የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እመ ብርሃን – የብርሃን እናት

ድንግል ሆይ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የምሥራቹን ወዳንቺ ይዞ በመጣ ጊዜ የዳዊትን ስም ለምን አነሣ ? “እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል ፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” ብሎ የምሥራች ለምን ነገረሽ ? ንጉሥ ዳዊት ልጆቹ ስጋቱ ነበሩ ። አገር ገዝቶ ቤቱ ያመለጠው ሰው ነበር ። ከቤርሳቤህ የተወለደው ልጅ እየጸለየ ሞተበት ፣ የሚወደው ልጁ አምኖን የገዛ እኅቱን ትዕማርን ደፈረ ። አምኖንም ትዕማርም ሁለቱም ልጆቹ ናቸው ። አቤሴሎም አባቴ አምኖንን በቸልታ አልፎታል ብሎ ተቀየመው ፣ የእኅቱን ውርደት ለመሸፈን ወንድሙ አምኖንን ገደለው ። አቤሴሎም ተሰድዶ በእርቅ ተመለሰ ፣ ነገር ግን እርቁን አርክሶ አባቱን ከዙፋን ገለበጠ ። ዳዊትም ሸሽቶ አመለጠ ። አባቱን ሊዋጋ ወጥቶ አቤሴሎም ሞተ ። ዳዊትም ኀዘን ባጠላበት ሽምግልናው ለሰሎሞን ዙፋኑን ሲለቅ ፣ ታላቅ ልጁ አዶንያስ ራሱን ቀብቶ ንግሥናን አወጀ ፣ ሰሎሞንም ወንድሙን በሞት ቀጣ ። ሰሎሞንም በመልካም ጀምሮ በክፉ አጠናቀቀ ። ጉልበቱ ለጣዖት ሰገደ ፣ በሴት ፍቅር የእግዚአብሔርን ፍቅር ጣለ ። ዳዊት ወልዶ የተጨነቀ ሰው ነበር ። ወልዶ መካን ለሆነው ዳዊት ፣ ልጅ ሊሆን ክርስቶስ ወልደ ዳዊት/ዳዊት ልጅ ሆኖ መጣ ። የዳዊት ዙፋን በባቢሎን ምርኮ ፈርሶ እንደገና ሊጸና አልቻለም ። ከ600 ዓመት በኋላ ክርስቶስ ካንቺ ሰው በሆነ ጊዜ ወልደ ዳዊት ተብሏልና የዳዊት ስምና ዙፋን ተመለሰ ። ዘላለማዊው ንጉሥ ከዳዊት ቤት በመወለዱ የዳዊት ስም በዘላለም መንግሥት የሚጠራ ሆነ ።

ዳዊት መንግሥቱ ለዘላለም እንደሚጸና በተነገረው ጊዜ ስለ ሰሎሞንን ያስብ ነበር ። ነገር ግን የሰሎሞን የስሙ ትርጓሜ “ሰላማዊ” እንደሆነ ሁሉ የሰላም አለቃ ክርስቶስ ከእርሱ እንደሚወለድ የሚገልጥ ትንቢት ነበር ። (2ሳሙ. 7፡13-14፤ ዕብ. 1፡5)። የይሁዳን ተራራ በወጣሽ ጊዜ ይህን ለዳዊት ያደረገለትን ቸርነት ታስቢ ነበር ። ጊዜ አይቶ የማይከዳ እግዚአብሔር ዛሬ ይመሰገናል ። የብርሃን እናት ሆይ ! ሴት ያለ ወንድ ትወልድ ፣ ምድር ያለ ዘር ታበቅል ዘንድ አይቻልም ። ነገር ግን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም በተባለ ጊዜ ከልብሽ አመንሽ ። በዚህም አባትሽ አብርሃምን ፣ እናትሽ ሣራን አስታውሰሻል ። በእውነት ኤልሳቤጥ ብትፀንስ ዘካርያስ አላት ፣ ያለ ወንድ መፅነስ ግን በእግዚአብሔር ከሀሊነት የሚፈጸም ነው ። እንዲህ ያመነ ከቶ አልሰማንም ። እግዚአብሔር ቢሻ በምክንያት ፣ ቢሻ ያለ ምክንያት ይሠራል ። መንደርደሪያ የሚፈልግ ፍጡር ብቻ ነው ። እርሱ ግን የሌለውን እንዳለ አድርጎ መጥራት የሚችል ነው ።

ኤልሳቤጥን ባገኘሻት ጊዜ ደስታዋ ልዩ ነበር ። የፀነስሽውን ጌታዬ ብላ ጠራች ። አንቺንም የጌታዬ እናት አለችሽ ። እርሱን የሚያከብሩ ያከብሩሻል ። ኢየሱስን የሚያፈቅሩ ይወዱሻል ። ከኤልሳቤጥ የሚወለደው ዮሐንስ የአባቱን የሊቀ ካህንነት ወንበር የሚወርስ አልነበረም ። በሕግ የሚችለውን በጸጋ ተወ ። ዘካርያስ ስም የሚያስጠራ ፣ ወንበር የሚወርስ ልጅ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያፈቅር ልጅ ወለደ ። ዮሐንስ በከተማ መቀመጥ ሲችል በበረሃ ኖረ ፣ ሐር መልበስ ሲቻለው የግመል ጠጉር ለበሰ ፣ የላመ የጣመ መብላት ሲችል ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር ነበረ ። በልጆች ላይ እኛ ካለን ዓላማ እግዚአብሔር ያለው ዓላማ ይበልጣል ። ልጁ ሲመንን የሚያለቅስ ክርስቲያን ነኝ ባይ ብዙ ነው ። ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ግን ልጅ እንቅፋት ሳይሆናቸው በአንድ ልብ አገለገሉ ፣ ልጁ ሲወለድ ገና በሕፃንነቱ ሞቱ ። እግዚአብሔር ልጅን ያሳድጋልና ዮሐንስ በበረሃ አደገ ። በከተማም በበረሃም ያለው አንዱ እግዚአብሔር ነው ።

መንፈስ ቅዱስ ባለበት መከባበር አለ ። አንቺም ኤልሳቤጥን ተሳለምሻት ፣ እርስዋም ያንቺን መመረጥ ተናገረች ። መናናቅና መገፋፋት ያለው ሰይጣን በሚያዝዝበት ግዛት ነው ። አንቺም በመንፈስ ቅዱስ ታላቅ ትንቢት ተናገርሽ ። ሦስት ወርም ከኤልሳቤጥ ጋር ተቀምጠሸ ወርዋ ሲገባ ተመለስሽ ። በድካምዋ ልታግዥአት ይህን አደረግሽ ። አምላክን ፀንሻለሁና ሌላው ያገልግለኝ አላልሽም ። ክርስቶስን የሚወዱ ትሑታን ናቸው ። የእውነተኛው አምላክ መልኩ ትሕትና ነው ። ሰው እግዚአብሔርን የሚመስለው በትሕትና ነው ። ትሕትናም ለሚበልጡን ሳይሆን ለሚያንሱን መታዘዝ ነው ።
እመ ብርሃን ሆይ! ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ ። ሴቶች ቢባረኩ ንጉሥ ፣ ጳጳስ ቢወልዱ ነው ። አንቺ ግን አምላክን ወልደሻልና ከሴቶች ተለይተሸ የታደልሽ ነሽ ። በምድር ላይ የራስሽ ቤት እንኳ ያልነበረሽ ፣ ጸጋውን ሳይሆን ባለጸጋውን ሀብት ያደረግሽ የእምነት አርበኛ ነሽ ። እመ ብርሃን ሆይ ! ፀሐይም ትጠልቃለች ፣ ጨረቃም ትሰወራለች ፣ ከዋክብትም ከዕይታ ይጠፋሉ ፣ መቅረዝም ዘይቱ ሲያልቅ ይጨልማል ። የልጅሽ ብርሃንነት ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል ። በድንግዝግዝ እውቀት የምንዘላብድ ፣ ሁሉን ልስማ ብለን በመደናበር የምንጋጭ ፣ በተስፋ ቢስነት ጨለማ ነገ አልታይ ያለን ፣ በጽልመት ጥላቻ የደነቆርን ፣ በውድቅት ሌሊት በሚመሰለው መለያየት የተወረርን ልጆችሽ የልጅሽ ብርሃን ያግኘን ። ሰጥቶ የማይነሣው ልጅሽ በመልካም ያስበን ። በረከትሽ ይደርብን !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ