መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » እርስ በርሳችሁ » እርስ በርሳችሁ /19/

የትምህርቱ ርዕስ | እርስ በርሳችሁ /19/


እረኞችን አክብሩ
“እንዲሁም፣ ጎበዞች ሆይ፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” /1ጴጥ. 5፡5/፡፡
እረኛ የሚፈልጉ በጎች ናቸው፡፡ የዱር አራዊት እረኛ አይፈልጉም፡፡ እርስ በርሳቸው ወይም በጉልበት የሚበልጠው ይመራቸዋል፡፡ እረኛ ግን በጉልበት የሚያንስ ሊሆን ይችላል፡፡ ባለ አደራ ነውና ይመራል፡፡ አዎ የቤት እንስሳት እረኛ ይፈልጋሉ፣ የዱር አራዊት ግን እረኛ አይፈልጉም፡፡ ክርስትና ተጠሪነት ያለው ሕይወት ነው፡፡ ማንም እንደ ፈለገው የሚኖርበት ሳይሆን በእረኝነት ሥር በትሕትና የሚኖርበት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ብዙ ድምፅ የለም፡፡ የእረኞች ድምፅ መሰማት አለበት፡፡ “የወፍ ዘፈን አውራጁ አይታወቅም” እንዲሉ እንዲሁ መንጫጫት ያለባት ተቋም አይደለችም፡፡ ዛሬ እረኝነት እየተጠላ ቤተ ክርስቲያን በሰፈር ጎበዝ ለመመራት እየተጓዘች ይመስላል፡፡ የዘመነ መሳፍንት ትልቁ ችግር፡- “በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር” ተብሎ ተገልጧል /መሳፍ. 21፡25/፡፡ ንጉሥ ወይም መሪ በሌለበት አንድ መንገድ የለም፡፡ ሥልጣንን እስካላከበርን የምንጓዘው ወደዚያው ነው፡፡ ዛሬ የምናያቸው ብዙ የድንኳን አብያተ ክርስቲያናትም በአብዛኛው እረኝነት የማይፈልጉ ሰዎች፣ የአኩራፊዎች ስብስብ እንጂ የመብዛት ውጤት አይደለም፡፡ አካላዊ ግንኙነት እየቀረ ሰዎች የኢንተርኔት አማኝ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
እረኞች ወይም የሃይማኖት አገልጋዮች በኢትዮጵያ ክብር ካጡ ግምሽ ምእት ዓመት እየተቆጠረ ነው፡፡ የወለደውም እግዚአብሔር የለሽ ሥርዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር የለሽነት ከአደባባይ ወድቆ የገባው በሰው ልብ ውስጥ ነው፡፡ ዛሬ የሚደረገው ክፋት እግዚአብሔር መኖሩን የሚያምኑ ሰዎች የሚሠሩት አይመስልም፡፡ በዘመናችን ባለው ክብር የለሽነት እግዚአብሔር አዝኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የሁከት ስፍራ ሆናለች፡፡ በእኛው ዘመን ፓትርያርክ በጫማ ሲመታ አይተናል፡፡ በእኛው ዘመን ጳጳሳትን ልብሳቸውን ገልበው ሰዎች ሲሰድቡ ተመልክተናል፡፡ ፊደል ቆጠሩ ልጆቻቸው ደግሞ በኢንተርኔት ጫካ ተሸሽገው አባቶችንና አገልጋዮችን ሲያዋርዱ እያነበብን ነው፡፡ እነርሱ የሚጽፉት እኛ ስለምናነብ ነውና ቅጣቱ ሲመጣ የጋራችን ነው፡፡ አባቶች ሲዋረዱ የሳቅን የሚያዋርዱ ልጆች መውለዳችን እርግጥ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ስትታመስ ከመጸለይ ጎራ የያዝን የእኛ ትዳር መታመሱ አይቀሬ ነው፡፡ ቤቱን እያፈረሱ ቤትን መገንባት የማይታሰብ፣ እግዚአብሔርን በጻድቅነቱ ያለ ማወቅ ሞኝነት ነው፡፡ ሌሎች ሲወጉ በእኔ አልደረሰም ብለን ፀጥ ያልን እኛ የተወጋን ቀን አጽናኝ አናገኝም፡፡
ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጎበዞች ሆይ” በማለት ወጣቶች እረኞችን እንዲያከብሩ ያስጠነቅቃል፡፡ በቤተ ክርስቲያን የዕድሜ እርከን የሚያመጣው ጠባይ ወይም የሴትነትና የወንድነት አመል ሊኖር አይገባውም፡፡ ሊኖርና ሊታይ የሚገባው የክርስቶስ መልክ ብቻ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ ትዕቢተኞች እነማን ናቸው? እረኞችን የማያከብሩ ናቸው፡፡ እነዚህ በቀጥታ የሚጣሉት ከእግዚአብሔር ጋር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጠውን ጸጋና ክብር የሚያስጠብቅ አምላክ ነው፡፡ በቃሉ ያገለገሉአቸውን እረኞች የሚያከብሩ ትሑታን ደግሞ ጸጋ ይጨመርላቸዋል፡፡ ልብ አድርጉ መከባበር በሌለበት መደማመጥ፣ መደማመጥ በሌለበት መጓዝ የለምና እግዚአብሔር የትሕትናን መንፈስ ያድለን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም