October 1, 2021 by ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
አጋጣሚው አይለፈን
“ክርስቶስን ለመምሰል ያገኛችሁትን አጋጣሚዎች ሁሉ አታሳልፉት ፣ ተጠቀሙበት ።” /እማሆይ ትሬዛ/
የሰው ልጆች ፣ ማኅበራዊ ሕይወት ፣ ምድራዊ ቆይታ ፣ ጸጋ እነዚህ ሁሉ የእገዚአብሔርን ትእዛዝ ተግባዊ የምናደርግባቸው ስለሆኑ ደስ ሊያሰኙን ይገባል ። ከዐሠርቱ ትእዛዛት ግማሹ ከሰው ልጆች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚመለከቱ ናቸው ። ሰዎች ጋር መኖራችን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ አስፈላጊያችን ነው ። ማኅበራዊ ሕይወትም የመስጠትና የመቀበል ሂደት ነው ። ሕይወት የግል ተጠያቂነት ፣ የጋራ ተጠቃሚነት ያለባት ስሪት ናት ። ሰው በተፈጥሮው ማኅበራዊ ነው ። ከሌላው የሚሻው ፣ ለሌላውም የሚቸረው ሁኖ የተፈጠረ ነው ። በዚህ ዓለም ላይም ከሚያስደስቱ ነገሮች ዋነኛው ማኅበራዊ ሕይወት ነው ። የገለልተኝነት ሕይወት ፣ የግለኝነት ኑሮ ፣ የራስ ወዳድነት ዘይቤ ለጊዜው ስልጣኔ ይመስላል ። ቆይቶ ግን ሰው ራሱን በራሱ እንዲጎዳ የሚያደርግ ክፉ ዝንባሌ ነው ። ሰይጣን የሚያገኘን ብቻችንን ስንሆን ነው ። ሔዋን ብቻዋን በመሆንዋ ለራስዋና ለዘርዋ የሞት ምክንያት ሆነች ።
ምድራዊ ቆይታም እጅግ ደስ የሚል ነው ። ዕድሜ ተከርክሞ ከዘጠኝ መቶ ዓመት ወደ ሰማንያ ዓመት ወርዷል ። በትክክል ካሰብነው ሰማንያ ዓመት ሰማንያ ቀን ማለት ነው ። የተሰጠንን ሥራ ለመፈጸም በጣም አጭር ነው ። ቀጥሎ ምን እንደምንሆን አናውቅምና ሕይወት በጣም አጭር ናት ። ሰው ትላንቱ እርግጥ ፣ አሁኑ እውነት ሲሆን ኋላው ግን አጠራጣሪ ነው ። የአሁን ሰው ፣ የኋላ ሬሳ ነን ። ምድራዊ ቆይታን አስደሳች የሚያደርገው ዘላለማዊ ውሳኔ የምናደርግበት ፣ በክርስቶስ አምነን በጎ የምንሠራበት ስለሆነ ነው ። ጸጋም አቅም ፣ መለኮታዊ እገዛ ነው ። ሰው ፈቃዱን ፣ እግዚአብሔር ኃይሉን ሲሰጥ በጎ መሥራት ይቻላል ። እግዚአብሔር እንደ ሮቦት ያለ ታዛዥ ሰውን አይፈልግም ። ሰው ወድዶና ፈቅዶ እንዲገዛለት ይሻል ።
ወደ መንፈሳዊ ዓለም ከመጣን በኋላ ለእግዚአብሔር ስለሰጠነውና ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለተውነው ነገር ብዙ እንቆጥራለን ፣ እንቆጫለን ። እኛን በመጥራቱና በማጽደቁ ክርስቶስ ሳይጸጸት የእኛ መቆጨት ይገርማል ። “ልጅነቴን ለጌታ ሰጥቼ ፣ መማርና መሥራት ስችል አገልግሎት መርጬ” እንላለን ። እኔ ብለን ስንናገር እግዚአብሔርን እንደምናጣ አናስተውልም ። ለጌታ ብለን ከተውነው ጌታ ለደሙ ብሎ የተወልን ይበዛል ። እኛ የእርሱን ጊዜ ለእርሱ ሰጠን ካልን እርሱ ደግሞ የእርሱን ዘላለም ሰጠን ። አገልግለን ገንዘብ ፣ ሮጠን ሹመት ፣ ወድደን መወደድ ባለመቻላችን ወደ ኋላ ለማለት እንዳዳለን ። የእግዚአብሔርን ስም እየጠራን ከሰው ዋጋ እንፈልጋለን ። ስለዚህ የምንጠራው እግዚአብሔርን ፣ የምናምነው ሰውን ነው ። ጴጥሮስ በአፉ ክዶ በልቡ አመነ እንላለን ። እኛ ግን እንደ አርዮስ በአፍ አምነን ፣ በልብ እየካድን ይመስላል ።
ስለሰጠነው ሳይሆን ስለተቀበልነው ፣ ስለተውነው ሳይሆን ስለተተወልን ማሰቡ መልካም ነው ። ቤተ ክርስቲያን የሰማዕታትን መታሰቢያ እንድናከብር ያደረገችው እግዚአብሔርን ያገለገለ ሰው መታሰቢያው መጥፋት ስለሌለበት ፣ ዳግመኛም የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ስለሆነ ሲሆን ከዚያ ባሻገር እኔም ብጋደል ለትውልድ አርአያ እሆናለሁ የሚል ዕጩ ሰማዕትን ለማነሣሣት ፣ ደግሞም ክርስትና ዋጋ እንደሚያስከፍል ለመንገር ነው ። እያንዳንዱ ገጠመኝ ክርስቶስን የምንመስልበት መንፈሳዊ መድረክ ነው ። ከሌለን ሊኖረን ይገባል ። እውቀት ከሌለን መማር ፣ ገንዘብ ከሌለን መሥራት ይገባናል ። ካለን ግን እንደሌለን መኖር ያስፈልገናል ። አለኝ ከምንለው ነገር ይልቅ ያለን ክርስቶስ ነውና ። ራሳችንን ዝቅ አድርገን መኖር ፣ ለድሆችና ለጦም አዳሪዎች የሚራራ ልብ መያዝ ክርስቶስን በዘመናችን የምሳይበት መድረክ ነው ። ስለጠፉት ወገኖች ከመፍረድ ማልቀስ ፣ ዳግም ገንዘብ እስክናደርጋቸው በክርስቶስ ፊት ማንባት ፣ የሰቀሉትን ይቅር ያለው ጌታ ተከታዮች መሆናችንን የሚያሳይ ነው ። ወንድማችን በመጥፋቱ እኛም ወንድም አጥተናልና ከስረናል ። የእርሱ መገኘት ከጠፋ ወርቅ መገኘት በላይ ነው ።
ብልጣብልጥነትን ክደን ፣ እንዴት ልብላ ? ሳይሆን እንዴት ላብላ ? በማለት ክርስቶስን በሰፈራችንና በአገራችን መጋበዝ ይቻላል ። ድሆች በመንገዳችን ሲገጥሙን ፣ ሰዎች በቍጣ ሲመልሱልን ፣ የጀመርነው ማለቅ ሲሳነው ፣ ቀና ተናግረን ክፉ ትርጉም ሲያዝብን ፣ ዓለም ሁሉ አድሞ ይሰቀል ሲለን ፣ አጠገባችን የነበሩ ርቀው ሲተኩሱብን ፣ ዳቦ ነው ያልነው ድንጋይ ሲሆን … ይህ ሁሉ ክርስቶስን ለመምሰል ልዩ አጋጣሚያችን ነውና አይለፈን ። እንጠቀምበት ። በሰማይ መንግሥቱን የሰጠን በምድር ግን ራሱን ሰጥቶናል ። ወደ ሰማይ ብንሄድም የምንቀበለው የሚያንሰውን ነው ። የመንገሥተ ሰማያት ጌታ በልባችን ለመኖር ይመጣል ። ቃሉን መፈጸምም የልባችንን ዙፋን ማደላደል ነው ።
ጠላቶቻችን የመጨረሻውን ጥላቻና ብቀላቸውን ሲያደርጉ ይቅርታ ማድረግ ፣ ኃጢአተኞች ተስፋ ቆርጠው ሲሰቃዩ ገነትን ማብሰር ፣ በሚጠሉን መካከል ለወዳጆቻችን ዋጋ መስጠት ፣ የሌሎችን ኃጢአት መሥራት ሳይሆን መሸከምና መሰወር ፣ በእግዚአብሔር ረክተን መኖር ፣ ሥራችንን ቶሎ መፈጸም ፣ የነፍሳችን አድራሻ እግዚአብሔር አብ መሆኑን አምነን ልበ ሙሉ መሆን ፣ ሞትን በዝማሬ መቀበል ይህ ሁሉ ክርስቶስን የምንመስልበት አጋጣሚ ነው ። ጌታ ሆይ አንተን ለመምሰል ኃይል ስጠን ።
የብርሃን ጠብታ 10
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም.