የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እረኝነት

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ኅዳር 13/2006 ዓ.ም.
 
እረኛ ማለት መጋቢ፣ ጠባቂ፣ ተንከባካቢ ማለት ነው፡፡ እረኛ ሕይወት ባለው መንጋ ላይ የሚሾም ነው፡፡ ሕይወት በሌለው ነገር ላይ ዘበኛ ሲቀጠር፣ ሕይወት ባለው ነገር ላይ ደግሞ እረኛ ይሾማል፡፡ የአንዱ ቅጥር ሲሆን የሁለተኛው ሹመት ነው፡፡ ሕይወት ያለው ነገር ተጠሪ ወይም እረኛ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ዓለም ሲዋቀር መሪና ተጠሪ ያለበት ዓለም ነው፡፡ ስለዚህ ሦስት ታላላቅ ተቋማት እረኛ ወይም መሪ አላቸው፡፡ ለቤተሰብ አባወራ፣ ለአገር ንጉሥ፣ ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ እረኛ ናቸው፡፡ በዚህ አገላለጽ እረኛ መሪ ወደ መልካም ግብ የሚወስድ ፊታውራሪ ማለት ነው፡፡
በእስራኤል አገር እረኛ ከፊት ለፊት ድምፁን እያሰማ ሲሄድ በጐቹ ይከተሉታል፡፡ እረኛ ከፊት ነው፡፡ በአገራችን ደግሞ መንጋው ከፊት እረኛው ከኋላ ነው፡፡ እረኛው ሲቀድም መሪ ይሆናል፡፡ ከኋላ ከሆነ ነጂ ይሆናል፡፡ እረኛው ሲቀድም በዜማ መንጋውን ያስከትላል፡፡ ከኋላ ሲቀር ደግሞ በጅራፍና በዛቻ ይነዳል፡፡ የአገራችን እረኝነት መንጋው ከፊት እረኛው ከኋላ ነው፡፡ ይህ በብዙ የሕይወት መስክ ያለ ነባራዊ ችግራችን ይመስላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ አይመሩም፣ ሣንቲም የሚጥለው ሕዝብ ይመራል፡፡ አንድ ነገር እናድርግ ከተባለ “ሕዝቡ ምን ይላል?” ይባላል፡፡ ሕዝቡ መሪዎቹን መከተል አለበት፡፡ አሊያ ራስና እግር ቦታ ከተለዋወጡ መጓዝ ሊኖር አይችልም፡፡
እረኛ የእርሱ ያልሆነውን መንጋ በአደራ ተቀብሎ ከራስ በላይ ይንከባከባቸዋል፡፡ እረኛ የሚያሲዘው ነገር ስለሌለ የገዛ ነፍሱን አስይዞ እረኛ ይሆናል፡፡ እረኛ ራሱን ካልሰጠ እረኛ አይሆንም፡፡ እረኛ፡-
 
1-      ነፍሱን አስቀምጦ መጀመር አለበት፡- ሀብቱን፣ ሥልጣኑን ሳይሆን ራሱን አስቀምጦ መጀመር አለበት፡፡ ራሱን የሰጠ ሰው የሚያስቀረው ነገር የለም፡፡ ራሱን የሰጠ በሌላ አይታማም፡፡
2-    ዘመኑን መስጠት አለበት፡- እረኛ ቀን ከመንጋው ጋር ይውላል፡፡ መንጋው ቀኑን በሙሉ ይበላል እርሱ ግን ጦሙን ሊውል ይችላል፡፡ ማታም በበረቱ ውስጥ ቆጥ ላይ ያርፋል፡፡ እረኛ ማለት ለቅጽበት ከመንጋው የማይለይ ነው፡፡ ስለዚህ እረኛ ዘመኑን ለመንጋው የሰጠ ነው፡፡ እንዲሁም አገልጋይ የዘመኑን ሽራፊ፣ የጊዜውን ጭላጭ ሳይሆን የዕድሜውን አስኳል ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ አገልጋይ የኮንትራት ሠራተኛ፣ የሚሻውን ሲያገኝ የሚታጠፍ አይደለም፡፡ አገልግሎት ቀን መግፊያ፣ የሚፈልጉትን ጉዳይ መጠበቂያ አይደለም፡፡ አገልግሎት የተፈጠርንበት ዓላማ የምንጓዝበት ግብ ነው፡፡ አገልጋይ የዘመኑን ዐሥራት ሳይሆን መላ ዘመኑን መስጠት፣ ከመንጋው ጋርም ያለ ማቋረጥ መገናኘት አለበት፡፡
3-    ከአራዊት ይናጠቃል፡- እረኛ የራሱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ መንጋውን ከአውሬ ያስጥላል፡፡ እንዲሁም ከአጋንንት፣ ከዓለም ምእመናንን መታደግ የአገልጋይ ድርሻ ነው፡፡ ከአውሬ ስናስጥል መቊሰል አይቀርም፡፡ ከእሳት ስናወጣ መለብለብ አይቀርም፡፡ በጐቹ የተከፈለላቸውን ዋጋ አያውቁትም፣ ላያመሰግኑን ይችላሉ፡፡ አገልጋይ ግን ለእግዚአብሔር ሲል ይህን ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡ አዎ እረኛ ለመሆን ራስን መስጠት ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም መያዣው ነፍስ ነው፣ ዳግመኛም ዘመንን መስጠት ይጠይቃል፣ አሁንም ከአራዊት ጋር መታገል ያስፈልጋል፡፡
         
      በዚህ ዓለም ላይ ራሳችንን የምንሰጥባቸው፣ የራሳችንን ኑሮ የሚያሰርዙን ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ የቤተሰብ ጥልቅ ችግር፣ ትዳራችንና ልጆቻችን የራሳችንን ኑሮ ያሰርዙናል፡፡ ራስን መሠዋት የማይቀር ከሆነ ለአገልግሎት ራስን መስጠት ድንቅ ተብሎ የሚወደስ ሳይሆን ግዴታ ነው፡፡ ተገቢም ነው፡፡ ራስን መስጠት ካልቻልንም አገልጋይ መሆን ከባድ ነው፡፡ የአገልግሎት ቊልፉ ራስን መስጠት ነውና፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እረኛ በሆነ ጊዜ የፈረመው በደሙ ነው፡፡ የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊ፡- “በዘላለም ኪዳን ደም ለበጎች ትልቅ እረኛ የሆነውን ….” ይላል (13÷20)፡፡
ጌታችን የሕይወታችን ብቻ ሳይሆን የአገልግሎታችንም አርአያችን (ሞዴላችን) ነው፡፡ ጌታችን የልደቱን ምሥጢር ለካህናት ሳይሆን ለእረኞች መግለጡ የእረኞች አለቃነቱን ይሣያል፡፡ በዘመናትም ታላላቅ ምሥጢራት የተገለጡት ለእረኞች ነው፡፡ ያዕቆብ፣ ዳዊት እረኞች ነበሩ፡፡ “ተወልዶልናል” በሚለው መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ይነበባል፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቅደስ ሳለ በበረት መወለዱ፣ ካህናት እያሉ ለእረኞች መገለጡ ይደንቃል! እርሱ ለትምክሕት የሚሆን ቍራጭ ነገር የሌላቸውን የተናቁትን ይወዳል፡፡ ከዚህ በኋላ እነዚህን እረኞች ማን ድ ብሎ ያማቸዋልከዚህ በላይ ሀብት የት ይገኛልየጎንደሩ አለቃ ክፍለ ዮሐንስ በጎንደር ረሀብ ሆኖ የከብት ሀገር ወደሆነው ወደ ደምቢያ ተሰደው ከአንድ ባሏ ከሞተባት ሴት ቤት ከብት ጠባቂ ሆነው ይቀጠራሉ፡፡ ለካ ሴቲቱ የካህን ሚስት ሆና ባሏ ሞቶባት ትክለኞቹ በቶፋ ካላስቀደስሽ ርስቱን ልቀቂ እያሏት በጣም ተጨንቃ ነበር፡፡ አለቃ ክፍለ ዮሐንስም ነገሩን እንደ ሰሙ እኔ እሞላዋለሁ ብለው ተተኩላት፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሄደው በመጀመሪያው ቀን እንዲህ ብለው ተቀኙ፡
እም ከዊነ መምህር ይኄይስ ከዊነ ኖላዊ
ወጎለ እንስሳ ትትበደር እም ቤተ መቅደስ ዓባይ
እስመ ቤተ መቅደስ ኮነት ቤተ ፈያታይ
በላዕለ ኖሎት ኢሀለወ ላዕለ ካህናት ዘሀሎ እከይ
ትእምርተ ዝኒ ከመ ንርአይ
በጎለ እንስሳ ሠረቀ ዘኢየዐርብ ፀሐይ፡፡
ትርጓሜው፡
መምህር ከመሆን ይልቅ እረኛ መሆን ይሻላል፡፡
በካህናት ያለው ክፋት በእረኞች ላይ የለምና፡፡
ከታላቋ ቤተ መቅደስም የከብቶች በረት ትበልጣለች፡፡
ቤተ መቅደስ የሽፍቶች ቦታ ሆናለች፡፡
ለዚህም ማስረጃው በከብቶች በረት
የማይጠልቀው ፀሐይ ወጥቷልና፡፡
አለቃ ክፍለ ዮሐንስ መምህርነትንም እረኝነትንም ያውቁታል፡፡ የራሳቸውን ታሪክ ከልደት ጋር አስማምተው ገለጡት፡፡ ካህናቱ የባል ሞት ብዙ ላጎደለባት ለዚያች ሴት መራራት አለመቻላቸውን ጠቅሰው ኢየሱስ ክርስቶስም በልደቱ ከካህናት እረኞችን እድምተኛ እንዳደረገ፣ ለመወለድም ከቤተ መቅደስ በረትን እንደ መረጠ አወሱ፡፡ የሁሉም ነገር ማስረጃውና መመዘኛው ክርስቶስ መሆኑንም ገለጡ፡፡ ቅዱሳን ሁሉ በጎ ዕድልን ትዳርን፣ ሥልጣንን ሳይቀር ከክርስቶስ አንጻር ይመዝኑ ነበር፡፡ እርሱን የሚነካባቸው ከሆነ ራሳቸውንም ለመተው ዝግጁ ነበሩ፡፡ የሊቃውንት ትንታኔ፣ የዳኞች የፍርድ አንቀጽ፣ የክርክር ሁሉ መቋጫ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ በምኩራብ በቃሉ አስተምሯል፡፡ በበረት ግን በዝምታ አስተምሯል፡፡ መቅረዝም ይጠፋል፣ ፀሐይም ትጠልቃለች፡፡ በቤተ ልሔም የተወለደው ኢየሱስ ግን የማይጠልቀው የሃይማኖት ፀሐይ ነው፡፡ አዎ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእረኞች ተገለጠ፡፡” /”ተወልዶልናል” 2005 ዓ.ም የታተመ/
 
እረኝነትን ካነሣን በመንጋው ዙሪያ፡-
 
1.              የመንጋው ባለቤት
2.            የመንጋው እረኛ
3.            የመንጋው ነጋዴ አሉ፡፡
 
1-   የመንጋው ባለቤት፡-  እረኛ ባለ አደራ እንጂ ባለቤት አይደለም፡፡ የመንጋው ባለቤት እግዚአብሔር ነው፡፡
2-   የመንጋው እረኛ፡-  የእረኝነት ልብና ጥሪ ያለው እርሱ እረኛ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ሰው ይህ ጸጋ እንዳለው እንኳ አያውቅም ምእመናን ሊያወሩት የሚፈልጉት፣ ሁሉን ለመስማት የልብ ስፋት ያለው ሰው፣ ማስተማር የሚችል እርሱ የእረኝነት ጸጋ አለው፡፡ እረኛ ባለቤቱን እያሰበ አደራውን ይወጣል፡፡ ሕዝቡ የእግዚአብሔር ነው፣ በደም ዋጋ የተገዛ የክርስቶስ ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ዋጋውን እያሰበ ጠንቃቃ ይሆናል፡፡
3-   የመንጋው ነጋዴ፡- መንጋውን የሚፈልገው ለሥጋዊ ጥቅሙ ብቻ ነው፡፡ ሥጋው ይህን ያህል ቆዳው ይህን ያህል ያወጣል እያለ ሲተምነው ይውላል፡፡ የበግ እረኞች ሳይሆኑ የበግ ነጋዴዎችም ከምእምኑ ምን እንደሚያገኙ ሲያሰሉ ይውላሉ፡፡
የእረኛ ባሕርያት (መገለጫዎች)
1.             መጋቢ ነው፡- እረኛ ለምለሙን ሣር፣ ንጹሑን ውሃ እየፈለገ መንጋውን ይመግባል፡፡ አገልጋይም የጠራውን ቃለ እግዚአብሔር፣ ጤናማውን ትምህርት በመስጠት የምእመናንን ነፍስ ይመግባል፡፡
2.            ጠባቂ ነው፡- እረኛ በጐቹን ከራሳቸው ሞኝነትና ከጨካኝ አውሬ ይጠብቃል፡፡ መጠበቅ አድካሚ መሆኑን የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ምእመናን ያለባቸው ፈተና ሰይጣናዊ ብቻ አይደለም፣ የገዛ ሞኝነታቸውም ፈተናቸው ነው፡፡
3.            አካሚ ነው፡- እረኛ ገደል ገብታ የወደቀችውን ያወጣታል፣ ስብራቷን ይጠግናል፣ መራመድ ቢያቅታት ይሸከማታል፡፡ አገልጋይም በስህተትም ሆነ በድፍረት ለወደቁት ምእመናን ይራራል፡፡ ካሉበት ድረስ ሄዶም ሐፍረታቸውን ገፎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመልሳቸዋል፡፡
4.            አመጣጣኝ ነው፡- እረኛ ብርቱ ደካማውን እንዳይገፋው፣ ግልገሎች ከትልልቆች ጋር ሲጓዙ ኋላ እንዳይቀሩ ያመጣጥናል፡፡ አገልጋይም ሁሉንም በእኩልነት መመገብ፣ ደካማና ብርቱውን ማጨባበጥ አለበት፡፡ ብርቱውን ብቻ የሚከተል አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡
5.            መሸከም፡- እረኛ የተሰበረውንና ፍጥነት የሌላትን ግልግል ይሸከማል፡፡ አገልጋይም ብዙ ማባበል የሚፈልጉትን ምእመናንን መታገሥ፣ ዕድገታቸው ዘገምተኛ የሆኑትን በተስፋ መጠበቅ ይጠበቅበታል፡፡ ሙሴ የሕዝቡን ድካም፣ ሸክም፣ ክርክር ተሸክሞ ነበር (ዘዳ. 1÷12)፡፡
6.           ማሰማራት፡- እረኛ መንጋውን ያሰማራል፡፡ በቅርብ ርቀት ሆኖ ይከታተላቸዋል፡፡ አገልጋይም ምእመናንን ማሰማራት፣ ሥራ መስጠት፣ እንዲያገለግሉ ማበረታታት አለበት፡፡
7.            ስለ አንድ ይቆረቆራል፡- እረኛ ዘጠና ዘጠኝ በጐች ቢኖሩትና አንዲቱ ብትጠፋበት የሚበዛውን አትርፌአለሁ ብሎ አይተዋትም፡፡ ይፈልጋታል፡፡ አገልጋይም ስለ አንድ ነፍስ ግድ ሊለው ይገባል፡፡ የአንድ ነፍስ ዋጋን ያላወቀ አገልጋይ ሊሆን አይችልም፡፡ የብዙዎችም ዋጋ የክርስቶስ ደም ነው፣ የአንዲቱም ዋጋ ያው የክርስቶስ ደም ነው፡፡
መጸለይ
ቃሉ፡- “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ እረኛ እንደ ሌላቸው በጐች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው፡፡ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- መከሩስ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን  ጥቂቶች ናቸው፤ እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው” ይላል (ማቴ. 9÷36-38)፡፡ የጌታችን ታላቅ ሀዘንና ታላቅ መመሪያ ነው፡፡ ሀዘኑ እረኛ አልባ መሆናቸው ነው፣ መመሪያው እረኛ እንዲሰጥ እግዚአብሔርን መለመን ነው፡፡ እረኛ የሌለው መንጋ የሚባዝን፣ የማይሰባሰብ፣ ድንጉጥ ነው፡፡ የሚታዩ እረኞች ያስፈልጉናል፡፡ እረኛ የሚገኘው ደግሞ ምእመናንን ሲጸልዩ ነው፡፡ ካልጸለዩ መልካም እረኞች አይነሡም፡፡ የበግ ነጋዴዎች ይወሩናል፡፡ ዛሬ ስለ እረኛ እየጸለይን ይሆን? እረኞችስ ድርሻችንን እየተወጣን ይሆን?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ