መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » እመጣለሁ

የትምህርቱ ርዕስ | እመጣለሁ

ምን ቤት አለኝና እዚህ እቀራለሁ እመጣለሁ ። አንድ ቀን ፊትህን አያለሁ ። ፊት በነሣኝ ዓለም ለምን አዝናለሁ ፣ ከፀሐይ ሰባት እጅ የሚያበራ ፣ ሕይወት የሚሰጥ ፊትህን አያለሁ ። አንተስ ታየኛለህ ፣ እኔ እስካይህ ቸኩያለሁ ። የችንካርህን ምልክት እስክዳስስ ፣ የተሰወርሁበትን ቍስልህን እስክስም ፣ ያሳመምኩህን የጎንህን ውግ እስክሳለም ልቤ ይፈጥናል ። ይህን ይመስላል እያልሁ አምላክን መሳል ያደክማል ፣ የእምነቴ መነጽር ተሰብሮ ላይህ ስል ብዥ ይልብኛል ። ብዙ ያየው ዓይኔ አንተን አይቶ መዳን ይፈልጋል ። ፊትህን ማየት ያየሁትን ጉድ ይሽርልኛል ፣ ድምፅህን መስማት የሰማሁትን ሁሉ ያጥብልኛል ። ልቤ ከተማህ ሲሆን መንፈሴ ይረጋልኛል ። እመጣለሁ ሂድ የሚለኝ ብዙ ነው ፣ ና የምትለኝ ተቀባዬ ማኩረፊያዬ እንደሆንህ ፣ አዲስ ዓለም ተሰናድቶ እንደሚጠብቀኝ ሁሉ ይወቀው ፤ እመጣለሁ ። ቀሪ ቤት የለኝ ፣ ናልኝ እያልክ ባታቻኩለኝ እመጣለሁ ። የሆዴን እነግርሃለሁ ፣ የልብ አምላክ ነህና የልቤን አጫውትሃለሁ ። ሳገኝህ የማወራህ ብዙ አለ ፣ ሌሊት በሌለበት ዓለምህ ብዙ አወጋሃለሁ ። የውስጤን እንፋሎት ላንተ እተነፍሳለሁ ። ጥይት ያሳምማል እንጂ አይታመምም ፣ መንፈሱ የሞተበት ሰውም ፣ ሌላውን ይጎዳል እንጂ አይሰማውም ። ሁሉም በአቅሙ ከሚያጠቃበት ዓለም ወጥቼ እመጣለሁ ።

ከተወለድሁበት ቀን ጀምሮ እየሞትኩ ነው ። ጥርሴ ይወልቃል ፣ ዓይኔ ማየት እያቃተው አጋዥ ይፈልጋል ። በረዳት መሳሪያ እተነፍሳለሁ ። እገሬ እንዳልሮጠ መራመድ ያቅተዋል ። በዳዴ የጀመርኩትን ዓለም በዳዴ እጨርሳለሁ ። በሕፃንነቴ ስበላ አዝረከርክ ነበር ፣ ሳረጅም እደግመዋለሁ ፤ በልጅነቴ ልብሴ ላይ ሁሉን እጠቀማለሁ ፣ ሳረጅም የሚያጸዳኝ ሰው እፈልጋለሁ ። ምን ቢሰነብቱ መምጣት አይቀርም ፣ ጌታዬ እመጣለሁ ። መተኛቴን እንጂ መንቃቴን አላውቀውም ። መውጣቴ እንጂ መመለሴ ምሥጢር ነው ። እኔ ብቻዬን ሳቅድ አንተ ፈገግ ትላለህ ። ተሸኝቶ አዳሪ ነኝ ፣ ከሰው ጋር ክፉ ምን አናገረኝ ! ተሰባሪው እኔ ሌላውን እንዳልሰብር ፣ ተሰናብቶ ሂያጁ እኔ አገር አስለቃቂ እንዳልሆን እለምንሃለሁ ። እኔ የመሬት ነኝ ፣ መሬቱ የእኔ ነው እያልሁ እንዳልገበዝ እፈራለሁ ። እርሱ ሞቶ እኔ አልቀርምና የሌላውን ሞት እንዳልመኝ እሰጋለሁ ። እመጣለሁ ጌታዬ ።

የወላጅ ቤት ለአካለ መጠን እስኪደርሱ ውብ ነው ። ከዚያ ወዲያ አግባ ውጣ የሚለው ድምፅ ብዙ ነው ። አግብተውም የማይወጡበት ቤት ያንተ ማደሪያ ብቻ ነው ። ኑልኝ እንጂ ሂዱልኝ አትልም ። የጠፋውን ረስተህ አታድርም ። አገረ ገዥ ያባርራል ፣ ድንበር ሲሻገሩ ያመልጡታል ፣ እዚያ ሌላ አባራሪ ይመጣል ። የአባሮሽ ዓለም ከሳቁ ልቅሶው ይበዛል ። በዓለም ያለው ይኸው ነው ። ዓለም በምኞት ትልቅ ናት ፣ ሲጨብጧት ባዶ ናት ። ታሯሩጣለች ፣ ሲይዟት ባዶ ናት ። አድጌ ላልወጣ ፣ ተሞሽሬ ራሴን ላልችል በአንተ እቅፍ ለዘላለም ልኖር እመጣለሁ ። ዛሬ በድንግዝግዝ አይሃለሁ ፣ ያን ቀን በብሩህ አስተውልሃለሁ ። ዛሬ ስላንተ የማውቅ ሊቅ ነኝ ብዬ እመካለሁ ፣ ያን ቀን ባንተ መታወቄን ሳስብ እደነቃለሁ ። የሚዘል ሁሉ ማረፊያው መሬት ነው ። ለሰዓታት እንጂ ለዓመታት በአየር አይበሩም ። ማረፊያው አንተ ነህ ። በወደድኩት ስቀጣ የት ነህ ብዬ እፈልግሃለሁ ። አንተ ማንንም አትቀጣም ፣ ምኞታችን ግን ይቀጣናል ። እኮ እመጣለሁ ።

ሁልጊዜ የቤቴ መሠረት ያረገርጋል ፣ ምሰሶው ይነቃነቃል ፣ በሩ ይወዛወዛል ፣ ጣራው ያፈሳል ። የጸናው ቤቴ በሰማይ ነው ፤ እመጣለሁ ። ሌላ ሰው ከምታስቸግር በሰባራው ገል በእኔ ብትጠቀም ብዬ ነው ። ምግባሬን ጨርሼ ሃይማኖቴን እንዳላባክን ና ካልከኝ እመጣለሁ ። መምጣት ለእኔ ጥቅም ነው ። ከዘላለም ሞት ለመሰወር ሞትን ትልካለህ ። በሽፍቶች መንደር መክሊቴን እንዳልዘረፍ ና ስትለኝ እመጣለሁ ። ጠርተኸው እምቢ ብሎ የቀረ ጎበዝ ማን ነው ? ብኖርም ጫማዬን አጥልቄ ፣ ወገቤን ታጥቄ ፣ በትሬን ጨብጬ ነው ። የፋሲካውን በግ አንተን ቀምሶ የት ይቀራል ? የመንገድ ስንቁ አንተ ነህ እመጣለሁ ። ማዶ ማዶ እያየህ ትጠብቀኛለህ ። አብረኸኝ እየተጓዝህ ቀድመህ ትጠብቀኛለህ ። አሳብህ ነኝ አውቃለሁ ግን እመጣለሁ ። ያንተን ልብ አሳርፋለሁ ። ወደ አባቴ ደስታ ግባ የሚለውን ቃልህን እናፍቃለሁ ።

ትንሽ ብሠራ ፣ ጥቂት ባገለግል ብዬ ነው ። ዓለም ቀዳዳ ስልቻ ናት ። ከላይ ሲሞሉ ከሥር ታፈሳለች ። ዓለም የተሻላት መስሎኝ ሰማይን ስረሳ ይብስባታል ። ትልልቆች ትንንሽ ሥራ እየሠሩ ያውኳታል ። ሕልም እልም የሆነው ወጣት ያሳዝነኛል ። ሽማግሌ በሌለበት በጎረምሳ ዘመን መኖር ያሰጋኛል ። ፍሬኑ ተበጥሶ ነዳጅ እየሰጠ የሚጓዘው ትውልድ ያሳስበኛል ። እንደ ማቱሳላ ኑሩ ቢባል እሺ የሚልህም የለም ። እመጣለሁ የሚልህ ብዙ ነው ። ባዶ እጅ ከመምጣት ጠብቀኝ ። በዕድር ደብተር ለመጻፍ ብዬ ከሕይወት መጽሐፍ ራሴን ከመደምሰስ ሰውረኝ ። እመጣለሁ ፣ ንጉሡ ሳይጠራ መሄድ ቅጣት እንዳለሁ አውቃለሁ ፣ ስትጠራኝ እመጣለሁ ። ሕለተ ወርቅህን/በትረ መንግሥትህን ስትዘረጋልኝ ፣ ና ስትለኝ ያለ ሰበብ እመጣለሁ ። ከቤቴ ከአገሬ ርቄ እንደምኖር አውቃለሁ ። ቤቴም አገሬም በሰማይ ነው ፣ እመጣለሁ ። ወደ እውነቱ ስፍራ አንድ ቀን እመጣለሁ ፣ እስከዚያው እንዳገለግልህ ኃይልን እመኛለሁ ። እመጣለሁ !

 

ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ