የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እረግጣለሁ ገና

                                  ቤተ ጳውሎስ፤ ቅዳሜ ሚያዚያ 27 2004 ዓ.ም.
የአሸዋ ላይ ሕንፃ ለነፋስ እስክስታ
የነፋስ ላይ ጐጆ ለእሳት ተስጥታ
የውኃ ላይ ኩበት ዝም ብሎ ጉዞ
ዕረፍት አልባ ትጋት ፈዞና ደንግዞ
ቦግ ብሎ ድርግም ብልጭ ብሎ ጠፊ
ገደቡን የጣሰ እጅግ በጣም ሰፊ
ቢሆንም ይህ ዓለም
ድግዝግዝ ጭልምልም
አያረገርግም ቤቴ ድምድማቱ
አለት አንተ ሆነህ ሥነ- መሠረቱ፡፡ 

የላመ የጣመ ፍርጥምጥም ሰውነት
ሕዋን ያስጨበጠ የመጠቀ ዕውቀት
እንደሰም አቅልጦ
እንደገል ቀጥቅጦ
ሁሉን ቢያስገዛልኝ የሥልጣኔ ጭብጥ
ሊያኖረኝ አይችልም አኑሮኝም አያውቅ
መሠረተ ሕይወት አንተ ነህ የኔ አባት::
የእምነት ምሰሶ የገርነት ወለል
የትህትና ጣሪያ የየዋሃት ጉበን
እራስን የመግዛት ሌላንም የቻለ ውብ ብርቱ ማዕዘን
የነብሴ አዕማዳት ቤቴ የቆመበት
እኒህና ሌሎች ደገኛ ምግባራት
በፍፁም አይደሉም እኔን ያስጠለሉ
መሠረቴ አንተ ነህ አንተ ካለህ ብቻ እኒህ ሁሉ አሉ፡፡
እርፌን አልጨብጥም የኋሊት ለማረስ
አንተን ትቼ ሌላ ልመሠርት አዲስ
በደም ዋጋ ቤቴን ያነጽክ ኢየሱስ ሆይ
ፍፁም አልታወክ የለም አልናወጥ የስምህ አገልጋይ
ገና በእግሮቼ እረግጣለሁ ደግሞ ከደመናት በላይ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ