የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (12)


ተመካከሩ
እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው” (1ተሰ. 511)
መመካከር ድምፅን ቀንሶ በርን ዘግቶ እውነትን አጀንዳ አድርጎ የሕይወት ለውጥ ግብ ሆኖ የሚደረግ የወንድማማች ወግ ነው። መምከር የመምህራን ድርሻ ነው። መመካከር ግን የወንድማማቾች መገለጫ ነው። እንመክራለን፣ እንመከራለን። መመካከር የእኩያነት ፍቅር ስላለው አያፈራራም። ግቡም የሕይወት ለውጥ ስለሆነ አያጸጽትም። በሕይወት ውስጥ ሁሉንም ጸጋና እውቀት ለብቻው ጠቅልሎ የያዘ ማንም የለም። በመመካከር ውስጥ ያላየነውን ወንድማችን ያሳየናል። ያቃተንን ያግዘናል። ከምክክሩ ጠረጴዛ ሲነሡም ምሥጢሩ ተቀብሮ፣ለውጡ ተናፍቆ ይለያያሉ። ምክክርን ካደረጉ በኋላ አማካሪ ሲገባ ሊበላሽ ይችላል። ምክንያቱንም ምክክር ፍቅር ሲሆን አማካሪነት ግን ሙያ ነው። ምክክር የሁለት ወገን ድምፅ ሲሆን አማካሪነት የአንድ ወገን ድምፅ ነው።
በሕይወት ውስጥ የሚያማክሩን አዋቂዎች ያስፈልጋሉ። የሚመካከሩን ወዳጆችም ያስፈልጋሉ። አዋቂዎች ባሻገር ያለውን ያለርኅራኄ ያሳውቁናል። ወዳጆች ግን ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ እውቀት ውስጥ ስለምንሆን የተለየ እይታ ላያመጡ ይችላሉ። አማካሪዎች መክረው ሲለቁን ወዳጆች ግን አብረውን ለተፈጻሚነቱ ይተጋሉ።
መመካከርን የሚጎዱ ነገሮች ምንድናቸው? ስንል ላለመደራረስ ያስቀመጥናቸው ዘመናዊ አጥሮች የመጀመሪያዎቹ ናቸው። ያንተ እውነት ላንተ፣ የእኔ ለእኔ ልክ ነው አትድረስብኝ የሚለው የድኅረ ዘመናዊነት አስተሳሰብ ለመመካከር እንቅፋት ነው። ለመመካከር ሌላው እንቅፋት መተማመን መጥፋቱ ነው። ሰው ሁሉ የቆቅ ኑሮ እየኖረ፣ ልብና አፍ እየተለያዩ ነውና ይህ ለመካከር እንቅፋት ነው። አንዱ ላንዱ ጉዳይ የሚሰማው የእኔነት ስሜት መዳከምና ምን ቸገረኝ? የሚል አስተሳሰብ ለመመካከር እንቅፋት ነው። ሰዎች ስሜታቸው እየሳሳ በመምጣቱ የሚነገሩትን ቃላት በክፉ ስለሚያዩ መመካከር አስቸጋሪ ይሆናል። በፍቅር ካልሆነ በቋንቋ መግባባት ከባድ ነው። ራስን ብቻ ማዳመጥና ሌሎችን መናቅ እንዲሁም በሌሎች ተስፋ መቁረጥ ለመመካከር እንቅፋት ነው። ምሥጢር የተባለው ነገር በደጅ ሲገኝ ይህም ለመመካከር እንቅፋት ነው።
እርስ በርስ መመካከር ለሕይወት ሕንፀት ወሳኝ ነው። ትልቅ ጸጋም ነው። የፍቅር ሥልጣንም የሚያስገኝልን በረከት ነው። “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ነው” እንደሚባለው መመካከር የሕይወትን ሸክም ያቀላል። መመካከር ግን የራሱ ሥነ ሥርዓት አለው። እውነተኛ ፍቅር፣ ለመፍትሔ የጋራ ጥረት፣ ብርቱ ትዕግሥትና ውስጥን ማሳየት መቻል፣ ምሥጢረኛነትና ለወዳጅ ወኪል ሆኖ መናገር መቻል፣ ያገባኛል በሚል ስሜት የሌላውን ሸክም መጋራት፣ መልካምነታችንን ግዴታችን አድርጎ መመልከት፣ ሐሜትን ማራቅ፣ ችግሮችን አቅልሎ ማየትና መፍትሔውን መፈለግ… እነዚህ ለመመካከር የሚረዱ ሥነ ሥርዓቶች ናቸው።
መተናነጽ የመመካከር ግቡ ነው። የታነጸ ቤት ማረፊያ ይሆናል። የምናሳርፍ ሰዎች፣ ሌሎችን የምንቀበል ቤቶች ለመሆን መተናነጽ ወሳኝ ነው። ሕንፀት ግን ጥንቃቄ ይፈልጋል፣ ነፋስ ሥራውን ስለሚያውክም መጋረድ ያሻዋል። እንዲሁም መመካከር በጥንቃቄ ሊሆን ይገባዋል። ጥንቃቄ ከጎደለው አደጋ አለው። መመካከር መተያየት እንደሆነ በዕብ. 10፡24 ላይ ተጠቅሷል። አንዳችን የሌላው ዓይኖች የምንሆንበት፣ አንዱ ላንዱ ዘብ የሚቆምበት ነው። ስንተያይ አንዱ የአንዱን ጀርባ ያይለታል። መተያየት አራት ዓይና ያደርጋል። የመመካከርና የሕንፀት ዘመን ያድርግልን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ