የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ /20/


ተጠባበቁ
“ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ” /1ቆሮ. 11፡33/፡፡
ቤተ ክርስቲያን የፍቅር ደሴት ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከዓለም ልዩ የሚያደርጋት የመዋቅር ሰንሰለቷ፣ የሥልጣን ተዋረዷ፣ የአመራር ስልቷ፣ የተዘረጋው ፕሮጀክቷ፣ የልማት እቅዷ አይደለም፡፡ የፍቅር ኃይሏ ነው፡፡ ሞትን ያሸነፈ ፍቅር ያለውን አምላክ ስለምታመልክ ፍቅር መለያዋ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን የምእመናንን ፍቅር ከሚያሳድጉ ሥርዓቶች አንዱ የፍቅር ግብዣ ነው፡፡ በጥንት ዘመን የነበሩት ምእመናን በየሳምንቱ አብረው ማዕድ ይቆርሱ ነበር፡፡ ሁሉም ሰው በየተራ የሚደግሰው ሲሆን በዚህ ላይ ግን አንዳንድ ችግሮች ተገኝተዋል፡፡ የመጀመሪያው የኅብረት ማዕዱን የሚበሉት በተከፋፈለ ልብ ነበር፡፡ ማዕድ የአንድነት መግለጫ ነው፡፡ አንድነቱ በሌለበት መግለጫው ሐሰት ሆኖ ነበር፡፡ ስለዚህ አንድ እንዲሆኑ ሐዋርያው ይመክራል፡፡ ሌላው ችግር በመካከል ብዙዎች እየተራቡ ድግሱ ተርፎ የሚፈስ ነበር፡፡ ብዙዎችም ይሳከሩ ነበር፡፡ ድግሱን አሳንሶ ድሆችን መርዳት ግን ትልቁ ግብ ነበር፡፡ ሌላው ችግር ባለጠጎች ከፍ ያለ ድግስ እየደገሱ ድሆችን አሳቅቀው ነበር፡፡ ስለዚህ ድግሱ አነስተኛና መጠነኛ መሆን ነበረበት፡፡
ሌላው ጉድለት ማዕዱን በመጠባበቅ አይቆርሱም ነበር፡፡ የአንድነት ማዕድ አብሮ ሊቆረስ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው፡- “ስለዚህ፣ ወንድሞች ሆይ፣ ለመብላት በተሰበሰባችሁ ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ” ያለው /1ቆሮ. 11፡33/፡፡
በአገራችንም ብዙ የማዕድ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሰንበቴው፣ ጽዋው፣ ማኅበሩ፣ ፀሪቀ መበለት፣ ዛቲ… የሚባሉ አገልግሎቶች አሉ፡፡ እነዚህ የዕለት፣ የሳምንትና የወር አገልግሎቶች ናቸው፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች ከወንጌል ትምህርት ጋር፣ ከእውቀት ጋር ብንይዛቸው በጣም ጠቃሚ ናቸው፡፡ ሁሉም የሚያመለክቱት አንድነትን ነው፡፡ የዕብራውያን ፀሐፊ፡- “በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ” /ዕብ. 10፡25/ ብሏል፡፡
አብሮ መብላት በጣም ደስ ይላል፡፡ ፍቅራችን ዕለት ዕለት ማደግ ይገባዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ደግፎ የሚያቆማት የምእመናን ኅብረት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የብዙ ማኅበራት ውጤት ናት፡፡ ኅልውናዋንም የምትጠብቀው በማኅበራት ምእመናንን በማቀፍ ነው፡፡ ወንዝን ትልቅ የሚያደርገው ገባሮቹ ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን አንዲት ናት፡፡ በማዕድ አገልግሎት እርስ በርስ መጠባበቅ ይገባል፡፡ የየራስን ጎራ መያዝ አይገባም፡፡ ይህ የጋበዝነውን ጌታ ማሳዘን ነው፡፡ በጸሎት በተጀመረ ጉባዔ ጌታ አለ፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ክፉ ሰው ጋብዞ ነገር የሚያበላ ነው፡፡ ጌታን ጋብዘን ጭቅጭቅና መለያየትን ማሳየት እጅግ ክፉነት መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡ በማዕድ ብቻ አይደለም በሁሉም ነገር እንድንጠባበቅ እግዚአብሔር ይርዳን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ