እንግድነት ተቀባበሉ
“ያለ ማንጎራጎር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ” /1ጴጥ. 4፡9/
እንግዳ ከብዙ ዓይነት ስሜት ጋር ወደ እኛ የሚመጣ ነው፡፡ ምናልባት ተደስቶ ሊያስደስተን አሊያም አዝኖ ሊያርፍብን የሚመጣ ነው፡፡ እንግዳ ወደ እኛ ሲመጣ ችግሩን በውስጡ ያምቃል እንጂ ለእኛ አይነግረንም፡፡ የሚገርመው ግን አስልቶ የመጣው ፊታቸውን ካየሁ እድናለሁ፣ ስሜቴን እገዛለሁ ብሎ ነው፡፡ ሲያየንም ይፈወሳል፡፡ እንዴት ቢያከብረን ነው? እንዴትስ ቢወደን ነው? እንግዳ መንገዱን ሲሄድ፣ በሩን ሲያንኳኳ የሚናፍቀው የእኛን ፊት ነው፡፡ እንግዳን በብሩህ ፊት መቀበል ይገባል፡፡ ምክንያቱም “እንግዳ ብሆን አልተቀበላችሁኝም” የሚለው የጌታ ጥያቄ ራሱ ጌታ እንግዳ ሆኖ እንደሚመጣ ያሳያል፡፡ በምናውቀው ሰው መልክ የመጣው ራሱ ጌታ ነው፡፡ ምናልባት ቸኩለን አሊያም ልንወጣ አስበን ይሆናል፡፡ እንግዳን ግን በብሩህ ፊት መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ትልቁ ግብዣ ፍትፍት ሳይሆን ፊት ነው፡፡ ፊት ብቻም አይበቃም፣ እግዚአብሔር የሰጠንን በረከት ማቅረብ አለብን፡፡
የቀደሙት ወላጆች በትንሽ ገቢ ብዙ ቤተሰብና እንግዳ ሸኝተው፣ በብዙ መከራ ውስጥ ከጭንቀት ድነው ኖረዋል፡፡፡ ምሥጢሩ ምንድነው? ስንል የበረከትን ኑሮ መለማመድ ነው፡፡ የበረከት ኑሮ ባለው ላይ መጨመር ሳይሆን ማካፈልም ነው፡፡ “በበረከትም የሚዘራ በበረከት ደግሞ ያጭዳል” /2ቆሮ. 9፡6/ ይላልና፡፡ እኛ ገቢያችን የበለጠ ሆኖ የማይበቃን፣ በመከራችን ረድኤት የምናጣው ምናልባት ማካፈልን ስለረሳን ሊሆን ይችላል፡፡
ልብ አድርጉ! አብርሃም እንግዳን በመቀበሉ እግዚአብሔርን ተቀበለ፡፡ ተስፋውም ተፈጸመለት፣ ለሎጥም ማለደለት፡፡ ሎጥ እንግዳን በመቀበሉ መላእክትን ተቀበለ ስለዚህ ከምትጠፋ ከተማ ጋር አልጠፋም፡፡ ሰዶምም በዚያ ምሽት እንግዶችን ብትቀበል ኖሮ መፍትሔ ታገኝ ነበር፡፡ ስህተቷ እንግዶችን አለመቀበልም ነበር /ማቴ. 10፡15/፡፡ የጌታን እንግዶች አለመቀበል ከሰዶም ሰዎች ጥፋት ጋር አብሮ መጠቀሱ ይገርማል፡፡ እንግዳ ትልቅ በረከት አለው፡፡ በበጀት መኖርና በበረከት መኖር ልዩነቱ በበረከት መኖር ደስታ ይሰጣል፡፡
እቤቴ ገብታችሁ አልበላችሁም ብለው የተቀየሙን እነዚያ ደግ ወላጆቻችን ይባረኩ፡፡ በራቸውን ከፍተው ለተጠማው ያጠጡ እነዚያ እናቶቻችን ይቀደሱ፡፡ እነዚህ ደጋግ ሰዎች ናቸው የምድሪቱን ስቃይ ሲቀንሱ የኖሩት፡፡ ለክፉ ቀንም መሻገሪያ ሆነዋል፡፡ እነርሱ ተቀብለዋችሁ ትምህርታችሁን የጨረሳችሁ፣ ከአገር የወጣችሁ ውለታ አትርሱ፡፡ ትንሹን ስህተት አታጉሉ፡፡ ከልጃቸው እኩል አላዩኝም አትበሉ፡፡ “የባዳ ሞኝ ከልጅህ እኩል አድርገኝ ይላል” ይባላል፡፡
እንግዶችን ለመቀበል አንዱ ችግር አለማሰብ ነው፡፡ “እንግዶችን ለመቀበል ትጉ” ተብሏልና /ሮሜ. 12፡13/፡፡ ሌላው ማጉረምረም ነው፡፡ እንግዳን መቀበል ግን አገልግሎት ነው፡፡ በደስታ ስናደርገው እንባረካለን፡፡ በእውነት ዛሬ መሄድ ብናስብ ማን ጋ እንግድነት እንሄዳለን? ጭልም ይልብናል፡፡ ይህ የሚያሳየን መግቢያ እየጠፋ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ እኛ እንጀምረውና በሮች ይከፈቱ፡፡ እርስ በርሳችን እንግድነት እንድንቀባበል፣ መገናኘታችንም ለጌታ ክብር እንዲሆን ጸሎቴ ነው፡፡ ቡሩካን ቅዱሳን ሁኑ!