የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አጥቶ ማግኘት

እግዚአብሔር በመልካሙ ብቻ ሳይሆን ክፉ ከመሰለው ነገር ደግ በማውጣት የሚባርክ አምላክ ነው። ማጣት ፣ የደከምንለትን ነገር መክሰር የብዙዎቻችን ፍርሃት ነው። ማጣት ፣ መክሰር፣ በእጃችን የነበረው ከእጃችን ሲያመልጠን የሚሰማን ኀዘን ወደር የለውም። በማጣት ውስጥ ግን ማግኘት አለ። መቼም የማንማረውን ትምህርት እጦት ያስተምረናል። ማጣት ገንዘብንና ንብረትን ማጣት ብቻ አይደለም። ክብርን፣ ዝናን፣ ከበሬታን፣ ሥልጣንን፣ ጤናን ፣ አገርን ማጣት ሊሆን ይችላል። ሁሉም እጦቶች የዓለም መጨረሻ መጣብህ እያሉ ይነግሩናል። ሁሉም እጦቶች ያለንን ውድ ነገር እንዳናይ ያደርጉናል።

እግዚአብሔር ግን በአስቸጋሪ ቀኖች ዳር ቆሞ የሚያየን አይደለም።ማዕበሉ ንብረታችንን ቢነጥቀን እምነታችንን እንዳይነጥቀን ይጠነቀቅልናል። ማዕበሉ ያልፋል፣ ሃይማኖት ግን ዘላለማዊ ነው። ማዕበሉ ያሳጣንን ነገር በእጥፍ እናገኘዋለን፣ ሃይማኖትን መክሰር ግን የማይካስ ጉዳት ነው። ነጋዴዎች፦ “የከሰርኩት ስለ ሠራሁ አይደል? ሠርቼ  አገኘዋለሁ” ይላሉ። ሃይማኖት ግን ለሰው የተሰጠች ሀብተ ሥላሴ ናት። ጌታችን በባሕር ላይ ማዕበል ገጥሟቸው ለተጨነቁትና አድነን ልንጠፋ  ነው ብለው ለለመኑት ደቀ መዛሙርት ከማዕበሉ በፊት አለማመናቸውን ገሠፀ። የሚያስፈራው ማዕበሉ ሳይሆን አለማመናችን ነው። ማዕበሉ በእምነት ይሸነፋልና ።

በሕይወታችን ያገኘነው ውድ ነገር ሁሉ በማጣት ያተረፍነው ነው። በትንሹ ምሳሌ ስናይ ከትውልድ ቦታው ርቆ የሄደ ሰው ብዙ ጊዜ ይሳካለታል። በማጣት ያተርፋል። እንደውም ለማግኘት ማጣት የሕይወት ሕግ ነው። አንዳንዴ አስቸጋሪ ሰዎች ከአጠገባችን ዞር ባይሉ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላንደርስ እንችላለን። እነዚያ ሰዎች በከዱን ሰዓት ግን ተረብሸናል። ይህ ስሜት እንዳለን ማሳያ ነው። ጊዜ ካለፈ በኋላ ግን ወደ ራእያችን እንዳንደርስ ያደረጉን የእግር ብረቶች መሆናቸውን እናስተውላለል። ብዙ ሰው ቤት የሠራው አከራዮቹ በግፍ አስወጥተውት ነው። ወደ ሥልጣን ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች መጠቃት ደርሶብኛል ብለው የሚያስቡ ሰዎች ናቸው። ሁልጊዜ ማጣት ለትልቅ ማግኘት በር ይከፍታል። ሰዎች ሄደው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይቀራል። ዓለምን የለወጡ ሰዎች ከትምህርት ቤት የተባረሩ ሰዎች ናቸው። ትምህርት ቤቱ አይችሉም ብሎ አባረራቸው ፤ እውነቱ ግን ትምህርት ቤቱ እነርሱን ማስተናገድ አልቻለም።

በማግኘት ውስጥ ከምናገኘው ተጨማሪ በረከት በማጣት የምናገኘው ይበልጣል። በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች መጽሐፍ ለመጻፍ ጊዜ አያገኙም። ብዙ ባለ ሥልጣናት ግን እስር ቤት ሆነው ጽፈውልናል። በማጣት ውስጥ ማግኘት አለ። በሰው አገር ሆነው በትውልድ ቀያቸው ቤት የሠሩ ሲባረሩ ወደ አገራቸው ገብተው በቤታቸው መኖር ሲጀምሩ እንኳን አባረሩኝ ብለዋል። ሁሉም በሮች አይዘጉም። አንድ በር ሲዘጋ አሥር በር ይከፈታል። የአቀባበላችንና የዕይታችን ብቃት ግን ለማጣጣም ወሳኝ ነው። አንዳንድ ሰዎች ፈተና ሲበዛ የሆነ ነገር ላገኝ ነው ብለው እንደ ምልክት ይወስዱታል።  ፈተና የበረከት ዋዜማ ነውና። ምንም የሌለውን ድሃ ሌባ አይከተለውም። ሰይጣንም ከጸጋ የደኸየን ሰው አይፈልገውም።

ማጣት መራራ ነው። ስናጣ ግን ገለባ ባልንጀሮች ይበተናሉ። ከዚያ በኋላ እውነተኛ ወዳጆችን ማየት እንጀምራለን። ገንዘብን መዝራት እንጂ መበተን ዋጋ እንደሚያስከፍል እንረዳለን። ከማን ጋር እንዳለን የሚነግረን ከደስታ ይልቅ የችግር ቀን ነው። ከአደባባዩ ዘወር ስንል ራሳችንን የምናዳምጥበት ጊዜ እናገኛለን።  ወደ እግዚአብሔር ቤት የመጣንበትን  ጊዜ እናስታወስ ። ግራ የተጋባንበት ጊዜ ነበር። በሚያልፈው ችግር የሚያልፈውን ጌታ አገኘን። ዕለተ ዓርብ ጌታ ጴጥሮስንና ይሁዳን ያጣበት የቀሬናው ስምዖንን ያገኘበት ነው። የግልጽ ደቀ መዛሙርት ሲሰወሩ የስውር ደቀ መዛሙርት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ቅዱስ ሥጋውን ከመስቀል አወረዱ። ክፉ ቀን እያሳመመ ያስተምራል። ጨረቃንና ከዋክብትን ያየነው ስለመሸ ነው።

የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ከከነዓን ባያባርሩት በግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር አይሆንም ነበር። ተዘናግተን ሲገፈትሩን ጠንክረን እንቆማለን። ሲያሳድዱን የመውጫው ቀዳዳ ይታየናል። መገፋት መልካም ነው። መግፋት ግን መከራ አምጪ ነው።  እነዚያን መራራ ታሪኮች ለምን አሳለፍኩ?  ብለህ አትቆጭ ፣ በዚያ መንገድ ባታልፍ  ኖሮ ዛሬ የደረስህበት ከፍታ ላይ አትደርስም ነበር ።

እግዚአብሔር ሆይ በእጦት ውስጥ ስላገኘነው ነገር  ተመስገን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ታኅሣሥ 9 ቀን  ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ