነው ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ከላይ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ የሚወዱ የሕጉን ምንነት ያልተረዱ ፣ ሕጉ ወንጀል ባለበት ብቻ ድምፅ እንዳለው ያላስተዋሉ ሰዎችን ሲመክር ቆይቷልና አሁን ደግሞ እርሱ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የተጨመረበትን ምሥጢር ማለትም የቸርነቱን መንገድ መናገር ፈለገ ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ሕጉ የገደለ ወይም ከገዳዮች ጋር የተባበረ ነውና የሚገባው ሞት ነው ። እንደ ቸርነቱ ግን የእግዚአብሔር አገልጋይ ሁኗል ። የኤፌሶን ሰዎችም በጸጋው ተጠርተው በሕግ ለመኖር ፈለጉ ። ሕጉን መፈጸም ሳይሆን በበጎነታቸው እንደ ተጠሩ ለማሰብ ሞከሩ ። ሐዋርያው ግን እኔ ራሴን በአገልግሎቱ ያገኘሁት በቸርነቱ ነው እያለ ነው ።አንዳንዱ ጥሩ አስተዳደጉን እያነሣ ፣ ሌላውም ጨዋነቱን ከግምት ውስጥ እያስገባ እግዚአብሔር በዚህ ብቻ እንዳዳነው ያስብ ይሆናል ፤ ሐዋርያው ግን ከቸርነቱ ውጭ አለኝ የምለው ምንም ነገር የለኝም እያለ ነው ።
“ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ” ይላል ። ሹመት ሹዋሚ አለው ። አገልግሎት ከፊት ሹመት ፣ ከኋላ ሽልማት አለው ። አገልግሎት ከፊት ሹመት ፣ ከኋላ ተጠያቂነት አለው ። ሐዋርያው አገልግሎትን ዕድል ብቻ ሳይሆን አደራም አድርጎ እየተመለከተው ነው ። አንድን አሳዳጅ ሰው ፣ ትልቁን ምስክር እስጢፋኖስን ያስገደለ ቀናተኛን ረቢ አገልጋይ ለማድረግ እኛ አናምነውም ። እግዚአብሔር ግን ጳውሎስን ታማኝ አድርጎ ቆጠረው ። እኛ በመጠራጠር ፣ እግዚአብሔር ግን ታማኝ አድርጎ በመጠር ይጠራል ።እግዚአብሔር የምንደሰትበት ብቻ ሳይሆን የሚደሰትብን መሆኑን ማሰብ እንዴት ደስ ይላል ። እግዚአብሔር የምናምነው ብቻ ሳይሆን ታማኝ አድርጎ የሚቆጥረን መሆኑን ማሰብ እንዴት ልብን ያሳርፋል ። እግዚአብሔር ትእዛዛቱን የሰጠን ስለሚያምነን ነው ። እኛ የማናምናቸውን አናዛቸውም ። እግዚአብሔር ግን ስለሚያምነን ያዘናል ። ትላንት እንዳልነገረን አድርጎ ዛሬም ይናገረናል ።
ትእዛዝ ለሁሉ ሲሰጥ ሹመት ግን ለሁሉ አይሰጥም ። ሁሉም ክርስቲያን አገልጋይ ነው ቢባልም ሁሉም ግን ሹመት ያለው አገልጋይ አይደለም ። ብዙ ጊዜ እኛ የንጉሥ ካህናት ነን የሚለውን ቃል በመጥቀስ አገልጋይ ወይም ካህን አያስፈልግም ይባላል ። ይህ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተነገረው እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በምድረ በዳ ላይ ነው ።እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ ።” ይላል /ዘጸ. 19፡6/ ። በዚህ ቃል መሠረት እስራኤል ሁሉ የንጉሥ ካህናት ናቸው ። በዘጸ. 28፡1 ላይ ደግሞ፡- አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ ካህናት ይሆኑልኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ ይላል ። መላው እስራኤል የካህናት መንግሥት ናቸው ። ምክንያቱም ተዋጅተው ከግብጽ ወጥተዋልና አሮንና ልጆቹ ግን የተሾሙ ካህናት ናቸው ። በአዲስ ኪዳንም ተዋጅተው የወጡ ምእመናን በሙሉ ካህናት ሲባሉ እንደ ጳውሎስ ያሉት ደግሞ የተሾሙ ናቸው ። /1ጴጥ. 2፡9፤ ሉቃ. 10፡1/ ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ደጅ የሚከፍቱና የሚዘጉ ካህናት ወይም አገልጋዮች አያስፈልጉም ብለን ማሰብ የለብንም ። ካህን ማለት ኮሄን ከሚል የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ሲሆን አገልጋይ ማለት ነው ።
ጥሪ ፣ ሹመት ፣ ተልእኮ ፣ አገልግሎት የሚባሉ አራት ነገሮች አሉ ። የክርስቲያንነትና የአገልግሎት ጥሪ የሚባል ሁለት ዓይነት ጥሪ አለ ። ሹመት ደግሞ ከጌታችን በቀጥታ የምንቀበለው ወይም ሐዋርያዊ መስመር ያለው ተዋረድ ፣ ዐሠረ ክህነት ነው ። ተልእኮ ወንጌልን ለማዳረስ የምንወጣበት የዘመቻ ሥራ ነው ። አገልግሎት ደግሞ የተተከለውን የምናሳድግበት እረኝነትና አስተማሪነት ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጥሪውና ሹመቱ ይናገራል ። እነዚህ በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ ናቸውና ።
እግዚአብሔር ከትእዛዙና ከሹመቱ ጋር ማስፈጸሚያ እንዲሆን ኃይል ይሰጣል ። መንግሥት ሹመት ለሰጠው ሰው ኃይል አብሮ ይመድባል ። ኃይል ባይኖር ሹመት ከንቱ ይሆን ነበር ። እግዚአብሔርም ከሹመቱ ጋር ኃይል የሚሰጠው ራሳችንን እንድንገዛና አገልግሎቱን እንድናከናውን ነው ። ያለ እግዚአብሔር ኃይል ራሳችን መግዛት አይቻልም ። የእግዚአብሔር ትእዛዝም ሌጣ ሳይሆን በትኩስነት ለሚታዘዙት ኃይል የተሞላ ነው ። ስንዘገይ ግን ኃይሉ ይሄድና ትእዛዙ ይቀራል ። ማገልገልም የሚታይና የማይታይ ፈተና ያለበት ነው ። ሰዎችን ከአጋንንት እስር ቤት ማስወጣት ነው ። ያሰራቸው እንዲሁ አይመለከተንም ። ይታኮሳል ፣ ይጋደላል ። ማገልገል ሰዎችን ከሲዖል እሳት ማውጣት ነው ። ሲዖልን ከሚያህል እቶን ነፍስ ሲያመላልሱ ወላፈኑ አይንካኝ ማለት የሚገርም ነው ። ሰዎችን ለራሳቸው መዳን ደጅ መጥናት ነውና አገልግሎት የእግዚአብሔር ኃይል ያስፈልገዋል ።
“ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ” ይላል ። መሾሙ አደራ መስጠት ሲሆን ኃይል መስጠቱ ደግሞ የአብሮነቱ ምስክር ነው ። አንድ ሹም ኃይል አብሮት ካለ የሾመው አብሮት እንዳለ ይረዳል ። ሐዋርያው ጳውሎስም የእግዚአብሔር ኃይል አብሮት እንዳለ ተረድቷል ። ስለዚህም ያመሰግናል ። ያ ኃይል የሚሠራው ነገር አለ፡-
1-  የሐዋርያውን ሕይወት ከሚታይና ከማይታይ አደጋ ይጠብቃል ።

2-  የሐዋርያው የሆኑትን ሁሉ ነቅቶ ይጠብቃል ።

3-  የአጋንንትን ግዛት እየጣሰ ምርኮን ለሐዋርያው ያሰናዳል ።

4-  ሐዋርያው ለጆሮ ሲናገር ያ ኃይል ደግሞ ለልባቸው እየተናገረ ቃሉን ያትማል። 

5-  በክፉ ነገሮች ላይ ፈውስን ይሰጠዋል ። ደዌያትንና አጋንንትን ይገሥጻል ።

6-  በማዕበልና በወጀብ ውስጥ ሲያልፍ ሐዋርያውን ያጽናናዋል ።

7-  ለሰማዕትነት እንዲጨክን በማድረግ ለክብር ያበቃዋል ።
እግዚአብሔር ተራ ጥሪ አልጠራንም ። ሹመቱም ኃይል አልባ አይደለም ። ስለዚህ ማስተዋል ያለብን ነገሮች አሉ ። የማናየውንና የማንሰማውን የሚያይና የሚሰማልን አምላክ አለን ። እኛን ብቻ ሳይሆን የእኛ የሆኑትም የደኅንነት ዋስትና አላቸው ። ፊታውራሪ ሁኖ እየቀደመ ድልን የሚያዘጋጅልን የአገልግሎቱ አምላክ አብሮን አለ ። የሰዎችን ልብ እያሰናዳ ፍሬ ያበዛልናል ። በክፉ ነገሮች ላይ ሥልጣን ሰጥቶናል ። ፈተናና መከራ ቢበዛም ድሉ የታወቀ ጦርነት ነው ። በመጨረሻም በሞቱ እንመስለው ዘንድ ለሰማዕትነት ያግዘናል ።
እግዚአብሔር አገልግሎቱን እኛ ላይ ጥሎት የሄደ ከመሰለን እግዚአብሔር ሥራውን የማይስት አምላክ ነው ። በመከራና በፈተና ውስጥ አሻግረን የእርሱን ተስፋ መስማት ቢያቅተንም የጠራን ግን ታማኝ ነው ። ስለዚህ መበርታት አለብን ። የአገልግሎቱ ጥሪና ሹመት እንዳለን ግን ማረጋገጥ መልካም ነው ። እንኳን እኔ እነ እገሌም ሰብከውታል ብለን የገባንበት ከሆነ ደግመን ማሰብ አስፈላጊ ነው ። ለአገልግሎት የሚያስፈልገው ወንድነት ፣ ሥጋዊ ጀግንነት ፣ ዲግሪና ቁመት አይደለም ። ጥሪና ጸጋ ነው ። ጥሪ የሌለው ሰው ጥሪ ያላቸውን ያፈናቅላል ። ጥሪዬ ምንድነው ? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው ።
እስከ ዛሬ በቤትህ ለመቆየት ኃይል የሰጠኸን ጌታ ተመስገን !!
1ጢሞቴዎስ /14/
ኅዳር 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ